“አጥር መስራት የውሻ ተግባር ነው” ~ የገዳ ስርዓት
—
እንደ ማሕበረሰብ አንቀላፍተናል… ጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ ነን… ለሞት የቀረበ እንቅልፍ… ችግሩ ማንቀላፋታችንን አናውቅም… ማንቀላፋታችንን ስላላወቅን የተኛንበትንም አናውቅም… ማንቀላፋታችን ደግሞ በሌባ አስደፍሮናል… ችግሩ መሰረቃችንን አናውቅም… ወይም ግድ የለንም… የተዘረፍነው ግን አማናዊነት ነው… እውነተኛውን ማንነት!!… ስንነቃ እንደምን እንደነግጥ ይሆን?…
—
“Race is a lazy byproduct of not knowing your true self” ― Shaun S. Lott
___
የሰውን ልጅ እጅግ ከሚያሳንሱ ነገሮች ዋነኛው ምናልባትም ትልቁ ጎሰኝነት ይመስለኛል… ጎሰኝነት ከሁዳድ ጋርዮሽ የመዳፍ ቁርስራሽ የሚያስመርጥ እብደት ነው… የሰው ልጅ የሁዳድ ጋርዮሽ Space ሲሆን የመዳፍ ቁርስራሹ ደግሞ መንደርተኝነቱን የሚታቀፍበት ጎሳዊ ቅርጫት ነው… ስፔስ ላይ ቅርጫትን አኑሮ ማሰብ ጣና ሃይቅ ላይ አንዲት የጤፍ ፍሬ አስቀምጦ ከማሰብም በላይ ከባድ ነው…
___
ስለ [Multi verses] የሚያትተው የ Parallel universe ቲዎሪ እስከዛሬ ከምናውቀው በላይ ሌሎች ብዙ ቨርሶች ስፔስ ላይ እንዳሉ ሲያትት የ’ዓለም ዘጠኝ ናት’ ተረት ፉርሽ እንደሆነ ብቻ ሳይሆን ሺህ ምንተሺህ ፕላኔቶች ሕዋውን እንደሞሉም አስረጅ ነው… ከዚህ አንፃር የኛይቱ ምድር ስላለንባት ግዙፍ ትምሰል እንጂ ከሌሎቹ እልፍ አዕላፍ ፕላኔቶች ጋር ስትተያይ እዚህ ግባ የሚባል መጠን ልኬት የላትም…
___
የሰው ልጅ ግን ከምድርም፣ ከቨርሶችም ከራሱ ከስፔስም ይልቃል፤ በፈራሽ በስባሽ ሥጋ የማይመተር፣ በጊዜና ቦታ የማይሰፈር ታላቅ ማንነት ባለቤት ነውና… ይህን ጽሩይ ማንነት ግን ሁሉ አይረዳውም ሁሉ አይገነዘበውም፤ አብዛኛው በጠፊ ጥላው ላይ ተመስጧልና…
___
“You are here to enable the divine purpose of the Universe to unfold. That is how important you are!” ~ Eckhart Tolle
___
እውነታው የስብዕናችን ግዝፈት ልክ አልባነቱን አመልካች ቢሆንም በመንደርተኝነት መጨፈናችን ልክና ገደብ ከሌለው ሕዋ አንፃር የድቃቂ አቧራን ያህል ዓይን የማትቆረቁረውን ምድርን ወደ ሌሎች ብናኞች የመከፋፈል ክፋት ውስጥ ዶሎናል… ችግሩ በዚህ ቢቆም መልካም ነበር፤ ቅንስናሹ ውስጥ ‘ሌሎች’ እንዲኖሩ የምንፈቅድበት መስፈሪያ ደግሞ አለን… የኔ ወገን፣ የኔ ዘር፣ የኔ ምንትስ… ወዘተ የሚያስብል ህመም…
___
እርግጥ የቋንቋ መኖር እውነት ነው… የጎሳ መኖር ግን ቅዠት ነው፤ በምንም አታረጋግጠውም… ታዲያ እንዴት እኛና ሌሎች ለማለት የምንጠቀመው?… አማራ፣ ኦሮሞ ወይም ሲዳማነት በላብራቶሪ ውስጥ የሚረጋገጥ ነገር የለውም… ደምህ [A፣ B ፣ AB እና O] የሚል የወል ስም እንጂ ጉራጌ፣ ጋሞ፣ ትግሬ፣ አልያም ወላይታ የሚያሰኝ ንጥረ ነገር የለውም… ‘እኔ ምንትስ ነኝ፣ እከሌ እንዲያ ነው’ ስትል ቋንቋን፣ በአንድ አካባቢ መገኘትንና ትውስታን መሰረት ከማድረግህ ውጪ ምን ተጨባጭ ማስረጃ አለህ?…
___
የፍልስፍና ፕሮፌሰሩ David Livingstone Smith, “Less Than Human: Why We Demean, Enslave, and Exterminate Others” በተሰኘ ተሸላሚ መጽሐፉ ስለ ዘረኝነት ሲጽፍ “The folk notion of race is very much an artificial construction.” ብሏል…
—
እንግዲህ ቋንቋ እውቀት ነው – ማንም ይማረዋል… አንድ አካባቢ መገኘትም አጋጣሚ ነው – ማን አውቆ ይመርጠዋል?… የቆዳ ቀለም ለየአህጉሩ የተሰጠ የአየር ሁኔታ ግልባጭ ነው – በቆዳው ውስጥ ያለውን የ melanin መጠን ማን መወሰን ይችላል?… እስኪ ንገረኝ – ‘ነኝ’ የምትለውን ነገድ የሆንከው በምንህ ነው?… ራስህን ከኔ የነጠልከው ምን ይዘህ ነው?… ልዩ ልዩ ቋንቋና ባሕል ፈጥረን ውበት ከመጨመራችን ውጭ በሰውነታችን መሃል ‘ልዩነትን’ የሚያሳይ ምን ነገር አለን?… ነገዴ ግንባሬ ላይ ተጽፎ ይሆን እንዴ?…
___
ስለራሴ ልንገርህ…
___
እናትና አባቴ ፯ ቤት የሚባለው ጉራጊኛ ቋንቋ ተናጋሪ ናቸው… ቡታጅራ ሄደው መስቃንኛ ተናጋሪ በሆነው የጉራጌ ማሕበረሰብ መሃል እኔን ወለዱ… ቡታጅራ ሁለት አስርት ዓመት ብኖርም ሁለቱንም ቋንቋዎች በጥቂቱ ከመስማት ውጪ መናገሩን አልችልበትም… ከዚያ ይልቅ አማርኛ እቀለጥፋለሁ… ይህ እንግዲህ ከተማ መሃል በመገኘቴ የሆነ ጉዳይ ነው… ባለፉት ፲፫ ዓመታት በስራና ትምህርት ሰበብ አርባምንጭ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ቦዲቲና አዋሳ አሁን ደግሞ ሸገር እየኖርኩ ነው… በየመሃሉ ከሄድኩባቸው ከተሞች ውስጥ ደግሞ አሶሳ፣ ጅጅጋ፣ ድሬ፣ ሐረር፣ ደሴ፣ መቀሌ፣ ባሌ የሚገኙት (ዶዶላ፣ አሳሳና አዳባ) እንዲሁም አምቦ አይረሱኝም… ነገ የት እንደምገኝ አላውቅም…
___
እስኪ ንገሩኝ በዘመነኛው የጎሳ አስተሳሰብ ውስጥ ራሴን ምን ብዬ ነው መሰየም ያለብኝ?… ‘ወደ ክልልህ’ ብትሉኝ የኔ መውደቂያ የት ነው የሚሆነው?… በእናንተ መስፈሪያ የእትብቴ ማረፊያ ቡታጅራ እኮ ከተማዬ አይደለችም… ኮሌጅ ያስበጠሰችኝ አርባምንጭ፣ የስራ ሀሁ የተማርኩባት ወ/ሶዶ፣ የሰው ፍቅር ያገኘሁባት ቦዲቲ፣ ራሴን ያየሁባት አዋሳ፣ ነፍስ ያላቸው ሰዎችን የሰጠችኝ አዲሳባ የኔ ‘ትክክለኛ’ ቦታዎች አይደሉም… እና የት ልሂድ?…
—
ስነልቡናዬ እንደተገኘሁበት ቦታ ሲቃኝ የቆየ እንደመሆኑ እኔ ውስጥ ሁሉም እንጂ አንዱ ብቻ የለም… ከሳምንት እስከ ወራት የቆየሁባቸው ከተሞች ሳይቀር አሻራቸው እኔ ውስጥ አለ… በአካል ባላያቸውም በንባብ የተመላለስኩባቸው፣ በሬዲዮ ተረክ የሰማሁዋቸው፣ በቴሌቪዥን መስኮት ያስተዋልኳቸው ብዙ ናቸው… በዚህ ዘመን እንኳንና በአንድ ሃገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር ቅሩብነት እውነት ነው… ሶሻል ሚዲያ ላይ ከእልፎች ጋር አብሬ ስውል ሃሳቤን እንጂ ጎሳዬን የጠየቀኝ የለም…
___
ወዳጆቼ… ይህ የመንደርተኝነት ህመም በዚህ ከቀጠለ የእግር መቆሚያ ሁሉ ሊያሳጣን ይችላል… ለአማናዊ ማንነቱ ኢትዮጵያዊ ዜግነት የማይመጥነውን፣ አፍሪካዊነት የማይስተካከለውን፣ ምድር እንኳ የማትፎካከረውን ለብቻው ዩኒቨርስ የሆነን ሰው እንዴት ‘መንደርህን ፈልግ’ ትሉታላችሁ?… “You are here on earth to unearth who on earth you are.” ― Eric Micha’el Leventhal
___
አቦርጂኒስቶች እንዲህ ይላሉ…
“We are all visitors to this time, this place. We are just passing through. Our purpose here is to observe, to learn, to grow, to LOVE … and then we return home.”
___
ወደ እውነተኛው ቤታችን እስክንሄድ ከቀልባችን ሆነን እንጠይቅ እባካችሁ… እንዲህ የምንጋደለው ለየትኛው ዕድሜ ነው?…
___
ፍቅርን ከመስጠት በላይ ዕዳ አይኑርባችሁ!!