(ማስጠንቀቂያ …. አልባሌ ነገር የማትወዱ ሰዎች አታንብቡ … ኡኡኡኡኡ .. 🙆🏻♀️🙆🏻♀️ይሄን አልፋችሁ ካነበባችሁ እንዳትመክሩኝ)
“ከንፈር መሞከር ፈልጋለሁ።” አልኩት
“እስከዛሬ ተስመሽ አታውቂም።?”
“እስከዛሬ ፈልጌ አላውቅም።” ከንፈሩን አቀበለኝ።
ወራት ነጎዱ……
“ድንግል መሆን አልፈልግም።” አልኩት
“ገናኮ 18 ዓመትሽ ነው ማሬ። ለምን ትንሽ አንቆይም? ”
“አሁን ነው የምፈልገው።”…… አክሱሙን አቀበለኝ።
ወራት ነጎዱ………
“ጫት ለጥናት ጥሩ ነው ሲሉ ጊቢ ሰማሁ። መሞከር ፈልጋለሁ።”
“አይ አይ አይ…… ጥሩ አይደለም ማሬ ስሞትልሽ አትሞክሪ።” አለኝ እያንገፈገፈው
“ልንገርህ ብዬ እንጂ መሞከሬ አይቀርም። እነቤቲ ዛሬ እንቅማለን ብለዋል…… ” ሳልጨርስ ቀድሞ
“እሺ በቃ ፍቅሬ እሺ…… መሞከር ከፈለግሽ እኔም አብሬሽ እሞክራለሁ። ከኔጋ ቃሚ…… ” ጫቱንም ፍራሹንም ሰጠኝ።…… መቃም በፈለግኩ ቁጥር ከስራ እየቀረ አብሮኝ ቃመ።
ወራት ነጎዱ………
“ልመረቅ ስለሆነ ስክር ማለት እፈልጋለሁ ክለብ ውሰደኝ” አልኩት……
“እሺ እንደፈለግሽ ሁኚ እጠብቅሻለሁ።” አለኝ…… መጠጡን ቀዳልኝ… እንደፈለግኩ ሆንኩ……
ሰዓታት ነጎዱ……
“ማጨስ እፈልጋለሁ።”
“እማ ስካሩ አይበቃም? ፕሊስ ጭሱ ይቅር? “ለአፉ አለኝ እንጂ የፈለግኩትን ሳልሞክር ማቆሚያ እንደሌለኝ ያውቃል።
“እሺ ገዝቼልሽ ልምጣ? ”
“አልፈልግም የተጨሰ ግማሽ የደረሰ ሲጋራ ነው ማጨስ የምፈልገው።… እንደውም ያን ሰውዬ ስጠኝ እለዋለሁ።”
“እሺ እሺ በቃ የተጨሰ አይደል ማጨስ የምትፈልጊው? በቃ እኔ አጭሼ ሰጥሻለሁ።…… ከሌላ ሰው ከንፈር ተውሰሽ አታጨሺም! ” አጭሶ ሰጠኝ። አጨስኩ።… እስክመረቅ በጨፈርኩ ቁጥር የተጨሰ ሲጋራ አቀበለኝ።
ዓመታት ነጎዱ…… ብዙ ዓመታት…… እንደተመረቅኩ ከሃገር ወጣሁ።…… ተራራቅን…… ከጊዜ በኋላ መገናኘት አቆምን።… አገባሁ…… ወለድኩ…… ለበዓል ወደሃገር ቤት ተመልሼ ሳለሁ መንገድ ላይ አየሁት።…… ደነዘዝኩ። ያ ሊነኩት የሚያሳሳ ቆዳው ከስሎ…… የሚያንጠራራ መለሎ ቁመናው ጎብጦ… የሚያኮራ ደልዳላ አካሉ ኮስምኖ… አይሆንም እሱ አይሆንም!
“አቁምልኝ! አቁምልኝ! “ጮህኩኝ ባሌ ላይ… ዘልዬ ወረድኩ እና እጁን ይዤ አስቆምኩት።
“እማ አንቺ ነሽ ስካሬ እያስቃዠኝ ነው? ” አለኝ ከቃላቶቹ እኩል የርካሽ መጠጥ ጠረን እየተፋ
“አባ አንተ ነህ? ምን ሆነሃል? በየሱስም ምን አገኘህ? ታመህ ነበር? በየሱስ ስም…… ደህና ነህ? ቆይ ምንድነው የተፈጠረው?”
“አንቺ እማ! አንቺ ነሽ የተከሰትሽው! ሌላ ማን አለ አንቺ “…
የሆነ የአዳም ረታ መፅሃፍ ውስጥ ያለሁ ገፀ ባህሪ የሆንኩ መሰለኝ። እንጂማ እኔ በእውነታው ይህችን ሴት ልሆን አልችልም። በሱስ ምክንያት በተደጋጋሚ አማኑኤል ሆስፒታል እንደነበረ ነገረኝ። በዛ ምክንያትም ስልክ ኖሮት ስለማያውቅ ላገኘሁ እንዳልቻልኩ አብራራልኝ……
“እማ አንቺ ማለት የምትበር ቢራቢሮ ነበርሽ…… ነፃ የሆንሽ… ነፃነትሽን የምትወጂ… ካልሞከርሽ የማታረጋግጪ…… ሁሉን ሞከርሽ እኔን ጨምሮ ሁሉን ተውሽ! ሁሉን አስሞከርኩሽ ከሁሉ ተጋባሁኝና ቀረሁ። ” አለኝ።
አይ አይሆንም የአዳም አንዷ ገፀባህሪማ ሆኛለሁ።…… ነፃነት? ሌላውን የገደለ ነፃነት? በሌላው ባርነት ላይ የቆመ ነፃነት? የአባን ገፅ ያከሰለ ነፃነት?
……… አይሆንም ውሸት ነው። እኔማ እውን አይደለሁም…
(በነገራችሁ ላይ .. ይሄን ፅሁፍ ወደ ድራማ ቀይረነው ነበር:: ብዙ ሰው ወዶታል … ብታዩትና የተሰማችሁን ብትገልፁ በደስተኛ ነው የምወዳችሁ…ሊንኩ 👇🏼👇🏼👇🏼👇🏼)