Tidarfelagi.com

“አይ ምፅዋ”

በዕለቱ (የካቲት 9/1982) የ6ኛው ነበልባል ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ የነበሩት ብ/ጀኔራል ተሾመ ተሰማ ከጠዋቱ 1፡30 ላይ በምፅዋ ከተማ ርዕሰ ምድርዕ በተባለ አካባቢ የተወሰኑ የጦር መኮንኖችንና ባለሌላ ማዕረግተኞችን ሰብስበው ንግግር አደረጉ።
ንግግራቸውም …
“እኔ የሚፈለግብኝን አደራ ተወጥቻለሁ። ከጥር 30 ቀን 1982 ዓ.ም እስከ ዛሬ የካቲት 9 ቀን 1982 ዓ.ም የሞት ሽረት ትግል አድርጌያለሁ። የሻዕቢያን የጥፋት ዓላማ ለመግታት ያላደረኩት ጥረት የለም። ከዚህ በኋላ ግን የራስን ሕይወት በክብር ከማጥፋትና ለኢትዮጵያ ጀግኖችና ታሪክ ጸሃፊዎች ታላቅ ተምሳሌት ከመሆን ሌላ አማራጭ የለኝም።”

አፄ ቴዎድሮስ በእንግሊዞች እጅ ወድቀው ከመዋረድ ሞትን መርጠው የራሳቸውን ህይወት መቅደላ ላይ አጠፉ። እኔ ደግሞ በተራዬ ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት የተሰጠኝን የጄኔራልነት ማዕረግ ሳላስደፍር ለመንግስትና ሕዝብ በገባሁት ቃል ኪዳን መሰረት አቅሜ የፈቀደውን ያህል ተዋግቼና አዋግቼ ሻዕቢያን አራግፌያለሁ።

ጎበዝ ስሙኝ ይህ የአደራ መልዕክቴ ነገ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይደርስ ይሆናል። ምናልባት አምላክ ካለ ከእናንተ አንዱ መልዕክቴን ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ያደርስ ይሆናል። ዛሬ ሻዕቢያ ምፅዋን ተቆጣጥሬያለሁ በማለት የዓለምን መገናኛ ብዙኃን እንደሚያጨናንቅ ጥርጥር የለውም። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ሀገሬና ለሕዝቧ ትልቅ አደጋ ነው።

በቀይ ባሕር በራችን በኩል ብዙውን ጊዜ ወረራ ፈጽመውብናል። በተደጋጋሚ ያሳፈርናቸውና ፊት ለፊት ያልቻሉን ምዕራባውያን ሀገሮችና አረቦች ዛሬ የሻዕቢያን ጊዜያዊ ድል ሰምተው ይፈነጥዛሉ። ምናልባትም የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ድንበር የሆነውንና ለዘመናት በአባቶቻችን የደም ዋጋ ፀንቶ የቆየውን የባህር በራችንን ለመዝጋት እንዲሁም ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ባሕር አይደለም በማለት በምድር ተወስነን እንድንቆይ ይደረግ ይሆናል። ይህ ደግሞ የሞት ሞት ነው።

ይሁን እንጂ ምንም ማድረግ አልችልም። ሁሉም ነገር ከቁጥጥሬ ውጪ ሆኗል። ከሙታን አለም መጥቼ ማረጋገጥ ባልችልም የፈለገ ጊዜ ይጠይቅ እንጂ ጀግናው የኢትዮጵያ ሕዝብ የባህር በር አልባ ሆና እጁን አጣጥፎ አይቀመጥም። ይህ ከሆነማ የአፄ ዮሐንስ የቀይ ባህር ተጋድሎ እና የጀግናው ራስ አሉላ አባነጋ እንዲሁም የኔን ጨምሮ የአብዮታዊ ሠራዊት አባላት ደምና አጥንት የኢትዮጵያን ትውልድ ሁሉ እስከ ዘለዓለሙ ይፋረዳል።
ኢትዮጵያ ሀገሬ የጀግኖች መፍለቂያና ገናና ታሪክ ያላት ሀገር ናት። በመሆኑም ጀግናው ሕዝቧ ሕዝባዊ የባህር በሩ በሻዕቢያ ተይዞና የጠላቶቹ መፈንጫ ሆኖ አይቀርም። የፈለገ ጊዜ ይቆይ እንጂ ሻዕቢያ ምፅዋን እንደያዛት ለዘለዓለም አይኖርም ጊዜውን ጠብቆ የኢትዮጵያ ጀግና ጠላቱን ደምስሶ ምፅዋን ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚያስረክብ እምነቴ የጸና ነው!›› አሉና ትንሽ ፋታ ወሰዱ።

‹‹ስሙኝ አንድ ምሳሌ ልንገራችሁ›› አሉ ብ/ጀኔራል ተሾመ ቆጣ ብለው።
‹‹አንድ ሰው ቤት ሲሰራ የሚሰራው ቤት በርና መስኮት አሉት። አንድ ሰው ደግሞ ሞተ እንበል፡ መቃብሩ በርና መስኮት የለውም። በርና መስኮት የሕይወት ምልክቶች ናቸው። በመሆኑም ያለ ሀገር ነጻነትና ያለ ባሕር በር ብልጽግና ስለሌለ የኢትዮጵያ ሕዝብ የባሕር በር ተነጥቆ የሚኖር ሕዝብ አይደለም። ከሻዕቢያ ጀርባ ሆነው ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ አይደለም የሚሉ ሀገሮችና ጋሻጃግሬዎቻቸው ሁሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ፍላጎታቸው የኢትዮጵያ ሞት ነው።

ይህ ዕድል ለኢትዮጵያ እንዳይደርሳት ቀይ ባሕርን የኢትዮጵያ ትውልድ ይፋረድ።
ቻው! ቻው!!›› 😥
ምፅዋ

One Comment

  • yonasbirhanu@17gmail.com'
    yonas birhanu commented on November 9, 2021 Reply

    ዋው፡ ውቢት ጎርፉ፡ ምርጥ ትውስታ ነው፡፡ በርቺልን፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...