“ልትነግሪኝ የምትፈልጊው ነገር አለሽ?”
“ማለት? ስለምን?”
“እኔ እንጃ ቦስ አባትሽ እዚህ ቢሮ እግራቸው ከረገጠ ቀን ጀምሮ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ፍፁም ልክ አይደለሽም። ያዘንሽ ያዘንሽ ፣ የተከፋሽ ፣ የሆነ ነገር ያደከመሽ አይነት ነው የምትመስዪው።” ሲለኝ ለቅፅበት ያደከመኝን ሁሉ ልነግረው ዳድቶኝ ነበር።
ራሴን አውቄ ሀላፊነትን መሸከም ከቻልኩበት ጊዜ ጀምሮ ለሚያውቀኝ ሰው ወይም በምንም አጋጣሚ ቢሆን ድጋሚ ላገኘው ለምችለው ሰው ስለራሴ ተናግሬ አላውቅም። ነገር ውስጤ ተቆልሎ የሆነ ዓይነት እምቅ ሀይል ሆኖ እንደ ኒውክለር ሊፈነዳ የመሰለኝ ወቅት ላይ አንድ ሶስቴ ከዛን ቀን በኋላ ፊታቸውን አይቻቸው ለማላውቃቸው ሰዎች የተሰማኝን ዝርግፍግፍፍፍ አድርጌ ከመፈንዳት ተርፊያለሁ። አንዷ ‘ነገ አረብ ሀገር ልሄድ ነው።’ ያለችኝ ፀጉር ቤት ያገኘኋት ሴት ናት። ፀጉራችንን ተስርተን ስንወጣ ለማኪያቶ ካፌ ተቀምጠን ያወራኋት። ሁለተኛው ናዝሬት ለስራ ሄጄ ያረፍኩበት ሆቴል ብቻዬን ራት ስበላ አይቶኝ ‘እንብላ’ ባለኝ ሰበብ ያወቅኩት ጎልማሳ ነው። (ሊበላኝ(ሊያባላኝ) ባሰበ ምሽቱን የተበላው።) ሶስተኛው ከቂሊንጦ ስመለስ ሊፍት የሰጠኝ ሽማግሌ ነው። አንዳቸውንም ከዛ በፊትም ሆነ ከዛ በኋላ አይቻቸው አላውቅም። ስሜን አያውቁም ፣ ማን መሆኔን ፣ የት መሆኔን አያውቁም……… ሳወራላቸው ነገ ሲያዩኝ ምን ይሰማቸዋል? አልልም…… ሳለቅስ ወይ ስዝረከረክ ይዳኙኛል አያሰጋኝም…… በነሱ ፊት መሸነፌ ወይ ተስፋ መቁረጤ ድክመቴ አይሆንም። …… ለምንም ግድ የለኝም። ልግባቸው ላደናግራቸውም ጉዳዬ አይደለም። የተሰማኝን በሙሉ ዘርግፌ ተንፍሻለሁ።
ለሚያውቀኝ ሰው እንደዛ አላደርግም። ለሚያውቁኝ ሁሉ(ከቤተሰቦቼ ውጪ) ያቺ አልቅሳ የማታውቀው ፣ብርቱዋ ፣ ደካማ ጎኗን ማንም የማያውቅባት፣ መጠቃቷን ማንም የማያውቅላት… … የጉብዝና ምሳሌ የሆነችዋን ራሔል ነኝ።
“ፍትህ አንተ ደግሞ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ስራህን እርግፍ አድርገህ ትተህ እኔን ስራ አድርገኸኛል። am fine!! በቀን አስሬ ቢሮዬን የምትከፍተውን ነገር አቁም። please?” አልኩት። ብዙ ቀን ብዬዋለሁ ሰበብ እየፈለገ በጥያቄ ይወጥረኛል እንጂ።
“እሺ። ከፈለግሽኝ ግን አለሁ።” ብሎኝ ቆይቷል። ከቢሮዬ ግን አልወጣም። ከወንበሩም አልተንቀሳቀሰም። ሁሌም የማስበው የኖህ ታሪክ ትዝ አለኝ። ከውሃ ጥፋቱ በኋላ ኖህም ገበሬ ሆነ። ወይንም ተከለ። ከወይን ጠጁም ጠጣና ሰከረ። …… በድንኳንም ውስጥ ራቁቱን ሆነ ታናሹ ልጁ ካምም የአባቱን እርቃን ባየ ጊዜ ተሳለቀ። በአባቱ ገመና ሙድ ያዘ። ሁለቱ ልጆቹ ያፌትና ሴም ግን እርቃኑን እንኳን እንዳያዩበት አክብረውት ፎጣ በትከሻቸው አድርገው የኋሊት እየተራመዱ የአባታቸውን እርቃን ሸፈኑ… …… ኖህም ካምን ረገመው… ………… ይመስለኛል። ሲመስለኝ ሲመስለኝ……… የካም ነገድ የአክሱምን ልጅ ወለደ…… የአክሱምም ልጅ ልጆች በወንድምና ወዳጃቸው ገመናና ድክመት ሲደነቋቆሉ… … ሲሸረዳደዱ…… አንዱ የአንዱን ድክመት ሲጋለቡ ኖረው ኖረው። የእንጀራ እናቴ አባት ላይ ደረሱ። እሳቸውም ቀንደኛ ሸርዳጅ የሆነች ትውልድ አፈሩ……… ምናምን ምናምን………
የኖርኩት ዘመን የተረዳሁት አብዛኛው ሰው ከትልቁ ስኬትህ ውስጥ እንኳን ምናምኒት የምታክል ውድቀትህን ወይ እንከንህን ይፈልጋል። ካገኘብህ አለቀልህ። ሰማይ ያከለ ስኬትህን የጎመንዘር በምታክል እንከንህ ያጣፋልሃል።
“ፍትህ?”
“አቤት ቦስ?”
“ነገ ሰርጉን ትሄዳለህ እንዴ?”
“አወና!! እንዴ ቆይ ቆይ…… ትሄዳለህ ነው ትመጣለህ? ያ ማለት የእህትሽ ሰርግ ላይ አንቺ አትኖሪም ማለት ነው? ኦ……ኬ …… I think ይሄ ኬዝ ካሰብኩት በላይ ሊመስጠኝ ነው። ምንድነው እሱ?”
“ምንም big deal አይደለም። መሄድ አለመሄድህን ለማወቅ ነው። አበቃ!! የሆነ ታላቅ ግኝት ያገኘህ አታስመስለው።”
“እሄዳለሁ።” ብሎኝ ዓይኖቹን ዓይኖቼ ውስጥ ዘፍዝፎ ስሜቴን ሊጨምቅ ይታገላል።
“መልካም።” አልኩት ድምፄ ከስሜቴ ጋር አብሮ ሲወርድ እየታወቀኝ።
“በቃ?” ብሎ አፈጠጠብኝ ከተቀመጠበት መንጭቆ እየተነሳ። “በቃ ሌላ የምትዪኝ ነገር የለም?”
“እንዴ? ምን እንድልህ ነው የምትፈልገው?”
“አላውቅም!! ብቻ ከቤተሰብሽ ጋር በተያያዘ አንድ እንዳላውቅ የፈለግሽው ነገር ያለ ይመስለኛል። አላውቅም!! ንገሪኝ ማወቅ ያለብኝ ነገር ካለ ከሌላ ሰው ከምሰማው በፊት ንገሪኝ!”
“Excuse me? ከሌላ ሰው ከመስማትህ በፊት?ራስህን ምን ቦታ ላይ ነው የሰቀልከው ባክህ?” ሆኖ እንደማያውቀው እየጯጯህን ነው።
“Sorry boss! ራስን መስቀል አይደለም። እንደጓደኛ……”
“እኔና አንተ ጓደኛሞች አይደለንም! ደግሞ ቦስ አትበለኝ። አለቃህ አይደለሁም። ስም አለኝ። እኔና አንተ የስራ ባልደረቦች ብቻ ነን። የሚያገናኘንም ስራ ብቻ ነው።” ንግግራችን የማያስፈልገውን ያህል ቁጣ እየተቆጣሁ እንዳለሁ ራሴን ስሰማው አውቃለሁ። ግን ቁጣዬ ምክንያቱ ፍትህ ብቻ አልነበረምና መመጠን አልችልም።
“እሺ ጓደኛሽ አድርጊኝ? I mean not just for sayin… … real ጓደኛሽ ልሁን?።” አለኝ ሹክሹክታ በመሰለ ድምፅ እና ከኔ በተቃረነ እርጋታ። ሁኔታዬ ራሴኑ አሳፈረኝ። እሱ ላይ የምጮህበት ምንም ምክንያት የለኝም። ፀጥ አልኩ። ጠረጴዛዬ ላይ በአንድ መቀመጨው እየተቀመጠ
” I know አንቺ በጣም ጠንካራ ሴት ነሽ። ያ ማለት ግን ሰው አያስፈልግሽም ማለት አይደለም። ያንቺን ጭንቀት ማወቄ ላንቺ ያለኝን ቦታ አይቀንሰውም። በምታልፊበት ነገር ሁሉ ውስጥ አልፈሽ እዚህ መገኘትሽ ምን ያህል ጠንካራ ሴት መሆንሽን ያገዝፍብኛል እንጂ።” አለኝ የፍትህ በማይመስል እርጋታና ብስለት።
“ለምን ብለህ ምክንያቱን አትጠይቀኝ። እባክህ ሰርጉን አትሂድ?” ማለት ብቻ ነበር የመጣልኝ ሀሳብ
“እሺ።” አለ እንደዘበት። ከዛም ያልሰጠሁትን እጄን ፈልቅቆ እየማለ “ ይኸው !ቦስ ይቅርታ ራሔል ሙች! አልሄድም። ከፈለግሽ በቤተሰብሽ ኬዝም አልገባም። ያ የሚያስደስትሽ ከሆነ ምክንያትሽንም ማወቅ አልፈልግም። ራስሽ ፈልገሽ እስካልነገርሽኝ ድጋሚ አልጠይቅሽም። ግን አንድ እንድታደርጊልኝ የምፈልገው ነገር አለ!” እያለኝ ስልኬ ጠራ። ከቤት ነው። አንስቼው ስለእማዬ በሰማሁት ነገር እግሮቼ ዛሉብኝ። የብርትኳን ቢላዋ አንስታ ታፋዋ ላይ ሰክታለች። ሰራተኛዋ እየተርበተበተች ነው የነገረችኝ። ስለእማዬ በሰማሁ ቅፅበት ፍትህን ረስቼዋለሁ።
“ምንድነው እሱ? ምንድነው? እናትሽ ምን ሆነው ነው?” አፌ ቃላት መትፋት አቃተው። ምንም አላስፈቀደኝምም። አልጠየቀኝምም። ስልኬን አንስቶ መልሶ ደወለ። ልሄድ ቆሚያለሁ። ግን መንቀሳቀስ ከበደኝ። ከሰራተኛዋ ጋር እያወራ እንደሆነ አውቃለሁ። ግን አልሰማውም። ኮቴንና ቦርሳዬን ሰብስቦ እጄን መንጭቆ ይዞኝ ሲወጣ እግሬን ለመራመድ ማዘዜን ባላውቅም ተከትዬው መኪናው ጋር ደርሻለሁ። በሩን ከፍቶ መኪናው ውስጥ ሲያስገባኝ፣ ስንሄድ፣ ከሰራተኛዋ ጋር ሲደዋወል፣ እቤት ይዞኝ ሲገባ… …… ጆሮዬ ጭውውውውው ይልብኛል። ጭንቅላቴ የሆነ ከባድ ነገር እንደተጫነብኝ ለአንገቴ ከብዶታል። …………