Tidarfelagi.com

ሥግር ልብ ወለድ፤ ሕፅናዊነት (ክፍል 4)

ሕፅናዊነትን በዚህ ዘመን አስፈላጊ ያደረጉት የአገሪቷ ሁኔታዎች መብዛት፣ መስፋት፣ የተለያዩ ብቻ ሳይሆን መያያዛቸውም ነው። ጥቂቶቹን ወይም ክሱቶቹን ልጥቀስ

1. ከስድሳ ስድስት ዓመተምህረት በፊት የዜጎች ስደት ትልቅ ጉዳይ አልነበረም።

2. ሽብር ትልቅ ጉዳይ አልነበረም።

3. በፖለቲካ ምክኒያት መሞት ትልቅ ጉዳይ አልነበረም።

4. የፖለቲካ ድርጅቶች መኖርና መብዛት ትልቅ ጉዳይ አልነበረም።

5. ጦርነት ትልቅ ጉዳይ አልነበረም።

6. ዲሞክራሲ ትልቅ ጉዳይ አልነበረም። (ሁሉ ድርጅቶች በሰራተኛው አምባገነንነት ያምኑ ነበር)

7. የአየር ፀባይና የማያቋርጥ ድርቅ ትልቅ ጉዳይ አልነበረም።

8. ኤች አይ ቪ ትልቅ ጉዳይ አልነበረም።

9. ግሎባላይዜሽን ማዕከሉን ሲያጠናክር ሁሉን አንድ ለማድረግ መጣሩ ትልቅ ጉዳይ አልነበረም።

10. ከሕፅናዊ አፃፃፍ ስልት ጋር የሚመሳሰለው የሳይበር ዓለም አልነበረም።

11. ጎሰኝነት ከሚንቧችበት ወለል በአጭር ጊዜ ተነስቶ እዚህ አልደረሰም።

ወዘተ

በዝርዝር ሲቀርቡ የብቻ ስልጣን ያላቸው ይምሰሉ እንጂ የተያያዙ ጉዳዮች ናቸው። እንኳን እነዚህ ሁሉ ይቅርና አንዱ ብቻ አዲስ ጉዳይ ቢሆንም የአፃፃፍን ዚቅና ይዘት የመለወጥ ስልጣን ሊኖረው ይችላል።

አስራ አንዱም በቅርብ፣ በሩቅ፣ በጥልቀትና በግልብ የተቆላለፉ ናቸው። ፖለቲከኞች እንደ አቋማቸው፣ እንደሚመቻቸውና እንደ ጌታቸው አይነት የቅደም ተከተል ተዋረድ ሊያወጡ ይችላሉ።

ሥግር ለምን?

1. የስነ ዕውቀት ተስፈኝነት (epistemological optimism)

የማሥገር ሃሳብ የመጣው፤ አለም ፖሊፎኒክ (ብዙ ድምፅ ያላት) ከመሆኗ ነው። አለም ለተለያየ እውቀት/እውቀቶች ሳታቋርጥ በፍጥነትም ይሁን በቀስታ የምትገለጥ ናት። መገለጥዋ ወይም አለመገለጥዋ አንፃራዊነት እንጂ ስለ ዕውቀት ማለቅ/መጠናቀቅ አይጠቁምም።

በባክቲን አባባል በነዚህ ቃላቶች ውስጥ ያለፈው ዘመንና ምኞት (ትንቢት) የተሰባጠሩበት ሲሆን፥ ሥግር እነዚህን የማገናኘት ወይም የማያያዝ ስልት እንዲኖር ሆነ ብሎ መጣር ማለት ነው።

ሥግር፤ በነዚህ ለተረክ ከተሰደሩት ቃላትና አምባዎች ውስጥ የግንኙነት potential (ዕምቅ ሃይል) አለ ብሎ ስለሚያምን የስነ ዕውቀት ተስፈኝነት (epistemological optimism) አለበት።

2. የጅጊ ብሩህነት (Collective Intelligence)

የመርበብቱ (Network) ዓለም የምናልባታዊነት ዓለም ነው። እንደ ጉንዳን ቤት ወይም እንደምስጥ ኩይሳ ነው። ከላይ ብቻ ሳይሆን መረቡ በማይታይ መልክ ውስጥ ለውስጥ ይጓዛል። ወሰኑንም ይሄ ነው ማለት ይከብዳል።

አሜሪካዊው ሴማዮቲሺያን ፒርስ፤ ‘አንድን ጥቁር ነጥብና ነጩን መደብ የሚያዋስናቸው ምን ቀለም ነው?’ እንዳለው ድካ (Genre) ማበጀት የሚከብደው ለዚህ ነው። ድካ ወሰን ነው።

በሥግር በተዋቀረ ሕፅናዊ ዓለም ውስጥ የመረቡ ወሰኖች ማንንም ሳያማክሩ በግብታዊነት ስለሚለዋወጡ ይሄም የድርሰቶች ተፈጥሮ ሳያቋርጥ የሚገለጥ ተነቃናቂ ጉዳይና ስያሜን የሚጋብዝ እንጂ ደርቆ የቀረ የጥቂት ግለሰቦች ስም እየተጠራ ራሳችንን የምናሞካሽበት አይሆኑም።

በፖለቲካዊ ግፊት፥ በይሉኝታና በጭፍን ስግደት አላስፈላጊ ዝክር ውስጥ አንገባም። የግለሰብ ብቻ ሳይሆን በስነ-ፅሁፋችን ውስጥ የጅጊ ብሩህነት (Collective Intelligence) ይኖራል።

ወደፊት የሚያጋጥመን ስፋቱ መጠን የሌለው ከአድማስ አድማስ የተዘረጋ እንጀራ ነው። ካለንበት በተነቃነቅን ቁጥር ልንደርስበት ልናየው የማንችል ጠርዝ አለው። አለምን ይሸፍናል።

ኢትዮጵያውያን በዓለም ተዘርግተዋል። እየከፋቸውም ደስ እያላቸውም ይኖራሉ። እንጀራው ያን ያህል ይሰፋል ማለት ነው። እነዚህን ተከትሎ ጤፍ ይዘምታል። የኢትዮጵያን ባንዲራ የጠላ ሰው እንጀራዋን ዘርግቶ ምሳውን ይበላል። ካፈጠጠ እውነት ቢሸሽም ወደደም ጠላም እንጀራ ቀርቦ ኢትኤል ጥንት በሰራው ዳቦ ይቆርባል። ተገንጣይ ነኝ ባዩም በእጅ አዙር ለአገሪቱ ይሰግዳል።

ድሉዝ እንደሚለው ዛፎች አሰልችተውናል። ብዙ አሰቃይተውናል። አመለካከታቸው በአስልቺና በአስመራሪ የግለሰቦችና የቡድኖች ማዕከላዊነት ስር ጥሎናል። ለ10000 አመታት ያህል የሰፈነብን በተዋረድ በዋርካ የማሰብ ጣጣ በተለያየ መልክ አስሮናል። ዛፎች ካሰለቹን የምንወስደው አማራጭ የሕፅናዊነት ልዋጭ ነው።

3. አገራዊ የስነ ፅሁፍ መልክ

ብዙ ጊዜ መፅሀፍ ማንበብ በመስመር ማንበብ ነው። የሕፅናዊነት ጥረቱ በሥግር አፃፃፍ መስመራዊነትን ደጋግሞ የመስበርና ትክክለኛ የእውነታ ቅርፅ መስጠት ነው።

ድርሰቱን ግብታዊነት ውስጥ በማስገባት ለበላይ ገዢ ሃሳብ እንዳይገዛ አዲስ ሂደት (process) ማምጣት ነው። በዚህ መቃጣት ሁለትና ከሁለት በላይ በሆኑ የማስተማሰል (representation) ስራዎች ውስጥ እናልፋለን። የተለያዩ ደራሲዎችና ድርሰቶች በማምጣት ያልጠበቅነው ሁኔታ በመፍጠር በተለያየ የዘይቤ እርሾ መደሰት በፎርማሊስቶች ቃል (radical defamiliarization) ይሆናል።

በዚህ ድርሰት ውስጥ ውሱን (deterministic) ኩነቶች ድንበራቸው ይሰበራል። ገለልተኛ የመሰሉ አምባዎች በስድራት ኪነት የግንኙነት መርበብት (network) ውስጥ ይገባሉ። ድርሰቶች በአርዕስት፣ በቦታ፣ በግለሰብና በጎሳ የማይገደቡ ፈሳሽ ወንዞች ይሆናሉ። ያውም ከአምባው የሚሸሹ ሳይሆን በመርበብት (Network) መልክ ይይዛሉ።

ይሄ አፍ የተባለው መፅሀፍ ማዕከል መሆንና ማቆም ብቻ ሳይሆን ብዙ የሚወራረሱ መድረሻና መጀመሪያቸው በሃያሲያን ብቻ የሚደነገግ በቅርብና በሩቅ የአፃፃፍ DNA የሚዋዋሱ ብሄራዊ ስድሮች ይሆናሉ። የሄ በተለይ የዚህ ሀገር የድርሰት መልክዓ ምድር ላይ የሚከሰት የአገራችን ስነ-ፅሁፍ መልክ ይሆናል።

4. አገራዊ ስያሜ

በባህላችን በግዕዝም ይሁን በአማርኛ (በተለይ በግዕዝ) የተለያዩ የቅኔ ቤቶች (ቦታ) እና የቅኔ አይነቶች አሉ። በአንፃሩ ግን ልብወለዶቻችን በዚህ ስልት ሀገርኛ ስያሜ ሲያገኙ አልሰማንም። እንደተኮረጁበት ባህል በእንግሊዝኛና በፈርንሳይኛ ድካቸው ሲጠረጠርና ሲሰየሙ ግን መዝግበናል። ቢያንስ ቢያንስ ሥግር በሂደት ከዚህ የማይሆን አራጣ ተበዳሪነት ያላቅቀናል።

5. መረባዊ የግንኙነት ስፍራ

የድርሰቶቻችን ታሪክ እንደነገስታቱ ታሪክ የተፃፈ ነው። በተለምዶ የስነ-ፅሁፍ ታሪክ የጊዜ አጥሩ የሚበጀው ፖለቲካዊ የለውጥ ዘመንን ተንተርሶ ነው። ለምሳሌ ከአብዮቱ በፊትና በኋላ፥ ከሐይለስላሴ በፊትና በኋላ እየተባለ።

ስለ ሥነ ፅሁፍ እድገት ስናወራ የምንጠቀምበት የጊዜ ስሌት እንዲህ አይነት በመሆኑ ስለ ሥነ-ፅሁፍ የሚወራ አይመስልም።

ብዙ ጊዜ ‘ማንን ደራሲ ታደንቃለህ?’ የሚል ጥያቄ እንሰማለን። መልሱ ዘመኑን የተከተለ ወይም ለዘመኑ የሚያቃጥር ሊሆን ይችላል። አስገራሚው ነገር፤ እንምረጥ ቢባል ማን እንደሚመረጥ ሰማይ ምድሩ፣ ወረቀቱና ካድሬው ያውቃሉ። ስማቸውን መጥራት ግን በሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የፖለቲካ አቋምም ሊሆን ይችላል። በስነ ፅሁፍ አፍቃሪነት ኮሮጆ ውስጥ የተደበቀ ጎሰኝነት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ የሚጠራው ደራሲ የሞተ ቢሆን ይመረጣል።

በግልፅ ያልተነገረ መናናቅ በእጅ አዙር የፖለቲከኞች ብልጣ ብልጥ ተፅዕኖ ይታይበታል። አንዳንዴ ተፅዕኖ ይኑርበት አይኑርበት ሳያውቅ ለማሽቃበጥ ብቻ የነባር ደራሲ ስም የሚጠራ ይኖራል።

ሕፅናዊነት ከዚህ ሊገላግለን ይችላል። ለሂስ የምንመርጠው የመረብ ቦታ የብዙ ደራስያን መገናኛ ስለሆነ ስልጣንን በመፍራት ወይም ለስልጣን ለማዳላት ወይም በሌላ ድብቅ ሰበብ አንድ ደራሲ የሌለበትን ተፅእኖ ፈጥሮ አይናገርም።

በባዶ ሜዳ ያለ ሂስ፤ በአፍ ቅብብልና ያለሙያዊ ሂስ የማንቆለጳጰስ ትርክት የተፈጠረው ተዋረድ ሕይወት የሚያራዝምበት ምክኒያት የለም።

አዲስ የሚመጡ ድርሰቶችን ገና ከገበያ ቀልቦ፤ ቢቻል ጫፍ ከተገኘ ፖለቲሳይዝ አድርጎ ጠባብ ጣባ ላይ መዘርጋት፥ ይሄን ካመለጠ ደግሞ እንዲረሳ በጥበብ አድማ ማስመታት ያየናቸው ናቸው። ሕፅናዊነት ስትፅፍ ግን መረብ ውስጥ ነህ። ያንተ ቦታና ማንነት የሚታየው ከመረቡ በተቀበልከውና በምትሰጠው ነው።

6. ምልዓት

ምሳሌ በአፍ ውስጥ ያለውን አንድ ምዕራፍ ብንወስድ በእርግጥ አላለቀም። መዝነን በትክክል የቀረውን መዘርዘር ባንችልም ያለውን እምቅ ሃይል ደራሲው አልተጠቀመም ማለት እንችላለን። ደራሲው የተመጠነ ጊዜ፥ እድሜ፥ የእውቀት ማነስ፥ የነርቭ ስርዓትና የአካል ብቃት ገደብ ስላለበት ድርሰቱን እየዘለለ ወይም እያቆራረጠ ይፅፈዋል እንጂ አይጨርሰውም። እያረገው አያልቅም። አለማለቅ ግዱ ነው።

ሥግር ይሄን ያላለቀ የማያልቅም ነገር መሙላት ነው። በዚህም ልምዳችን ስናልፍ ትረካ መስመራዊ እንዳልሆነ እንረዳለን። የአንድ ተረክ አውድ ‘ይሄ ጠባብ ቦታ’ ብቻ ሳይሆን አለም ወይም የተፈጥሮ የስበት ሃይል ፀሀይና ጨረቃ ወይም ሙሉ ኩሌው ሊሆኑ ይችላል። አውዱ በተለያየ ቦታ በመሰራጨቱና በተለያየ ጉዳይ ስር በመሸሸጉ እንጂ እንደ አንድ ስርዓት ወይም አምባ ከሌላው ስርዓት ወይም አምባ ጋር በመገናኘት የትብብር ሕልውና ውስጥ እንደሆነ ያሳያል። ድካ (Genre) አይወስነውም።

7. ተለዋዋጭ አውድ

ሰላማዊት ማናት? ለሚለው ጥያቄ እዚህ አፍ ውስጥ ያለችውን ገፀ ባህርይ ለመፈተሽ መነሳት አንድ ልብ ወለድ ብቻ በማንበብ አይመለስም። መጀመርያ ኤልዛቤልን፥ ከዚያ የስንብት ቀለማትን ከዛ አፍን ማንበብ አለብን።

ተከታታይ የሚሉት አይነት አይደለም። ተከታታይ ድራማ በቲቪ ሲሰራ ወይም በጋዜጣ ሲቀርብ ቃል ተገብቶ ነው። በተስፋችንና በምናገኘው ነገር መሃል ብዙ ልዩነት የለም። ያው የምናውቀው ተከታታይ ድራማ ይመጣል።

ሥግር ሲሰራ ግን ድሮ ከምናውቃቸው ገፀ ባህሪያት ማንና እንዴት እንደሚመጡ (የመለወጥ ጉዳይ ይኖራል) የምናውቀው ብዙ ነገር የለም። ዋናው ባህርይ ዋና ባህርይ አይሆንም። የሞተ ሊነሳ ይችላል። ምናልባትም ማንም ባህርይ ከቀድሞው በጥቅስ ላይመጣ ይችላል። አንፃራዊ (አነፃፃሪ) ትንታኔም አይደለም። በሰላማዊት ጉዞ ላይ ሰላማዊት ብቻ አይደለችም፥ ብዙ አውድም ይለዋወጣል። የአንባቢ አውድ፥ የሂስ አውድ፥ የዘመን አውድ ወዘተ።

7. ሕፅናዊ ግንዛቤ

አንደኛ የሕፅናዊነት ልዋጭ ሲጀመር የተቀዳው ከፍልስፍናዊ ምርምር ሳይሆን ከቁስ ነው። ይሄም ከአምስት ሺህ አመት በፊት የነበረው ህብረተሰብ ስለመረባዊ ግንኙነት የተረዳው ነገር አለ ብሎ ከመጠርጠር ነው። ቢረዳው እንግዳ አይሆንም።

ጤፍን ያላመደው ኢትኤል የተባለው ንጉስ አህያን ከፈረስ አዳቅሎ በቅሎን ያገኘ (በቅሎ ራይዞም ናት ወይም ንጥቀት ናት) ነው። እንደውም ከድንጋይ የሚፈልቅ ልዩ ውሃ ይጠጣ እንደነበር ይነገራል። ይሄ ኢትኤል የተባለ ንጉስ የተፈጥሮን መሰረታዊ አሰራር የቅጥ ይዘት (ሞርፎሎጂካል ይዘት) በመረዳቱ የተከሰተ እንደሆነ መከራከርያ ጥቅስ ማቅረብ ይቻላል። ማለት እንግዳ አይደለም።

ማኑኤል ደ ላንዳ the rhizome is not self-imposed conjectural view on our existence, but a fundamental topology of nature and underlying element to the complex fabric of life. ይላል።

ራይዞማዊ ግንዛቤው በዘመኑ የነበረ ግን ጎልቶ ያልወጣ ጉዳይ ነው። ሕዝቡን በማዕከልና በተዋረድ ቢተዳደርም ቢያንስ ንጉሱ የተረዳው ነገር አለ። እሱ እንደዛፍ ሲያስተዳድር ሕዝቦቹ ሕፅናዊ ኑሮአቸውን ይኖራሉ።

የሥግር አለም ምን ሊመስል ይችላል?

ሕፅናዊ ልብ ወለድ አያልቅም። እዚህ አሁን የተቀመጥንበት ቦታ ይሄን ወይም ያን መፅሀፍ አንብበን ጨርሰናል ብለን ስንዘጋው ሌላ ቦታ ያለ አንድ ደራሲ የመፀፉ የሆነ ጉጥ ላይ ሕፅን ሊሰራ እየተዘጋጀ ነው። ይሄም ማለት የእኔ ይህንን መፅሐፍ አንብቤ ጨረስኩ ማለት በቋፍ የተቀመጠ መደምደሚያ ይሆናል። በማላየው በማላውቀው ደራሲ ሥግር ሲሰራ ይሄ ያነበብኩት ድርሰት ያላለቀ ይሆናል። አፍን አንብቤ ጨረስኩ የሚለው አባባል አስተማማኝ መሆን ያቆማል። አንብቦ ያላነበቡ መሆን ወይም ማንበብን መጨረስ በመጨረስ እርግጠኛ አለመህልን አንድ ነጥብ ይሆናል።

ተምሳሌትነቱም እንደ ሕይወት ነው። ሁሉ ነገር እንዲያልቅ እንጠብቃለን። አለም ማለቂያ አላት። የመጨረሻ ፍርድ አለ ቢባልም አንደርስበትም። የመጨረሻ ፍርድም የለም። የምንኖረው ጠባቧን ቦታ በድፍረት ከአውድ አግልለን በማብጠልጠል አዋቂ መምሰል ብቻ ነው።

አዳም ረታ አንጋፋ የሀገራችን ደራሲ ነው፡፡

One Comment

  • weluteklit2017@gmail.com'
    ኢዞና ናዛኢ commented on December 1, 2018 Reply

    ከአቅሜ በላይ የሆነና በኔ ጊዜ ልረዳው የማልችል ትርክት ባይሆን:የሥግርን ፅንሰሀሳብን apply ባደርግ ግን የበለጠ አስተምህሮ አገኝበት እንደነበር አምኛለሁኝ።
    በጣም ጥልቅ ትንታኔ ነው…
    ፍሬ-ነገሩን አንጠፍጥፌ ለመረዳት ከአሁን በኃላ ሐተታው ሰንት ግዜ ማንበብ እንደሚጠበቅቢኝ እርግጠኛ አደለሁም።
    ጥበብ ትገለጥ ዘንድ ደራሲዎቻችን ልቦናቹና አዕምሮአቹ ይለምልም።
    አዳም ረታ ከልቤ አደንቅሀለሁ።
    እግዚሄር ይስጥልኝ …

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...