አሳዛኝ ታሪክ
ትናንት በራፌ ተቆረቆረ፤ ከፈትኩ፥ ሁለት ያሜሪካ ወታደራዊ መለዮ የለበሱ ሰዎች ቆመዋል ፤ ባለባበሳቸው መገመት እንደቻልኩት አንደኛው ፊልድ ማርሻል ነው፤ ሁለተኛው ፊልድ ሻለቃ ሳይሆን አይቀርም፥
“ሚስተር ቤኪቱ” ብሎ ጠራኝ ማርሻሉ ፥
“አቤት”
“እንኳን ደስ ያለህ ለብሄራዊ ውትድርና አልፈሀል! “ አለና ተጠመጠመብኝ ፥
ከጥምጠማው ራሴን እንደምንም መንጭቄ አላቅቄ፤ “ የቅጥር ደብዳቤ ማስገባቴ ትዝ አይለኝም ጌታየ” አልሁ፥
“ጎረቤትህ ነው ያስገባልህ”
ግር አለኝ፤ ሻለቃው ግርታየን ለማጥራት የሚከተለውን ማብራሪያ አበራልኝ፥
“ መቸም፥ ማረ ፋከ ብላድሚር ፑቲን ዩክሬንን እንደወረረ ሳትሰማ የቀረህ አይመስለኝም፤ ይሄ ትልቅ አገር በትንንሽ አገር ላይ የሚፈጸም ወንጀል ነው፤ የነገሩን ክብደት እንዴት ብየ ላስረዳህ፥ ኢትዮጵያ ጅቡቲን በወረራ ብትይዝ ብለህ አስበው”
ኢትዮጵያ ጅቡቲን በወረራ ስትይዝ አሰበኩትና ምራቄን ዋጥሁ።
ማርሻሉ በበኩሉ፥ በርጩማ ወንበሬ ላይ ቁጭ አለና፥ ያነገተውን ታጣፊ ድሮን ጉልበቱ ላይ አጋድሞ እየወለወለ የሚከተለውን አለ፥
“ አሁን በአሜሪካና በሩስያ መካከል ጦርነት አይቀሬ ሆኗል፤ ለዚህ ከፍተኛ ዝግጅት እያደረግን ነው፤ ሰለዚህ በጦረኝነት ከታወቁ አገሮች የመጡ ስደተኞችን በመመልመል ላይ እንገኛለን፥ አንተም አብደልነስር የተባለው ግብጻዊ ጎረቤትህ ባደረገው ጥቆማ ተመርጠሀል፡”
“ደስ ይለኝ ነበር፤ ግን በቅርቡ ወዳገሬ ልመሰስ ወስኛለሁ”
“ምን አጣደፈህ! ትንሽ ተዋግተህ ትመለሳለህ፤ “ አለኝ ማርሻሉ።
“ብዋጋ እማገኘው ጥቅም ምንድነው ማር?” አልሁት፥ (“ማር” ስል ማርሻሉን ማቆላመጤ ነው )፥
“ተጠቂዎችን መታደግ በታሪክ ያስከብራል፥ በጦርነቱ ከተሰዋህ ሶስት ቦታ ሀውልት ይቆምልሀል፤ ዩክሬን ፤ አዲሳባና ዲሲ ላይ፤ “
“ከቆሰልክ ደግሞ የቴስላ ካምፓኒ የሚያመርተው ዘመናዊ የኤልትሪክ ዊልቸር ከወገብህ በታች ይገጠምልሀል” ተቀበለ ሻለቃው፥
አመነታሁ፤ ” ላስብበት” አልሁና ሽንት ቤት ገባሁ፤ ከሽንት ቤት ስመለስ ወኔየ ተቀሰቀሰ፤ ማመንታቴን ከሽንቴ ጋር ደርቤ የሸናሁት መሰለኝ፥
“በውነቱ ለኔ ትልቅ ክብር ነው ፤ አንድ ቦድካ የነሆለለ ወራሪ ኮዛክ ጥየ ብወድቅ ለኔም ላገሬም ለመላው ሰው ልጅም ክብር ነው”
“ዛትስ ማይ ቦይ! አለኝ ማርሻሉ በደስታ ፈንጥዞ፥
“በምንዘርፍ እንደምዘምት ብታስረዱኝ”
“አየር ወለድነት ይመችሀል? አለኝ ሻለቃ፥
“ከልብወለድ ወደ አይርወለድ ትንሽ አይከብድም? ቀለል ያለ ነገር ፈልጉልኝ እንጂ “
“ብረት -ለበስ ላይ እንዴት ነህ”
“በልኬ የተሰፋ ብረት ከተሰጠኝ አሳምሬ እለብሳለሁ”
ሻለቃው ትንሽ ካሰላሰለ በሁዋላ ፥
“በመድፈኝነት ዘርፍ ትመደባለህ፤ መድፈኛው ሲተኩስ አንተ ጥይት ታቀብላለህ” በማለት ወሰነ፥
“የመድፉ ጥይት ራሱ ከሱ ቁመት ይበልጣል፤ ሊሆን አይችልም” አለ ማርሻሉ፤
ሁለቱ መኮነኖች ትንሽ ተጨቃጨቁ፤
“የደመወዙ ነገር እንዴት ነው ? “ በማለት አቋረጥኳቸው፥
“በወር አስርሺህ ዶላር፥ ከነጥቅማጥቅሙ ፥
“በቃ ጥቅማጥቅሙን ብቻ ስጡኝና ዩክሬን እንና ሩስያን ላደራድራቸው”
በጣም ተናደው፤ በሩን ከፍተው መውጣት ጀመሩ፥
በር ላይ ቆሜ፥
“ቤተሰብ እማስተደድር ሰው ነኝ ! ብዙ ሪስክ የሌለው ሚሽን ስጡኝ” ብየ ጮህኩ”
በራፌ ላያ ያቆሙትን ታንክ አስነስተው ከመሄዳቸው በፊት የሚከተለውን ብያለሁ
“ዲሲ የሚገኘው የሩስያ ኢምባሲ ላይ ድንጋይ የሚወረውር ሰው ከፈለጋችሁ ደውሉልኝ “