አንድ ፋሲካ እነ ወሰን የለሽ ቤት ተልኬ መልዕክቴን ካደረስኩ በሁዋላ እንድቀመጥ ተነገረኝና ከዋናው በር ጎን ያጋጠመኝን የጉሬዛ አጎዛ የለበሰ የሳጠራ ወንበር ላይ ኮሰስ ብዬ ቁጭ አልኩ። (መንኩዋሰሴ ለራሴ ይታወቀኛል) ብዙም ሳይቆይ እንዲህ ሆነ ………………
ነጭ የላስቲክ ሳህን ፊት ለፊቴ ተቀምጧል… ከትሪው ላይ ከሳህኑ ጎን ጠይም ድፍን ዝቡቅቡቅ እንጀራ እንደ ቱባ ተጠቅልሎ ተጋድሞአል። የወሰን እናት ከጓዳ ባለ አበባ ጎድጓዳ ሳህን ይዘው መጡና ለወሰን አቀበሉዋት። … ጎድጉዋዳው ሰሀን በአበባ ስዕል ባሸበረቀ እፊያ ተከድኖአል። በእፊያውና በሳህኑ ከንፈሮች መሀል ብር መሰለ የሚያበራ ጭልፋ ወደ አየር ውስጥ ተዘርግቷል። ወሰን እፍያውን ስትከፍተው ዐይኖቼን ወደ ጎድጓዳው ሳህን ሆድ ዕቃ ወረወርኩ። ታላቅ ቀይ ወጥ አየሁ። ንጉሠነገሥት ኃይለሥላሴ፣ ደጃዝማች ክፍሎም፣ አፈንጉሥ ዘለቀ፣ አባ ጆቢር፣ አባ ጅፋር የሚባሉት የሚበሉት ዐይነት ቀይ ወጥ። የተጌጠ ጠይም ደም ይመስላል። በቅባት የሰከረ። ከዚህም ሰካራም ወጥ ደካማ ጢስ ቀስ እያለ ወደ ላይ ይነሳል (ምን አድርጌው ነው እንዲህ በቀስታ የሚነሳው? ልቤን ሊሰልበው ነበርን?)።
ከዚያ በጭልፋው ተረበሸ። እና ውፍረቱ። ወሰን መሰል፣ መሰል…መሰልሰል አደረገችው፣ በቀስታ ከውስጡ የአልማዝ ቀለበት ለማውጣት እንደምትፈልግ። ከዚያ በጭልፋው እፍኝ ያህል አውጥታ ነጩ ሰሀን መሀል ‘ጣል’ አደረገችው። የሚፈስ አይመስልም። እና ጣል። መረቁ ከደቀቀው ሥጋ ጋር በማር የተያያዘ ይመስል ነበር። የነጩ ሰሀንና የወጡ ቀለም ግጭት ከላይ እስከ ታች በጠበጠኝ። ከዚያ በጠረኑ፣ በዚያ የተስፋ ጣዕሙ ምክንያት ከጉሮሮዬ እስከ እምብርቴ ስር ቀላል ነጎድጓድ ሰማሁ። ቶሎ እንድትሄድልኝ ፈለግሁ። የመኩራሪያ ጊዜ አልነበረኝም። በሆድ ነገር ኮርቼ አላውቅም። ወሰን ስቃዬ ስላልገባት፣ እኔንም ለማስደሰት፣ ሁለተኛ ጊዜ ከወጡ ጨልፋ ሰሀኑ ላይ አደረገች። “ብላ እንጂ” አለች። ረሳሁዋት። ጠቅላላ ገላዬ ዐይን እጅ አፍ ሆድ ሆነ…ከዚያ ከጠይሙ እንጀራ ስቀድ… በመቅደዴና ወጡ ውስጥ በመንከሬ መሀል ያለው ጊዜ የሶማ በረሀን እንደማቋረጥ ያለ ሥቃይ… በሚንቀጠቀጡ ጣቶቼ ከደቀቀው ሥጋ በእንጀራው አፍኜ ዘገንኩ። የወጡ ለዘዝ ያለ ሙቀት (በምን ለኩት እቴ። አንዳንድዋ ሴት የማትሠራው ታብ የለ) ጣቶቼ ጥፍር ውስጥ ሁሉ ይሰማኛል። ስጎርሰው እጅግ በፍጥነት ነበር…ሮጦ ወይም በሮ እንደሚያመልጠኝ። አፍ ውስጥ ደሞ ይለሰልሳል። ትናንሾቹ የስጋ ጥንጎች ጥርሶቼ መሐል ሲፈነዱ መጠው የያዙትን ቅባትና የበሰለ ውሀ ወደ ጉሮሮዬ ሲደፉ…
እመቤቴ ማርያም ሆይ በመላኩ በቅዱስ ገብርኤል ሠላምታ ሠላም እልሻለሁ…ሠከርኩ።
ግራጫ ቃጭሎች፤ ገጽ 84 – 85