Tidarfelagi.com

‹‹ልቤ››

አዲስ ፀባይ ካመጣች ሰነባበተች።

ስሙን ለመጥራት ሰበብ መፈለግ እስክታቆም ወዳዋለች። ይሉኝታዋን እንደ ቆሸሸ ልብስ እስክታወልቅ ልቧን ሰጥታዋለች። ፍቅር ይሉኝታ ያስጥል የለ? ምን ይሉኝ ፍርሃትን ይገፍ የለ? እህ…እንደሱ።

የጀማመራት ሰሞን ፣ ‹‹በረከት እኮ…ሂ ኢዝ ሶ ስማርት…እኛ ቢሮ የሚቆይ አይመስለኝም…ማስተርሱን ይጨርስ እንጂ ዩኤን ይጋደልበታል …እጁን ስመው ነው የሚቀበሉት››
‹‹ባለፈው ከነ በረከት ጋር ሄድንበት ያልኩህ ካፌ ትዝ ይልሃል? እዚያ ውሰደኝ…››
‹‹በረከት እኮ ካለ ቶሞካ ቡና አይጠጣም…እስቲ አንተም የዚህን የመንደር ቡና ተውና እዛ ጠጣ…››
‹‹ እስቲ ይሄን ዲኦ ተቀባው…የዛሬ ወንዶች እኮ ካለዚህ አይቀቡም…አሽተውማ…ወንዳወንድ ሽታ…ደስ አይልም? ?

እያለች ነው የጀመረችው።

አብረን ብዙ ቆይተናል፣ ‹‹ብዙ ነገሬን አስታምማ ነው የምትኖረው፣ እወዳታለሁ፣ ከእሷ የተሸለ ሴት አላገኝም›› እያልኩ ተውኳት። አለ አይደል…ሲጋራ አጨሳለሁ…ጫት እቅማለሁ…እጠጣለሁ…ትወቅ አትወቅ አላውቅም እንጂ ሌላ ሴት ጋር ሄጄ አውቃለሁ….ሱሱንም ቢሆን እንደ ሌሎች ሴቶች ተው እያለች አተነዘንዘኝም…ከነምናምኔ ትወደኛለች ››…እያልኩ።

የሚያልፍ ነገር ይሆናል…ትረሳዋለች…ብዬ ተውኳት እሷ ግን ባሰባት። ስሙን በየቦታው ከመሰንቀር ዘልላ በሃሳብ-በመንፈሷ ተሸክማው ትገባና ትወጣ ጀመር።

ሳምንታት ሲያልፉ ነገሩ አድጎ ይሰረስረኝ፣ ይገዘግዘኝ ጀመር። ሁለመናዋ ይቀየር ጀመር።

አንዱን እሁድ ምሽት መፅሃፌን ትቼ አስተውላት ነበር።
አብረን መኖር ከጀመርን ሶስት አመት ስላለፈን የምሽት- የቀን – የአዘቦት ድርጊቷን ቅደም ተከተሉ ሳይዛነፍ አውቀዋለሁ። ሳምሪ ግዴለሽ ሴት ናት። ፀጉሯን በየሳምንቱ የውበት ሳሎን ሄዳ የማታቃጥል፣ ልብሷን ተኩሳ የማትለብስ፣ ኩል እና ቻፒስቲክ የሜክአፕ ጥግ የሚመስላት፣ አዲስ ልብስና ጫማ በቀጠሮ የማትገዛ ግዴለሽ ሴት ናት።

ያን ማታ ስታደርግ ያየሁት ነገር እንግዳ የሆነብኝ ለዚህ ነው።
በመተኛትና በመቀመጥ መሃከል ሆኜ መፅሃፍ የማነብበት አልጋ ጫፍ ላይ አይቼ የማላውቀውን ቄንጠኛ እና ውድ የሚመስል ፓንት ከመሳዩ ጡት መያዣ ጋር ዘርግታ ልክ ቢለበስ ምን እንደሚመስል በሚያሳይ ሁኔታ ለረጅም ደቂቃዎች ታየዋለች።

ከዚያ ደግሞ ሁለቱንም ታነሳና ጡት መያዣውን ያደረገችውን አሮጌ የሌሊት ካናቴራ ሳታወልቅ አድርጋ ፓንቱን ደግሞ በተግባቢው ቦታ ላይ በሁለት እጆቿ ደገፍ አድርጋ መስታወት ታያለች።

– አዲስ ነው አይደል ይሄ ነገር….?አልኳት ትኩረቷን ለመስበር
– እ…? አለች ፓንቱን ወደ አልጋው ጥላ ከነጡት መያዣዋ ወደ እኔ እየዞረች
– ፓንቱና ጡት መያዣው…አዲስ ነው ወይ…? ራሴን ደገምኩ..
– እ…አዎ….ያምራል አይደል?
– አዎ…ግን እንዲህ አይነት ነገር ስታደርጊ አይቼሽ አላውቅም….ነይ እስቲ..አልኳት መፅሃፌን ወደ አንደኛው የአልጋው ጥግ ወርውሬ ቀኝ እጄን ዘርግቼ..

መጣች።

– ለኔ ነው…?ፈገግ ብዬ ጠየቅኩ…
– ሃ.ሃ…ታዲያ ለማን ይሆናል…እጆቼን ይዛ መለሰች
– ልበሺውና ልየዋ…
– አይ….ለነገ ነው…ማታ ታየዋለህ….

ተስፈንጥራ ወደ ቁምሳጥኑ ሄዳ ልብሶቿን አለቅጥ ማተራመስ ጀመረች።

– ምነው…ምን ሆንሽ…?አልኩ ባካሄዷ ድንገተኝነት ተገርሜ
– አይ…ለነገ ልብስ ልምረጥ…ጠዋት መተራመስ አልፈልግም…
ነገ ስለምትለብሰው ልብስ ስትጨነቅ አይቻት አላውቅም። ጠዋት ላይ እጇ የገባውን ልብስ አድርጋ እንደነገሩ ሆና እንደምትወጣ ነው የማውቀው።

ለአፍታ የረሳሁት ጥርጣሬ ሆዴ ውስጥ ተገላበጠ።

ያ ሁሉ ግዴለሽነትዋ የት ገባ? ያልፋል ያልኩት ተባራሪ ስሜቷ መቼ ስር ሰድዶ ባህሪዋን መቀየር ጋር ደረሰ?

ያን ቀን ነገር እያላመጥኩ አድሬ ነጋልኝ።

ሲነጋ.፣ ከጠዋቱ አንድ ሰአት አልፎ በታክሲ አናገኝም ጭንቀት ተሰቅፌ ቶሎ እንውጣ እያልኩ እማፀናታለሁ።

– ረፈደ ሳምሪ..ቶሎ በይ…
– በናትህ ልብሴ ሁሉ አስጠላኝ…
– ትላንት መረጥኩ አላልሽም?
– አዎ ግን አስጠላኝ…
– ያ ስኩዌር እሰኩዌሩ ሱሪሽ አሪፍ አይደል? እሱን ልበሺ ሳምሪ..
– አንተ ደግሞ…እሱ በጣም ሰፊ ነው…
– ሰፊ ልብስ የምትወጂ መስሎኝ…
– እወድ ነበር አዎ…ግን ሰፊ ልብስ ይበልጥ ያወፍርሻል ብሎኛል…ማለቴ ብለውኛል…ጓደኞቼ

ተንተባተበች።

ሲጋራ ልለኩስ በረንዳ ወጣሁ።

የሁለት ሲጋራ እድሜ ጠበቅኳት። አልወጣችም። በጥልቅ ተነፈስኩና ወደቤት ገባሁ።
– ሳምሪ..!
– ጨርሻለሁ
እየተንደፋደፈች ሁሉ ነገሯን አጣብቆ ይዞ፣ ጾታዋን በአንድ እይታ ብቻ የሚያረጋግጥ እጅግ ጠባብ ቢጫ ሱሪ ለብሳለች።

አይቼው አላውቅም።

ፀጉሯን ሙልጭ አድርጋ አሲዛዋለች።

ይሄንንም አላውቀውም።

ማታ ያየሁት ጡት መያዣዋ ጫፍ ከለበሰችው ነጭ ሹራብ አፈንግጦ ይታያል።
ይሄንንም አልለመድኩትም።

ያለ ቦታዋ የምትወድቅ አንዲት ዘለላ ፀጉር እስክትረብሻት ድረስ ተጨንቃና ተጠባ ያመለጡ ፀጉሮች እንደሌሉ ለማረጋገጥ ፀጉሯን ትሞዥቃለች። ከኩል ውጪ የማታውቅ ሚስቴ….የአውሮፓ እግር ኳስ ቡድን ደጋፊ መስላ መጥታለች።
– ምንድነው ዛሬ እንደዚህ ለየት ያልሽው አልኩ ታክሲው መጠበቂያው ጋር ስንደርስ
– ስብሰባ አለን..እኔ፣ ቃልኪዳን እና በረከት ስብሰባ አለን…

በረከት።

ጥርሴን እያንገጫገጭኩ ታክሲ ውስጥ ገባሁ።

በዚያ ሳምንት ቅዳሜ ጠዋት ለአራተኛ ጊዜ ቃልኪዳን እና በረከት ቤታችን እንደሚመጡ ነገረችኝ።
– ያው እንዳልኩህ በረከትም ይመጣል…ስምንት ሰአት ነው የሚደርሱት..ጥቁር ስንዴ ዳቦ እወዳለሁ ሲል ስለነበር እሱን ከባልትናው ቤት አዝዤለታለሁ…ማለቴ ቃልም ስለምትወድ…ይዤ እመጣለሁ…ልጅቷን ቤቱን በጠዋት መጥተሸ አፅጂ ብያት ነበር…የት አባቷ ናት በናትህ?….

ለስምንት ሰአት ቀጠሮ ከጠዋቱ ሁለት ሰአት ተኩል ላይ ምን እንዲህ እንደሚያደርጋት አውቃለሁ።

ድፎ ዳቦው…ጽዳቱ…ለወትሮው ከሰአት የምትመጣውን ተመላላሽ ሰራተኛችንን በሌሊት ድረሺ ማለቱ… ከሁለት ቀን በፊት የተጀመረው ባለ 6 ወጡ ድግስ….ግልፅ ነበር።

ዳቦዋን ይዛ ስትመጣ ሶስት ሰአት አልፎ፣ ልጅቱም መጥታ ፅዳቱን አጧጡፋ ነበር።

ስምነት ሰአት ከሩብ ሆነ።

ተሞልጮ የታሰረ ፀጉሯን አስር ጊዜ እየነካካች፣ ጥብቅ ያለ ቀሚሷ ያወጣውን ሞላላ ቂጧን ሰላሳ ጊዜ በመስታወት እያየች፣ በሜክአፕ ያበደ ፊቷን መቶ ጊዜ እያስተካከለች በመቁነጥነጥ ስትጠብቅ ቆይታ ስምነት ከሩብ ላይ በራችን ተንኳኳ።

ሚስቴን ሳይነጥቀኝ የወሰደውን፣ ሳይቀማኝ ያገኛትን ሰው ላየው ነው።
ፍቅሬን አጠገቤ እያለች እንቁልልጭ ያደረገብኝን ሰው ልተዋወቀው ነው።

በሩን ከፍታ ቃልኪዳን (በኔ ግምት ብቻውን መጣ እንዳይባል የገባች ሰበብ ናት) ካቀፈቻት በኋላ ልክ አይታው እንደማታውቅ ሰው እጆቿን ስትዘረጋለት ተመለከትኩ።

ረጅም፣ ጠይም ፣ ደልዳላና ዱባ ከንፈር ያለው ቢገፋ ቢገፋ ከሰላሳ ሶስት የማይዘል ሰው ነው።

በሳምኳት ቁጥር ስስ ከንፈሮቼን መንከስ የመጀመረችው ይሄን ዱባ ከንፈሮቹን ያገኘች እየመሰላት ይሆን?

እንዲህ አቅርባ የምታወራውን ሰው ለሁሉም ሰው እንደምታደርገው በማቀፍና መሳም ፈንታ እጆቿን ለመጨባበጥ ስትዘረጋለት ቤቴ ቤቴ ሳይሆን የብሄራዊ ቲያትር መድረክ፣ እነሱም ሊተውኑ የመጡ የኪነት ሰዎች ሆነው ያዩኝ።

– በረከት ባሌን ተዋወቀው.. አለችና ቀድማው ወደ እኔ መጣች። ስትሰናዳበት እንደቆየችው ቂጡዋን በእሱ የእይታ ማእቀፍ ውስጥ አድርጋ እየተወዘወዘች ስትመጣ እንደማፈር ብሎ እያያት ሲከተላት ተመለከትኩ።
– ሙሉጌታ…አልኩት የጨበጠኝ እጁን ጭምቅ አድርጌ ጨብጬ… የገዛ ስሜ አፌ ውስጥ ዝገት ዝገት እያለኝ…

ቤታችን ከሚፈቅደው በላይ የተነጋገሩ በሚመስል ሁኔታ..ተራርቀው ተቀመጡ። አልፎ አልፎ ካልሆነ አይተያዩም።
አየኋት።

መላ አኳሏ ሰፍ ብሎ ሲጠብቀው እንዳልቆየ ሁሉ እጆቹን ለመጨበጥ መስደዷ፣ አሁን ደግሞ ካጠገቧ አስፈንጥራ ማስቀመጧን እያሰብኩ አየኋት።

አየሁት።

አይቶ እና ነክቷት እንደማያውቅ ሁሉ እጆቹን ባፈረ ሰው አኳኋን አጣምሮ፣ ሶፋው ላይ እየተቁነጠነጠ ተቀምጧል።

ቀሽም ተዋናዮች!

የግብዣውን ቡፌ አጋምሶ ሆዱ ጢቅ እስኪል ከበላ በኋላም የጠገበ አልመሰላትም መሰለኝ…
– በረከት ይሄ ዳቦ እኮ ልክ አንተ እንደምትወደው ነው…ያዝ እንጂ
– አረ ጎመን በስጋውን መች ነካኸው በረከት…
– ላዛኛው ከውጪ የመጣ መስሎህ ነው.? .በረከት ሙት …እኔው ራሴ ነኝ እኮ የሰራሁት…ባለሙያ እኮ ነኝ ሃሃ

ምሳው አብቅቶ ለቡና ስንቀመጥ እንደገና አየኋቸው።
በአይኑ ይነካታል።
በአይኑ ልብሷን ያወልቃል።
በአይኑ ይተኛታል።

በአይኖቿ ትስመዋለች።
በአይኖቿ ትዳራዋለች።
በአይኖቿ የአልጋ ላይ ጨዋታ እንደሰመረላት ሴት እየተስለመለመች ትሞትለታለች።

ያለ ቃል፣ ያለ አልጋ፣ ፊት ለፊቴ ሲዳሩ ደሜ ከፍ አለ። ሲጋራ ላጭስ ብዬ ወጣሁ።

አርባ አራት ሲጋራ ይመስለኛል አጭሼ ስመለስ ጭኮ ቀርቧል።

ይሄ ሰው ሚስቴን ብቻ ሳይሆን ጓዳዬንም ሊዘርፍ ነው የመጣው?

– ብላ በናትህ…እንደ ወለጋ ጭኮ ባይሆንም አሪፍ ነው….አለችው ሶፋው ላይ ዝርፍጥ ብዬ ስቀመጥ
– በቃኝ ሳምሪ….ተግደረደረ
– እስቲ እሱን ነገር ለእኔ ስጪኝ….አልኩ ንዴቴ ጢም ብሎ ሲሞላ።

አየችኝ።

– ምነው…ጭኮ እንደምወድ ታውቂያለሽ..ስጪኝ…አልኩ መልሼ
– እኔ እኮ ለበረከት የገዛሁት ደምቢዶሎ የምበላው የእናቴ ጭኮ ናፈቀኝ እያለ ሲያወራ ሰምቼ አሳዝኖኝ ነው…አንተማ አይፈቀድልህም….ሃሃ
ሳቀች።

ጥርስሽ ይርገፍ።

– ተይ እንጂ…በቤቱ አትከልክይው…አለች ቃል ከዳን ተነስታ ሰሃኑን እያመጣች። መምጣቷን ብቻ ሳይሆን መፈጠሯንም ረስቼው ነበር።
– ተይ ቃል….ወድጄ እኮ አይደለም የከለከልኩት..ቦርጩን አታይም…?ያወፍረዋል….በረከት እኮ ቢያንስ ጂም ይሰራል…የኔ ባል ግን ሰነፍ ነው….ለእሱ አስቤ እኮ ነው…

አላበዛችውም?

ከአንድ ሳምንት በኋላ…

የበረከት ስም በድንገት ሊባል በሚችል ሁናቴ ከሚስቴ አፏም ከቤታችንም ተለየ። ፈፅሞ አትጠራውም። ጨርሶ አታነሳውም።

በነገሩ ስገረምም ስብሰለሰልም ከረምኩና አንዱን ማታ የመጣው ይምጣ ብዬ፣
– እኔ የምልሽ…አልኳት
– አንተ የምትለኝ…?
– ያ በረከት ደህና ነው…?ምነው ስለእሱ ስታወሪ አልሰማም ይህን ሰሞን?
አልቆዘመችም። ለማሰብ ጊዜ አልወሰደችም። ልክ ለጥያቄው እንደተዘጋጀች ሁሉ
– ኡፍ…እሱ ልጅ እንዳስጠላኝ….አለችኝ
– ምነው ምን አደረገ?እያቁነጠነጠኝ ጠየቅኩ
– አይ…ምንም….ማለት እኔን ምንም አላደረገኝም ….ግን አንዳንድ ሰው ደህና ይመስል እና ስታውቀው ይደብርሃል…አይደል? እንደዛ ነው….በቃ አለ አየደል…

ወሬዋን ሳትቋጭ አቀርቅራ ወደ ማእድ ቤት ሄደች
ስታውቀው ይደብርሃል? …
ምን ተፈጥሮ ነው? ተኝቷት አይንሽን ላፈር አላት?
ሌላ አየባት?
ተደብሮባት ወደ ዩኤን ሄደ? እጁን ስመው ተቀበሉት?

ሲያዝንባትና ሲጠየፋት የከረመ ገላዬ ተኮማተረ። የበጠሰችው አንጀቴ ደነደነ።

በነጋታው እንቅልፍ ያላየ አይኔን እያሻሸሁ ሳሎን ሆኜ ንግስቴን ‹‹ ከልቤ ዙፋን ተባረሻል›› ብዬ ለመንገር እሰናዳለሁ።
ለምን እንደበቃኝ ላስረዳት እዘጋጃለሁ።

ሃሳቤን ሳልቋጭ መጣች።

ፀጉሯን በቅድመ- በረከት ዘመን እንደነበረው ጨብራራ ፍሪዝ አድርጋ፣ የምወደውን ዘልዛላ ሰፊ ሱሪዋን እና ታኮ የለሽ ክፍት ጫማዋን ተጫምታ ከመኝታ ቤት መጣች።

አየኋት።

…ልቤ አንገራገረ።

የጎዳችው ልቤ አንገራገረ።

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...