ከጓደኞቼ ማህደርና እስከዳር ጋር፣ ያቺ በረባሶ ከሚሰራበት ጎማ ጫማ ሰርታ ሸጣ እስካሁን በማይገባኝ ፍጥነትና ሁኔታ ሚሊዮነር የሆነችው ሴትዮ…ማነው ስሟ ? እ……ቤተልሄም… እሷ አዲስ ከከፈተችው ዘናጭ ካፌ ቁጭ ብለን ውድ ማኪያቶ እየጠጣን ነበር። ማኪያቶው አሪፍ፣ ጨዋታው ደማቅ ነበር። መርዶዬን እስኪነግሩኝ…‹‹ናሆምና ማርታ ሊጋቡ ነው›› እስኪሉኝ።
እንደሰማሁ በድንጋጤ ምራቄ ከአፌ አለቀ።
በማኪያቶ የሞቀ ሰውነቴ በአንድጊዜ ቀዘቀዘ።
ሰበባ-ሰበብ ድርድሬ ካሰብኩት በጣም ቀድሜ ተለየኋቸውና ቤቴ ገባሁ።
ናሆም ሊያገባ ነው? የኔ ናሆም ሊያገባ ነው? ያውም ያቺን አብረን እንፎግራት የነበረች ዝንጅብል ቅርፅ ማርታ?
ሶፋዬ ላይ ቁጭ ብዬ ጥፍሬንም ነገርም ሳኝክ፣ ቅናት ሳመነዥክ ልጆቼ ከባለቤቴ ጋር ከትምህርት ቤት መጡ።
– እንዴት ዋልሽ…ፊትሽ ጠቋቆረ ምነው? አለኝ ባሌ ጉንጮቼን በእጆቼ እየዳበሰ።መልካሙ የአስር አመት ባሌ እንኳን ፊቴ በሃዘን ሲከስል ከፈገግታ ሲለይ ይጨንቀዋል።
– ደህና ነኝ…ትንሽ ደክሞኝ ነው..ራስ ምታት አለኝ….ቶሎ መለስኩለት።
ትንሽ ቆይቶ፣ ከጉሮሮዬ አልወርድ እያለ የሚታገለኝን ለመክሰስ የተዘጋጀ ጨጨብሳ ለመብላት ለይስሙላ ብቀርብም አልቻልኩም።
-ትንሽ ደክሞኛል አረፍ ልበል እስቲ …ብዬ ሚዛኔን ስቼ ደረጃው ላይ ባፍጢሜ እንዳልደፋ በመስጋት መወጣጫውን የሙጥኝ ብዬ እንደያዝኩ ወደ መኝታ ቤቴ ወጣሁ።
አልጋዬ ላይ ኩምትር ብዬ ተኛሁ። አልተመቸኝም። ተገለበጥኩ። አሁንም አልተመቸኝም። ብርድ ብርድ አለኝ። ተነሳሁና አንዱን ጋቢ ደርቤ ተመልሼ ተኛሁ። አልሞቀኝም። ከነጋቢዬ ተነስቼ መስኮቱ ጋር ቆምኩ። እንባዬ ያለ ፈቃዴ መፍሰስ፣ ሰውነቴ መርገፍገፍ ጀመረ።
ናሆሜ ሊያገባ ነው?
እርግጥ ነው ፣ ከተያየን ሁለት ረጃጅም፣ ቀለም አልባ እና አታካች አመታት አልፈዋል።
እርግጥ ነው፣ አትድረስብኝ ብዬ ካባረርኩት፣ ከእሱ የሚያገናኘኝን ድልድይ ከሰበርኩ ሃያ አራት ወራት አልፈዋል።
ግን እንዴት አይነግረኝም? እንዴት ለደቂቃ ደውሎ ‹‹ ከሌላ ሰው እንዳትሰሚው ብዬ ነው። ላገባ ነው›› አይለኝም?
ምንስ ቢሆን አብረን ላለፍነው ጊዜ ሲባል፣ ለነበረን ደስታ ሲል ይሄን እንዴት አያደርግልኝም?
ልደውልለት? አልደውልለትም። እሱ ሳይደውልልኝ እኔ አልደውልለትም።
ላግኘው? አላገኘውም። ስለምን ላወራው አገኘዋለሁ? ምንስ እለዋለሁ? ብቻውን ሊያገኘኝ ፈርቶ እየተንቦቀቦቀ ያቺን ማማሰያ እግር ይዞብኝ ቢመጣስ? አላገኘውም።
ደብዳቤ እፅፍለታለሁ።
ምን ብዬ?
ማግባትንህን ሰማሁ…ምነው ደውለህ ሳትነግረኝ..ቢሆንም እንኳን ደስ ያለህ…መልካም ትዳር…ማርታንም እንዴት ነሽ እንኳን ደስ አለሽ በልልኝ….እኔና ሶል ከልጆቹ ጋር ዱባይ ለእረፍት ልንሄድ ነው…ለሁለት ሳምንት….54 ኪሎ ገባሁ እኮ…በጣም ተሸናቅጬያለሁ ብታይ አምሮብኛል…መልካም ትዳር ምናምን ብዬ…
ሳሎን ወርጄ ሽንጠ ረጅም ወረቀትና እስኪብርቶ ይዤ ወደ መኝታ ቤቴ ተመልሼ ደብዳቤዬን ጀመርኩ። ወደ ፊት እንጂ ወደኋላ የማላውቅ ጠንካራ ሴት መሆኔን አሳየዋለሁ። በትዳሬ ፍፁም የረጋሁ፣ መልካም እናት እና ፍፁም ደስተኛ ቀጭን ሴት መሆኔን የሚያመላክት ደብዳቤ መፃፍ ጀመርኩ።
‹‹ሰላም ናሆም..እንዴት ነህ? መቼም በዚህ ዘመን በእጄ ደብዳቤ ስፅፍልህ ግር ሳይልህ አልቀረም። ልታገባ እንደሆነ ስሰማ ደውዬ ከምረብሽህ (መቼም ያው ደስታ ላይ ስለሆንክ) በደብዳቤ ይሻላል ብዬ ነው። በጣም ደስ ይላል። ደግሞ ከማርታ ጋር መሆኑ በጣም አሪፍ ነው። ገና ከድሮ ጀምሮ ትወድህ እንደነበር አውቃለሁ። ደስ ይላል….
ለምን ደውለህ እንዳልነገርከኝ ሳስብ ግምቴ አንድ ብቻ ሆነ። ምናልባት ስሜቷ ይጎዳል ብለህ ይሆናል። ያው ያኔ የነበረኝን ፍቅር አስበህ ምናልባት የኔ ማግባት ሊያማት ስለሚችል አልንገራት ብለህ ነው አይደል? እንደዚያ ከሆነ በጣም ተሳስተሃል። ትንሽም አዝኜብሃለሁ። ትንሽ ክሬዲት ልትሰጠኝ ይገባ ነበር። የተፈጠረው ሁሉ ከሆነ በኋላ ቢሆንም ይህን ነገር እናቁም ብዬ የወሰንኩት፣ የተለየሁህ እኔ መሆኔን ትረሳለህ መሰለኝ….ወይ ደግሞ በኔ ሕይወት ውስጥ ያለህን ቦታ አጋንነህ ትገምት ይሆናል…ባለትዳር …የልጆች እናት ሆኜ ካንተ ስለተኛሁ…በስሜት ማእበል ተውጬ እወድሃለሁ ብዬ ለሁለት አመታት አብሬህ ላይ ታች ስላልኩ በልቤ ውስጥ የተለየ ቦታ እንዳለህ ተሰምቶህ አዝነህልኝ ይሆናል ግን ይሄ ስህተት ነው….
በተዳጋጋሚ ነግሬህ ነበር….
ቦታህን አመላክቼህ ነበር…አሁን ግን ማግባቴ ልቧን ይሰባብረዋል ብለህ ማሰብህን ስገምት ላስታውስህ ፈለግኩ።
ኖሆም፣ አንተ እኮ ደካማ በነበርኩ ቀናት የሰራሁህ ስህተት ነህ።
በረጅም የሕይወቴ መፅሃፍ ውስጥ ቢበዛ አንዲት የማትረባ ገፅ ነህ። ብፈልግ ቡጭቅ አድርጌ ልጥልህ የምችል፣ ስፈልግ ገንጠጥዬ ላወጣህ የምችልግ የማትረባ አንዲት መናኛ ገፅ ነህ። መፅሃፎቹ ባሌ እና ልጆቼ፣ አብረን የገነባነው ቤትና ሕይወቴ ናቸው።
አሁንም መሽቶ በነጋ፣ ነግቶ በመሸ ቁጥር ስላንተ የማስብ፣ የምቆዝም መስሎ ከተሰማህ በጣም ተሳስተሃል። ልጆቼን ከትምህርት ቤት ሳመጣ በየ ትራፊክ መብራቱ ላይ የመኪና መሪ ይዤ የማይረሳ አሳሰሳምህን እያሰብኩ የምብሰለሰል፣ ስንቃበጥ የነበረኝን የሃጥያት ደስታ መልሼ መላልሼ እያሰብኩ እምባ ባይኔ ሞልቶ ከኋላዬ የቆሙት መኪኖች በጥሩምባ ሂጂ ብለው እስኪያምባርቁብኝ ድረስ የት እንዳለሁ የምረሳ ከመሰለህ እጅግ ተሳስተሃል።
ዛሬ ድረስ ከባሌ ጋር ፍቅር ስሰራ ስምህ ከአፌ እንዳያመልጠኝ የምታገል፣ ፀሃይ እንዳትወጣ የተመኘሁባቸውን እነዚያ ካንተ ጋር ያደርኩባቸው አጭርና ስኳር- ስኳር የሚሉ ሌሊቶች እያሰብኩ እምባዬን የማብስ መስሎህ ከሆነ… ናሆም በጣም ተሳስተሃል።
አንተ እኮ ደካማ በነበርኩ ቀናት የሰራሁህ ስህተት ነህ።
በረጅም የሕይወቴ መፅሃፍ ውስጥ ቢበዛ አንዲት የማትረባ ገፅ ነህ። ብፈልግ ቡጭቅ አድርጌ ልጥልህ የምችል፣ ስፈልግ ገንጠጥዬ ላወጣህ የምችል የማትረባ አንዲት መናኛ ገፅ ነህ።
ጌትነትን አልችል ብሎ የጠገበ ባለትዳር ልቤ ሲዋልል የተራመድኩብህ ሰወርዋራ መንገድ እንጂ አውራ ጎዳናዬ አልነበርክም። ዋና መንገዴ ሆነህ አታውቅም።
አሁንም አልጋ ውስጥ ገብተን ትንሽዬ የአንሶላ ድንኳን ቀልሰን ብርሃንም ንፋስም ሳናስገባ የምናወራው፣ የምንሳሳመው፣ የምንደባበሰውን ነገር ሁሌ እያሰብኩ ከእንባዬ የምታገል ይመስልህ ይሆናል።
ለልጆቼ በሶ ሳበሰብስ ፣እዚያች ሚጢጢ ግን የምትሞቅ ቤትህ መጥቼ በሶ በቅቤ ስሰራልህ ሁለመናችን በሶ በሶ እየሸተተ የምንተቃቀፈው፣ ሰውነቴ ከሰውነቴ የሚቆላለፈውን እያስታወስኩ የምርበተበትልህ ይመስልህ ይሆናል።
ግን ተሳስተሃል።
አንተ እኮ ድንገተኛ እንቅፋት እንጂ…ጊዜያዊ ፈርማታ እንጂ ዘላቂ ማረፊያዬ አልነበርክም።
አንተ እኮ ደካማ በነበርኩ ቀናት የሰራሁህ ስህተት ነህ። በሙሉ ጊዜ ሕይወቴ ውስጥ የነበርክ የትርፍ ጊዜ ስራ ነህ። መሪ ሳይሆን አጃቢ …ዋና ሳይሆን አስተኔ ገፀባህሪ።
በዛሬው ሕይወቴ ስንዝር ቦታ የሌለህ የሕይወት ታሪኬ ውስጥ በእመጫት የገባህ፣ በስርዝ ድልዝ ያስወጣሁህ ምራቂ ሰው ነህ።
እስከዛሬ በፌስቡክ፣ በቫይበርና በዋትስ አፕ የምንላላካቸውን ‹‹ሴክስቶች›› እያነበብኩ የምታመም፣ ፎቶህን ከባሌና ልጆቼ በሚስጥር ቆልፌ መታጠቢያ ቤት ገብቼ እያየሁት የማለቅስ፣ በፈገግታህ የምታመም፣ በናፍቆትህ የምፈረካከስ ይመስልህ ከሆነ ተሳስተሃል።
የሁለት አመት ወጣ-ገባ ፍቅራችን፣ የድብቅ ስሜት ጡዘታችን የአስር አመት ትዳሬን አፈር ድሜ አስግጦት የሕይወት ትርጉም፣ ጭራና ቀንዱ ጨርሶ እንደጠፋብኝ፣ በየቀኑ ሃዘን እንደ ቱባ ክር እንደሚተረትረኝ የምታስብ ከሆነ በጣም ተሳስተሃል።
አንተ እኮ ስምህ በእርሳስ የተፃፈ የማፍርብህ ትላንቴ እንጂ ዛሬዬ ወይ ነገዬ አይደለህም።
በአሸዋ ላይ አንፄ ወዲያው ያፈረስኩህ ዛኒጋባ ቤት እንጂ ቋሚ መኖሪያ አይደለህም።
አሻራ አልባ ዱካ እንጂ የማትረሳ ሰው አይደለህም።
ስለዚህ ማርታን ለማግባት ስትወስን በመደወል ፈንታ፤ ብነግራት ትናዳለች፣ ብነግራት ትሰባበራለች፣ ሰርጌ መርዶ ይሆንባታል በሚል ታብየህ ከሆነ ተሳስተሃል። በልቤ ያለህን ቦታ በድፍረት አጋንነሃል፣ በድፍረት አስፍተሃልና ትንሽም ታሳዝናለህ።
ለማንኛውም ልክ እንደኔ የራሴ የምትለው ሰው ስላገኘህ ደስ ብሎኛል… ናሆም…..
መልካም ጋብቻ ናሆሜ….መልካም ጋብቻ….