‹‹ ቆመሽ ቀረሽ እኮ…ቁጭ በይ እንጂ!›› አለኝ ወደ ትልቁ የቆዳ ሶፋ እያመለከተኝ። ለወትሮው ሶስት ወፍራም ሰው አዝናንቶ እንደሚያስቀምጥ የማውቀውን ሶፋ በሰጉ አይኖቼ ስገመግመው የአራስ ልጅ አልጋ ሆኖ ታየኝ።
መቀመጤን በመጠኑም ቢሆን ለማዘግየት ጮህ አልኩና፣
‹‹ስልኬ…ስልኬን ዴስኬ ላይ ትቼ ነው የመጣሁት….ከቤት ደውለው ይሆናል….ስላመሸሁ…እማዬ አስባ ይሆናል…›› አልኩ ክፍቱን ወዳለው በር በጉጉት እያየሁ።
‹‹ሂጂና አምጪዋ!..እኔም እስከዛ ምግቡን አዛለሁ›› ሲለኝ ሰኮንድም ሳላባክን ቢሮውን ትቼ ሄድኩ።
በእፎይታ አንዴ ዴስክና ወንበሬን፣ አንዴ ደግሞ አሁንም ክፍቱን ያለውን የአለቃዬን ቢሮ አፈራርቄ አየሁና ጠረጴዛው ላይ ትቼ የነበረውን ስልኬን አንስቼ ከፈትኩት።
ለሰበብ ልጠቀምበት እንጂ እውነትም እማዬ ሶስት ጊዜ ደውላ አጥታኛለች።
ስለመሸ እንዳስጨነቅኳት፣ እንደምዘገይ እንዳልነገርኳት ትዝ ሲለኝ በጥፋተኝነት ስሜት ቶሎ መልሼ ከመደወሌ እና እንዴት ዋልሽ እማ ከማለቴ
‹‹ምን ነካሽ ልጄ? ይሄው ሰው ቁጭ አድርገን ስንጠብቅሽ ዘመን የለንም…ብደውል ብደውል አታነሺም። ምን ሆነሽ ነው?›› ብላ በቁጣም በጭንቀትም ተናገረችኝ።
አሳጥሬ በስራ መወጠሬን እና ሳላውቀው እንደመሸብኝ ነገርኳትና ቁጭ ብሎ የሚጠብቀኝ ሰው ማን እንደሆነ እግረመንገዴን ስጠይቃት ድምፅዋ ባንድ ጊዜ በኩራት ተሞልቶ፤
‹‹ገርዬ ዛሬ ይመጣል ብዬሽ ነበር እኮ…አሁንማ አስኮ ድረስ መስትዬ ጋር ሄዶ ከሚያድር እዚሁ ቢያድር አንቺንም ቢያገኝሽ ይሻላል ብለን አሳደርነው…ቶሎ ነይ ቡና ሊፈላ ነው…›› አለችኝ።
ገርዬ- ጋሽ ገረመው -ናዝሬት የሚኖረው-ከ ሁሉ አስበልጬ የምወደው-ከልጅነቴ ጀምሮ ለክረምት ለክረምት ናዝሬት ቤቱ እየሄድኩ የምከርመው- የእናቴ ወንድም ተወዳጅ አጎቴ ነው።
‹‹የክረምት አባቴ›› እለው ነበር ነፍስ ካወቅኩ ጀምሮ።
በህፃንነቴ አሻንጉሊት ፣ ከዩኒቨርስቲ የተመረቅኩ እለት ደግሞ የወርቅ ሃብል- በሁለቱ መካከል ደግሞ ተቆጥረው የማያልቁ መጫዎቻዎች፣ እልፍ አእላፍ ሚሪንዳዎች- መአት ኮካኮላዎች፣ የማይቆጠሩ ኬኮች፣ ብዙ መፅሃፎች እየገዛ-ሳይደለው ያሞላቀቀኝ አብዝቼ የምወደው አጎቴ ነው።
‹‹ገርዬ መጣ? መች ይመጣል አልሽኝ…አላልሽኝም እኮ እማ…›› አልኳት በርግጠኝነት። ስለማየው ደስ በሎኛል።
‹‹ሰሞኑን ምን ቀልብ አለሽ አንቺ…አንቺ አልሰማሽ ይሆናል እንጂ መንገሩንስ ነግሬሻለሁ…›› አለችኝ እማ።
ገርዬን ከማየት ጉጉቴ እኩል ይሄንን አሰቃቂ ሁኔታ ማምለጫ ስላገኘሁ ተደሰተኩ።
እማን መጣሁ ብያት ስልኩን ዘግቼ ለአቶ ብሩክ የምናገረውን ማሰላሰል ጀመርኩ።
ሶሰት አይነት አረፍተ ነገሮች ተለማመድኩ
1ኛ- ‹‹ አቶ ብሩክ ይቅርታ….ክፍለሃገር ያለው አጎቴ መጥቷል…መሄድ አለብኝ››
2ኛ- ‹‹(ውይ) አቶ ብሩክ( በጣም )ይቅርታ…(ሩቅ ) ክፍለሃገር ያለው አጎቴ (ታሞ) መጥቷል አሉ…መሄድ አለብኝ…››
3ኛ- ‹(‹ውይ) አቶ ብሩክ በጣም (በጣም) ይቅርታ….(ጠፍቶ የከረመ) ሩቅ ክፍለሃገር (ይኖር የነበረ በጣም የምወደው )አጎቴ (ድንገት) በጠና ታሞ መጥቷል አሉኝ…መሄድ አለብኝ›..››
ስልኬን እንደያዝኩ ወደ አለቃዬ ቢሮ ተመለስኩና በሩን ደገፍ ብዬ እንደቆምኩ- ፊቴን 3ኛውን አረፍተነገር (ውሸት) እንዲመስል ካደረግኩ በኋላ እንዴም ሳልደናቀፍ፤
‹‹ውይ አቶ ብሩክ በጣም በጣም ይቅርታ….ጠፍቶ የከረመ ሩቅ ክፍለሃገር ይኖር የነበረ በጣም የምወደው አጎቴ ድንገት በጠና ታሞ መጥቷል አሉኝ…መሄድ አለብኝ›..›› አልኩት።
ይሄን ስለው ሶፋው ላይ ተዝናንቶ ተቀምጦ ከነበረበት ብድግ አለና አጠገቤ መጥቶ ቆሞ በውሸት የተረበሸ ፊቴን ትኩር ብሎ እያየ ይጠጋኝ ጀመር።
ምቾት በማይሰጥ ሁኔታ ተጠጋኝ።
‹ኦህ…አይ አምሶ ሶሪ…ምን ነካው አሉ?›› አለና በቀኝ እጁ ጣቶች ጉንጮቼን እንደ መዳበስ በግራ እጁ ደግሞ ወገቤን እንደመጨበጥ ሲያደርገው ደንበር ብዬ ወደ ኋላ ሄድኩና፤
አፌ እንዳመጣልኝ ፤ ‹‹እ…ኩላሊቱ ፌል አርጎ ነው አሉ…›› አልኩኝ መሬት መሬት እያየሁ።
ገሬ እና እግዜር ይቅር ይበሉኝ።
‹‹ኦህ ዛትኢዝ ቱ ባድ…በቃ ሂጂ…›› አለ ድጋሚ ሳይጠጋኝ- ቅር እንዳለው በግልፅ እያስታወቀ።
ልሸኝሽ ብሎ ስላልነዘነዘኝ ደስ እያለኝ ኮተቴን ሰብስቤ ራይድ ጠራሁና ቶሎ ቤቴ ገባሁ።
ጠበብ ያለችው ሳሎናችን በእጣን እና በቡና ጠረን ታውዳ፣ አባዬ፣ እማዬ፣ ታናሽ ወንድሜ ኪሩቤልና አጎቴ ገሬ ሞልተዋት ሲፈነድቁ ጠበቀችኝ።
ፍልቅልቁን ገርዬን እየሳምኩት ለዋሸሁት ውሸት የንስሃ ፀሎት ቢጤ አጉረመረምኩ።
እቃዬን መኝታ ክፍሌ አስገብቼ ልምጣ ብያቸው ወደ ጠባቧ ክፍሌ ገብቼ አልጋዬ ላይ ወደቅኩባት።
ያሳለፍኩት በእንግዳ ትእይንቶች የተሞላ ምሽት በአእምሮዬ ከለስኩት።
በተለይ የመጨረሻ ሁኔታው- ጉንጬን አደባበሱ-ወገቤነ ለቀም አደራረጉ ምንም አሻሚ ነገር አልነበረውም።
ሰውነቴ እንዳዲስ በፍርሃት ተወረረ።
እነዚያን ሁሉ ደቂቃዎች ቢሮው ስቆይ በማይነገር ሁኔታው ነፍሴን ቢያስጨንቃትም በጉልበት ጠፍንጎ አልያዘኝም።
ብሩክ እንዳልሄድ አላስገደደኝም። ግን ሁለንተናው-ሁኔታው የሆነ- አስሮ የመያዝ ስልጣን እና ስሜት ነበረው።
ስልኬ ጋር ባልሄድ-ስለገርዬ ባልዋሽ-መሄድ አለብኝ ባልልና እዚያ ሶፋ ላይ አብሬው ብቀመጥ በቆምንበት ወገቤን የያዙ እጆቹ በተቀመጥንበት መቀመጫዬን ለመንካት አይንደረደሩም ነበር?
ሊጎረሱኝ የጓጉ ክንፈሮቹ፣ እነዚያ ቁሌታም አይኖቹ ‹‹ሂጂ ›› የሚል አፉን ትእዛዝ ተቀብለው ይተዉኝ ነበር?
እሺ ብዬ ብቀመጥ ነገሮች በዚህ ያበቁ ነበር?
ምንድነው የተፈጠረው?
ምንስ ነው የማደርገው?
አጎቴን ትቼ ስለዚህ መብሰልሰልን አልፈለግኩም።
እያደገ የሄደ ፈርሃትና መሸበሬን በዝምድና ጨዋታ- በዋዛ ፈዛዛ ለመርሳት ሳሎን ተመልሼ ሄጄ ከጨዋታው ከመቀላቀሌ እማዬ ፈጠን ብላ፤
‹‹ለገርዬ እኮ ገና ስትገቢ አለቃ እንዳረጉሽ እየነገርኩት ነበር…እስቲ ስለእሱ በደንብ አጫውቺው…›› አለችኝ አይን አይኔን እያየች።
ገሬ፣ አባዬ፣ ወንድሜና ቡናውን የምታፈላው ሰራተኛችን ዋልታነሽ ሳትቀር በአንዴ-በጉጉት ይመለከቱኝ ጀመር።
‹‹እንዴ እማ…አረ እኔ አለቃ አይደለሁም….ዝም በላት ገርዬ….ገና ጀማሪ ባለሙያ ነኝ እኮ..›› አልኩ መሳቅ እየቃጣኝ።
‹‹ዝም በላት…ደሞዟ- ስራዋ እኮ የአለቃ ነው….›› አለች እማ ያልኩትን እንዳልሰማች ሁሉ።
ገሬ ፈገግ ብሎ ነይ ወደ ኔ በሚል በጣቱ ጠራኝና አጠገቡ ሄጄ ስቀመጥ
‹‹ድሮም እኮራባት ነበር…ኤን ጂኦ ገብታ እንደምታንቀባርረን አውቅ ነበር…አለቃ ባትሆን ነው የሚደንቀኝ›› አለ እንደልጅነቴ ጠጉሬን እየደባበሰ።
‹‹አለቃ አይደለሁም ዝም ብላ ነው…›› አልኩት ሳቅ ብዬ።
‹አሁን ባትሆኚም በቅርብ ትሆኛለሽ…እኔማ ለእናትሽ እየነገርኳት ነበር…የኔን ብሌናም አንድ ቦታ ፈልገሽ እንደምታስገቢልኝ…አይደል እንዴ የኔ ቡቱቶ?›› አለኝ በፍቅር እያየኝ።
ቡቱቶ ከልጅነቴ ጀምሮ ያወጣልኝ ስሜ ነው።
ብሌን ደግሞ ዘንድሮ የምትመረቀው ብቸኛ ልጁ ናት።
‹‹ወይ ገርዬ እኔ…›› አልኩ ያሳለፍኩትን ቀን ከወደፊት እጣ ፈንታዬ- ከዚያ ደግሞ እሱና ቤቱን የሞላው ሰው ከሚጠብቅብኝ ሁሉ እያነፃፀርኩ።
‹‹ታገኝላታለች አትስጋ…..በሁለት ወር ትልቅ ቦታ ነው የሰጡዋት አልኩህ እኮ….ብሌና ስትመረቅማ ቀጣሪና አባራሪዋ ዋናዋ ምትሆነው እሷ ናት…ትረዳታለች›› አለች እማ በፍፁም እርግጠኝነት።
እማ ግን ምን መሆኗ ነው?
ያልበላሁት ሊጣላኝ ሲል አባዬ እግዜር ይስጠውና፤
‹‹ተይ አንቺ…ገና መግባቷ ነው…አታስጨንቋት›› አለ።
እራት በጭንቀት በልቼ ከገርዬ ጋር የላይ የታቹን ካወራን በኋላ ‹‹ትልቅ ስራ አለባት ትተኛ›› ተብዬ ወደ አልጋዬ ሄድኩ።
ነገ ስሄድ ምንድነው የማደርገው?
ምንም እንዳልተፈጠረ መሆን?
‹‹ሁለተኛ አትንካኝ›› ብዬ ቡራከረዩ ማለት?
ተከራክሮ ያስቀጠርኝ እሱ ቢሆንም ኤች አር ሄጄ እከስሃለሁ ማለት?
የደሞዜ ባለ በጀት እሱ ቢሆንም- በኤን ጂኦ ባህል ባሻህ ሰአት ተነስቶ ለዚህ ፖዚሽን የሚሆን በጀት የለኝም ብሎ የስራ ሕይወቴን በአንዲት ወረቀት ላይ ማሰረዝ የሚችል ቢሆንም- የሶስት ወር የማስጠንቀቂያ ጊዜዋን በአጥጋቢ ሁኔታ አልጨረሰችም ብሎ ልታሰናብተኝ የሚችልበት ስልጣን ላይ ጉብ ያለ ቢሆንም አላግባብ ነክቶኛል ብዬ መክሰስ ? ከተራራ ጋር መጋፋት?….
ማለቴ….በዚህች መከረኛ ሃገር …በመከራ የተገኘ ስራ- ያውም ይሄን የመሰለ ስራ- አለቃዬ ፈለገኝ…ነካካኝ ተብሎ ይለቀቃል?
በዚህ ሰበብ በሶስት ወር ውስጥ ይሄንን ወርቅ የሆነ ስራ ብለቅ መሞላቀቅ ይሆናል? አለ አይደል ለአንድ አይረቤ የመንግስት ስራ ሁለት ሺህ ሰው ሲቪ በሚያስገባበት…ከፒያሳ እስከ አራት ኪሎ በሚሰለፍበት ሃገር በዚህ ሰበብ ምርጥ የኤንጂኦ ስራ መልቀቅ በእድል መጫወት…የእግዜርን አይን መውጋት ይሆናል?
ላገኘችው ሰው ልጄ ኤንጂኦ አለቃ ሆነች የምትለውን እናቴን ቅስ መስበር አይሆንም?
ከአባቴ ጠባብ ኪስ ገንዘብ ወደ መሻማት መመለስ ሃጥያት አይደለም?
ተስፋ የጣሉብኝ፥ የኮሩብኝ ዘመድና ጓደኞቼን ማሳፈር- የቀኑብኝ ሰዎች ማሽሟጠጫ መሆን አይደለም? ‹‹ውይ…ገና የሶስት ወር ደሞዝ ሳትበላ ለመባረር ነው ያ ሁሉ ያዙኝ ልቀቁኝ?›› ሲሉኝ ታየኝ።
በዛ ላይ ደግሞ….ሰውየው ጎበዝ ነሽ አለኝ እንጂ አልሰደበኝ-
ቀስ ብሎ-ድንበሬን አልፎ ነካካኝ እንጂ አላስፈራራኝ-
በፍቅር አቀፈኝ..ደባበሰኝ እንጂ አስገድድ አልደፈረኝ…
ካልተኛሁሽ አባርርሻለሁ ብሎ አላለኝ….
ምን አጠፋ?
ምን ቅብጥ አድርጎ ቶሎ አስለቀቀኝ?
ወይስ ዛሬ ያየሁት የመጪውን አመላካች ነው?
አስቀጥሬሻለሁ እና ተኚኝ
ለካክፌሻለሁና አስጨርሺኝ ቢለኝስ? የዛሬ ማባበሉ ወደ ነገር ማስገደድ ቢቀየርስ? ይሄንን የማስቆም መብት የለኝም? ብከራከር አላሸንፍም?
ሁለንተናዬ ሲሸራረፍ አድሮ፣ እንቅልፍን ሳላየው ሌሊቱ ነግቶ ወደ ቢሮ ለመሄድ ተዘጋጀሁና ቁርስ ተሰየምን።
ገርዬ የብሌንን ነገር አደራ ሲለኝ- የትራንሰፖርት ያለው ኢንተርንሺፕም ቢሆን አታጪም እያለ ሲያስጨንቀኝ-
እማዬ ያስገባችኝን የአመት እቁብ አንደኛ -በዚህ ወር -በልቼ እንደተመኘችው አሮጌ ሶፋችንን ስለመቀየሬ ደጋግማ ስታወራ-
እኔ ደግሞ አዲሱ ሶፋ ላይ ቁጭ ብዬ ከእኔ ደሞዝ ወዲህ የተራቀቀውን ምርጥ ቁርስ በልቼና የአስቤዛ ገንዘብ ሰጥቻት ስወጣ ልቤ ደንድኖ- ሃሳቤ ተወስኖ ነበር።
ሁሉ ነገር አይሳካም።
ፐርፌክት ብሎ ነገር የለም።
የሚቻለውን ችዬ፣ የሚደረገውን አድርጌ መቆየት አለብኝ። ሚ ቱ ምናምን ለሆሊውድ እንጂ ለአንዲት ደሃ አገር አይሰራም። እኔ ሚቱ ብል አዳሜ ጭጭ ቢል ተጎጂዋ እኔ አይደለሁም? አዳሜ የምትፈልገውን ለማግኘት ለማንም የሚፈልገውን እየሰጠች ፌስቡክ ላይ ሚቱ ስላለች እኔ ከስራዬ ለመልቀቅ ጀብደኛ መሆን አለብኝ? ቤተሰቤን ማሳዘን- ልባቸውን መስበር አለብኝ?
ውሳኔ ላይ ደርሼ…
ስራ ከጀመርኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ልቤን ክፉኛ እየከበደኝ ወደ ቢሮ አቀናሁ።
ቢሮ ከመግባቴ አቶ ብሩክ አስጠርቶኝ – ቅልስልስ እያለ- በሩን ከኋላዬ ዘግቼ እንድቀመጥ ሲጠይቀኝ ግን እንቁላልና ጨጨብሳዬ በአፌ ቱር ብላ ልትወጣ ነበር። ቁርሴ ሊጣላኝ ነበር። ከቁርሴ ጋር ስታገል አቶ ብሩክ ምን ብሎ ጀመረ?
‹‹አጎትሽ እንዴት ሆነ የኔ ቆንጆ?››
(አበቃ)