Tidarfelagi.com

“ሌጋሲዬ”

እስቲ ዛሬ በጥያቄ ልጀምር።

ከመሬት ተነስቼ “ አልፍሬድ ኖቤል” ብል መጀመሪያ ወደ አእምሯችሁ የሚመጣው ምንድነው?

ለብዙዎቻችን መልሱ ‹‹ዝነኛው የኖቤል ሽልማት ነዋ!›› ይሆናል ብዬ እጠረጥራለሁ።

ከዚያ ሁሉ በፊት ግን ይሄ ገናና ሽልማት በየአመቱ በስሙ የሚሰጥለት አልፍሬድ ኖቤል ስራው ምን ነበር? መተዳደሪያውስ?

እንደ ማዘር ቴሬዛ ድሆችን መመገብ እና መደገፍ አልነበረም።
እንደ ማንዴላ እና ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር ለነጻነት መታገል አልነበረም።
እንደ ሮዛ ፓርክስ በልበ ሙሉነት በተጨቆኑ ህዝቦች ስም ሊጋፉት በማይችሉት ባላጋራ ፊት እምቢተኝነትን መግለፅም አልነበረም።

ዛሬ ለእነ ባራክ ኦባማ፣ ለነ ኤለን ጆንሰን ስረሊፍ እና ዋንጋሪ ማታይ እና ለሌሎችም የተሰጠው የሰላም ሽልማት በስሙ የተሰየመለት ሰው ዋነኛ መታወቂያው ጅምላ ጨራሽ ፈንጂዎችን መፍጠሩ ነበር።

አባቱም ቢሆኑ ዘመናቸውን ሁሉ ከአንድ የጦር መሳሪያ ፋብሪካ ወደ ሌላ እየተዘዋወሩ ሲያስተዳድሩ፣ ንግዱን ሲያስፋፉ ኖረዋል።
አጅሬ ኖቤልም የእሳቸውን አጥፊ ፈለግ ተከትሎ እንደ እነሱ አቆጣጠር (እእአ) በ1867 ዳይናማይት ሲፈጥር ፈጠራው ከዚያ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ አኳኋን ብዙ ሰዎችን በአንድ ጊዜ እምሽክ አድርጎ መጨረስ በመቻሉ እጅግ ተደነቀ። ስሙ ገነነ፤ ሃብትና ንብረቱም ተስፋፋ።

ኖቤል በህዝብ መፍጃ መሳሪያ ፈጠራ በነበረው ስኬት ብዛት በሕይወቱ መጨረሻ ገደማ መቶ የሚደርሱ የፈንጂና የጦር መሳሪያ ፋብሪካዎች ባለቤት ሆኖ ነበር።

ታዲያ እንዴት ሆኖ ጦርነትን የበለጠ አስከፊ፣ ከመቼውም የበለጠ እጥፍ ድርብ የሰው ልጅ ሕይወትን የሚቀጥፍ ለማድረግ የሚተጋ፣ ተግቶም ገንዘብ የሰበሰበ ሰውዬ ዛሬ ስሙ ከሰላም ጋር ይነሳል?

‹‹ሌጋሲው›› ከጦር መሳሪያ አምራችነት ወደ የሰላም ሽልማት ሰጪነት እንዴት ሊሸጋገር ቻለ?

ነገሩ ወዲህ ነው።

አሁንም እእአ በ1888 ፈረንሳይ ሃገር ይኖር የነበረው የኖቤል ወንድም ሉድቪግ ይሞታል።
የእሱን ሞት ተከትሎ በጊዜው ፈረንሳይ ውስጥ ይታተም የነበረ አንድ ታዋቂ ጋዜጣ ታላቅ ስህተት ሰራ። ምን አደረገ? የሉድቪግን ሞት የታዋቂው አልፍሬድ ኖቤል ሞት ነው ብሎ ዘገበ።

‹‹ ሞትን በማከፋፈል የከበረው አልፍሬድ ኖቤል ዛሬ ከዚህ አለም በሞት ተለየ›› በሚል ርእስ ዜናውን አተመ።

የስህተቱን ዜና ያነበበው ዓለም እውነቱን ሲረዳ ቢዘነጋውም ይህንን ዜና፣ በተለይም ርእሱን ያነበበው አልፍሬድ ኖቤልን ግን ፍፁም እረፍት ነሳው።

እውነት ብሞት የዜና እረፍቴ ርእስ ይህ ነው የሚሆነው?
በቃ የኔ ብቸኛ ሌጋሲ ሞትን ማከፋፈል ነው? ሲል ተብሰለሰለ።

ተብሰልስሎም አላበቃ በወንድሙ ሞት ያገኘውን ‹‹ሌጋሲውን›› የመቀየር ልዩ አጋጣሚ ሊጠቀምበት ቆርጦ ኑዛዜውን እንዲህ ብሎ አፃፈ።

‹በስሜ ፋውንዴሽን አቋቁማለሁ። ከስራዬ ያገኘሁት አብዛኛው ሃብቴ በዚህ ፋውንዴሽን አማካኝነት ለሚሰጥ ሽልማት እንዲውል እፈልጋለሁ። ሽልማቱም የሰው ልጆችን ለመረዳት እና ኑሯቸውን ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ለሚያደርጉ ሰዎች በየአመቱ እንዲሰጥ ይሁን።››

ባለቀ ሰአት የሌጋሲውን መሪ የጠመዘዘው ኖቤል ያሰበው ሆኖለት በስሙ ለሰላም እና ለሌሎች በጎ አስተዋፅኦ ላደረጉ ሰዎች በሞተበት ቀን የሚሰጠው ሽልማት ስሙን አደሰው። የማይሞት ስሙን በበጎ ቦታ ላይ ተከለው።

በዚህ ‹‹የሌጋሲ ማስተካከያ ውሳኔው›› ኖቤል የሚለው ስም ከሞት አከፋፋይ ነጋዴነት ወደ ሰላም ወዳድ የፈጠራ ሰውነት ተቀየረ።

የኖቤል ታሪክ ፤ እኔስ ድንገት ዛሬ ክልትው ብል እና የእረፍቴ ዜና ጋዜጣ ላይ ቢወጣ ርእሱ ምን ይሆናል የሚለውን ጥያቄ አያስጠይቃችሁም?
ስለ ‹‹ሌጋሲያችሁ›› አያሳስባችሁም?
በጎ ስም ካላተረፋችሁ እንድታተርፉ፣ እኩይ ስም ከተሰጣችሁ ልክ እንደ ኖቤል የሌጋሲያችሁን መሪ ጠምዝዛችሁ ዛሬውኑ ቀይሩት ቀይሩት አያሰኛችሁም?

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...