Tidarfelagi.com

መከላከያን – ከመንደር ወደ ድንበር

ከላስ ቬጋስ ወደ ቴክሳስ ሳን አንቶኒዮ ልበርር ነው። ላስቬጋስ አውሮፕላን ጣቢያ ወደ አውሮፕላኑ መግቢያ በር አካባቢ ቁጭ ብያለሁ። የመሣፈሪያ ሰዓታችን እየደረሰ ነው። በመካከል የአየር መንገዱ ሠራተኛ ‹ይህንን ሳበሥራችሁ ደስታ ይሰማኛል› የሚል ነገር በማይክራፎኑ ተናገረች። ቀጠለችና ‹ዩኒፎርም የለበሱ የሠራዊቱ አባላት በመካከላችን ናቸው› ስትል እየተፍነከነከች ተናገረች። ሰው ሁሉ ከመቀመጫው ተነሥቶ አጨበጨበ። ጭብጨባው ለሁለት ደቂቃ ያህል ዘለቀ። ወታደሮቹ ወደ በሩ ተጠጉ። ሰባት ናቸው። ‹በክብር ወደ አውሮፕላኑ እንሸኛቸው› አለች ሴትዮዋ። ሁላችንም ቆመን እያጨበጨብን እነርሱ ወደ ውስጥ ገቡ። የቢዝነስ ክፍል፣ የአልማዝና የወርቅ ደንበኞች አልቀደሟቸውም። ከአውሮፕላኑ ስንወርድም ሁላችንም ባለንበት ተቀምጠን እያጨበጨብን እነርሱ ቀድመው ወጡ። ይህንን ሕዝባዊ ከበሬታ ስመለከት ዛሬ በግጭቶች መካከል የተሠማራውን የሀገሬን ሠራዊት አሰብኩት።

በሀገራችን እየተፈጠረ በሚገኘው ሀገራዊ ግጭት የተነሣ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን በየመንደራችን ማየት የተለመደ እየሆነ ነው። በተለመደው አሠራር የሲቪልና የፖሊስ ኃይሎች ሊሠሩት የሚገባውን ሁሉ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ሲያከናውኑት መመልከትም እንግድነቱ አብቅቷል።
ይህ ጉዳይ ግን መከላከያውንም ሕዝቡንም የሚጎዳ ነው።

መከላከያውን በሀገራዊ ግጭቶች መካከል አብዝቶ እንዲነከር ማድረግ አምስት ጉዳቶችን ያመጣል። የመጀመሪያው ሞራላዊ ጣጣ ነው። የተለያዩ ኃይሎች የሚያነሡትን ጥያቄ መመለስ ያለባቸው ለዚሁ የተመረጡትና የተሾሙት አካላት ናቸው። የተነሡት ጥያቄዎች ትክክልም ሆኑ አልሆኑ ነገሩ ሕዝባዊ መልክ ሲይዝ መከላከያው ለማን እየታገልኩ ነው? የሚል የሞራል ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ያደርገዋል። ምንም እንኳን ለሕገ መንግሥቱ የመቆም ዓላማና ግዴታ ቢኖርበትም እርሱም የሕዝቡ አካል ነውና የሕዝቡን የመልካም አስተዳደር፣ የዴሞክራሲ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጥያቄዎች ይሰማል፣ ይከታተላል፣ ይካፈላልም። ዱላውና መሣሪያውም የሚዞረው በሕዝቡ ላይ ነው። በግርግሮች መካከል በሚፈጠሩ ግጭቶች ሕጻናት፣ ወጣቶች፣ አዛውንት ይገደላሉ። የሚሞተው የጣልያን ወይም የደርቡሽ፣ የእንግሊዝ ወይም የዚያድባሬ ጦር አይደለም። የሀገሬው ሰው ነው። ይህ ሁኔታ ነው በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ የሞራል ጥያቄን የሚያጭረው።

ገድሎ ይፎክራል ወይ? የድል ስሜት ይሰማዋል ወይ? ሕዝቡ ጉሮ ወሸባዬ ይዘፍንለታል ወይ? ነገ እንደ ጀብዱ ይተረከዋል ወይ? ድንበር እንደጠበቀ ሀገር እንዳስከበረ ሆኖ ይሰማዋል ወይ? ይህ ነው ጥያቄው።

ሁለተኛው ደግሞ የብሔር ተጽዕኖ ውስጥ የመውደቅ ጣጣ ነው። ሀገሪቱ በብሔር ክልሎቿን ባዋቀረችበት፣ ብሔርተኝነት ጫፍ በደረሰበት በዚህ ዘመን ለክልሉና ለብሔሩ የማይቆረቆር የመከላከያ አባል ማግኘት አዳጋች ነው። የሚሰጠው ሥልጠና ይህንን እንዲከላከል ቢመክረው እንኳን የሚስበው አየር ግን እንዲህ እንዲሆን ያስገድደዋል። አንደኛውን ብሔር እንወክላለን የሚሉ አካላት በሌላኛው ብሔር ላይ የሚያከናውኑትን ነገር ለመግታት በየመንደሩ ሲገባ ሁለት ዕጣ ፈንታ ይገጥመዋል። በአንድ በኩል እርሱ ግፍ እንዳይደርስባቸው የሚከላከልላቸው አካላት ወገን ተደርጎ የመታየትና ለፕሮፓጋንዳው የመመቻቸት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ብሔሩን እንደከዳና በራሱ ብሔር ላይ መሣሪያ እንዳነሣ ተደርጎ የመታየት ዕጣ። በአሁኑ ጊዜ ብሔር የኢትዮጵያውያን የመጨረሻው ምሽግ እየሆነ ነው። ‹ኢትዮጵያዊ በሰላምና በነጻነት የሚኖረው ከብሔሩ ጋር በወገኖቹ ምድር ሲኖር ነው› የሚለው ሐሳብ ጉልበት እየገዛ ነው። ይህ ደግሞ እንደ ሰውና እንደዜጋ የመከላከያ ሠራዊቱን አባላትም ይመለከታል። እነርሱም ከራሳቸው ወገን ጋር እንደተጣሉ አድርገው ካሰቡ፣ ምሽጋቸውን እንዳጡ አድርገው ሊገምቱ ይችላሉ። የነገ ዕጣ ፈንታቸውም ያሳስባቸዋል።

ሦስተኛው ደግሞ የመከበር፣ የመታፈርና የመፈራትን ሞገስ ማጣት ነው። ወታደራዊ ሥነ ሥርዓት፣ ወታደራዊ ሰልፎች፣ አለባበሶች፣ አደረጃጀቶች፣ ማዕረጎችና ከበሬታዎች ለመከላከያው ከሚሰጡት ወታደራዊ ጥቅሞች ባሻገር በማኅበረሰቡ ዘንድ መከበር፣ መታፈርና መፈራትንም ያመጣሉ። በራችንን ጠዋት በከፈትን ቁጥር የመከላከያውን አባል ድንጋይ ላይ ቁጭ ብሎ ካገኘነው፣ በየማኅበራዊ ሚዲያው በገዛ ወገኑ ላይ ፈጸመ የሚባለውንና እርሱም በወገኑ የሚፈጸምበትን ነገር ስናየው፣ በየሠፈሩ ቡና ላይ የሚወራው ስለመከላከያ ሠራዊቱ ገድል፣ ጀብዱ፣ የድል ታሪክና የጦር ሜዳ ውሎ መሆኑ ቀርቶ የእርስ በርስ ግጭቶቹ ታሪክና ውጤት ሲሆን መከበር፣ መታፈርና መፈራት ደብዛቸው ይጠፋል።

ወታደራዊ ሂደት ከሲቪል የሚለይ የራሱ መንገዶች አሉት። በየመንደሩ ወታደሩን ስናስገባው በሲቪላዊ ተግባራት ልምድ እጥረትና በአስተዳደራዊ ዕውቀት ማነስ የተነሣ የሚፈጠሩ ስሕተቶች ይኖራሉ። የተለመዱት መዋቅራዊና ቢሮክራሲያዊ አካሄዶች ሳይጠበቁ ርምጃዎችና ውሳኔዎች ሲሰጡ በሕዝብ ዘንድ ቅሬታዎች ይፈጠራሉ፤ ቅሬታዎቹ ደግሞ በሕዝቡ ላይ ብቻ ሳይሆን በሲቪል መዋቅሩ ውስጥ በሚገኙትም አካላት ላይ ይንጸባረቃሉ። ይህ ደግሞ የሕዝቡንና የሠራዊቱን ግንኙነት በቅሬታ የተሞላ ያደርገዋል።

ከበሬታንና መፈራትን ከሚያመጡት ነገሮች አንደኛው ተገቢውን ርቀት መጠበቅ ነው። በሕዝቡና በመከላከያው መካከል ያለው ተገቢ ርቀት እየተሸረሸረ መጥቶ መንደርተኛ ወደመሆን ሲመጣ በኢትዮጵያውያን ውስጥ ለዘመናት የተገነባው ውትድርናንና ወታደርን ከፍ አድርጎ የማየቱ ሥነ ልቡና ይከሥራል። ትርክቱ ሲቀየር ሥዕሉም ይለወጣል። በተረቶቻችን፣ በአፈ ታሪኮቻችን፣ በአባባሎቻችንና በዘፈኖቻችን ውስጥ የነበረው ቦታ በሌላ እየተቀየረ ሲመጣ የሕዝቡም ኅሊናዊ ሥዕል እየተቀየረ ይመጣል።

ይህ ደግሞ አራተኛውን ኪሣራ ያስከትላል። ትውልዱ ወደ መከላከያ ሠራዊቱ የመግባቱን ፍላጎት ይቀንሰዋል። ወላጆቹና ሠፈሩ፣ አካባቢውና ብሔሩ አያበረታታውም። በዘፈንም በተረትም የሚሰማው ልቡን አያሞቀውም። ጓደኞቹና ወዳጆቹ ውሳኔውን አያደንቁለትም፤ ይህ ደግሞ በዞረ ድምሩ የሚጎዳው ሀገሪቱን ነው። በሀገሪቱ ላይ ጫና ለመፍጠርና ዐቅሟን ለማዳከም ለሚፈልጉ ኃይሎች የፕሮፓጋንዳ ክፍተት ይሰጣል። ሀገሪቱ ለሚደርስባት የውጭ ወረራ ‹ሆ› ብሎ የሚነሣ ደጀን ሕዝብ ያሳጣል።

የመከላከያ ሠራዊቱ ይህንን በመሰለው ሀገራዊ ኪሣራ ውስጥ ዋጋ ሲከፍል ለሲቪሉ መንግሥት አካሄድም አመቺ ሁኔታ አይፈጥርም። አምስተኛው ጣጣም ይህ ነው። ሀገሪቱ በመከላከያው ጫንቃ ላይ ትወድቃለች። መከላከያውም ይህንን ሥርዓት የታደገ፣ ከሁሉም በላይ ዋጋ የከፈለ፣ ሌሎቹ የለኮሱትን እሳት ለማጥፋት የደከመ፣ ሌሎቹ የሸሹትን ዕዳ የተቀበለ ሆኖ ይሰማዋል። ይህ ደግሞ በግጭቶቹ ጊዜ የተፈጠሩ ስሕተቶችን ለማጣራት፣ ለተፈጸሙ ስሕተቶችም እርማት ለመስጠት አዳጋች ያደርገዋል። አሠራሩና ሂደቱ ሳይሆን ውለታውና ዋጋው ከፍ ብሎ ስለሚታይ። ይህ ውለታና ዋጋ በዛሬ ብቻ ሳይሆን በነገው የመንግሥትና የመከላከያ ግንኙነቶች ላይም ተጽዕኖውን ያሳርፋል።

ምንም እንኳን የመከላከያ ሠራዊቱ ሀገሪቱ ችግር ውስጥ ስትገባ ዝም ብሎ መመልከት ባይሆንለት፣ የተሻለ ዐቅም፣ አደረጃጀትና የውሳኔ አተገባበር መዋቅር ስላለው ችግሮችን በአፋጣኝ ለመፍታት ያስችላል ተብሎ ቢታሰብ፣ ይህንን መሰሉን አስተዋጽዖ እንዲያበረክት ሕጉ ቢፈቅድለትና ቢያዘውም፤ አብዝቶ በግጭቶች ውስጥ ሲነከር ግን ከጊዜያዊ ጥቅሙ ይልቅ ዘለቄታዊ ጉዳቱ ያመዝናል። ጉዳቱ ደግሞ ሦስት መልክ ያለው ነው። ሕዝባዊ፣ ወታደራዊና መንግሥታዊ። የተሻለው መንገድ ለችግሮቹ ባሕላዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ሕዝባዊና አስተዳደራዊ መፍትሔዎችን በአፋጣኝ መስጠት፤ ግጭቶችን ከማብረድ ይልቅ ውኃን ከጥሩ፣ ነገሩን ከሥሩ አይቶ መነሻ ችግሩን መፍታት፤ ከዕለት ይልቅ ለዓመት፣ ከአሁን ይልቅ ለወደፊት፣ ከግል ይልቅ ለሕዝብ፣ ከቡድን ይልቅ ለሀገር አስቦ፤ የሚመረውን ኮሶ ውጦ መፍትሔውን ማሻር ነው። መከላከያውንም ከመንደር ወደ ድንበር መመለስ። የሚፈራ፣ የሚከበርና የሚታፈር መከላከያ እንዲኖረን – መከላከያችን ከመንደር ወደ ድንበር ይመለስ።

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...