Tidarfelagi.com

ላንድ ላልታወቀ አህያ ነጂ

የሚከተለው ግጥም በሚታየው ታሪካዊ ፎቶግራፍ ንሸጣ የተፃፈ ነው፤ በፎቶው ላይ ሻምበል አበበ ቢቂላ የልምምድ ሩጫ ሲሮጥ ይታያል፤ ከሁዋላው አህያ እየነዳ የሚያልፍ አላፊ ጠፊ ገበሬ አለ፤ ግጥሙን የጣፍኩት ለዚህ አህያ ነጂ ገበሬ ነው፤ )

ላንድ ላልታወቀ አህያ ነጂ

ባሮጌው ጎዳና፤ በጮርቃው ማለዳ
ጋልቦ እንዳልደከመ፤ እንደ ጥቁር ፈርዳ
አቤ እየሠገረ
ከኋላው የሚሳብ፤ አህያ እየነዳ
ስሙ ማን ነበረ?

የመንደር ወፍጮ ቤት፤ ቅሪቱን ሲተፋ
ዱቄት የሚለብሰው
በዝነኞች ፊት ላይ፤ ካሜራ ሲያካፋ
ጠብታ ሚደርሰው
ማን ይሆን ይሄ ሰው?

እኛ የምናዘው፤ እሱ የሚሰማን
ሰው እያደረገን፤ ከሰው የማንቆጥረው
አህያ እየነዳ፤ አስፋልቱን ሲሻማን
የምንገፈትረው፤
በጥሩምባ እሩምታ፤ ምናስደነብረው፤

በኑሮው ምንቀልድ፤ በሞቱ ምንተርት
በፈረሰ ጎጆው፤ ፓርቲ ምንመሠርት፤
ፊቱ ቢልቦርድ ላይ፤ ወጥቶ ባይሰጣ
ጀግና የማይባል
ግና ለጀግኖቹ፤ ጉልበት የሚያዋጣ፡፡

ካበበ ሰሀን ላይ፤ በሶው እንዳይጠፋ
በተራ ክንዶቹ፤ ተራራ ሚገፋ
ለናቀችው ዓለም፤ ላቡን የገበረ
ስሙ ማን ነበረ?

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

3 Comments

  • ልሳን commented on December 14, 2017 Reply

    የፊታችን እሑድ የሆሳዕና በዓል ይከበራል፡፡ ሆሳዕና የአህዮች ክብረ በዓል ነው፡፡ መቼም እንደ ዕለተ ሆሳዕና አህያ በታሪኳ የከበረችበት ቀን ያለ አይመስለኝም፡፡ ዙሪያዋን እየተዘመረ፣ ዘንባባ ተይዞ፣ ምንጣፍ ላይ እግሯ በኩራት እየተራመደ በኢየሩሳሌም ጎዳና ላይ ተጉዛለች፡፡ ከዚያ በኋላ ግን አህያ ስሟ እንዴት ሊጠፋና የድድብና፣ የሸክምና የድንቁርና ምሳሌ እንደሆነች እግዜር ይወቅ፡፤ ምናልባትም ከ50 ዓመት የዘለለው የአህያ ሽማግሌ አይገኝም እንጂ እንጠይቀው ነበር፡፡ ምን ያደርጋል ታድያ የአንድ አህያ እድሜ ቢበዛ ከሃምሳ አይበልጥም፡፡ ያም ሆኖ በአዳጊ አገር ውስጥ እድሜ ያጥራልና የአህያም እድሜ ከ10 አይበልጥም አሉ፡፡ ሽማግሌ ከሌለ እዚህ ሀገር ታሪክን ማን ያስታውሰዋል፡፡ የሀገሬ ታሪክ ነገርን ከመጽሐፍ በላይ በሚያስታውሱ ሽማግሌዎች ልቡና እንደ ጽላት ተጽፎ እንደሚገኝ የማያውቀው ያ የጀርመን ፈላስፋ ሄግል ‹ያልተጻፈ ታሪክ ታሪክ አይደለም› አለ፡፡

    አህያ ከሰው ጋር መኖር ጀመረች የምትባለው የዛሬ 5000 ዓመታት ገደማ አፍሪካ ውስጥ ምናልባትም ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ ሆኖ እየቀረበ ያለው ደግሞ የሜዳ አህያ የሚገኘው ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማልያ ውስጥ ብቻ መሆኑ ነው፡፡ ሰውን ማገልገሌ ካልቀረ አገር ላቅና ብላ መጀመሪያ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሄዳ በኋላ ደግሞ ወደ አውሮፓ ተሻገረች፡፡ አህያን መጀመሪያ ከአፍሪካ የወሰዷት ሮማውያን ናቸው፡፡ ሮማውያን ወደ ሰሜን አውሮፓ ሲስፋፉ በዚያው ሰሜን አውሮፓ አስገቧት፡፡ እንኳን ዛሬ አልሆነ እንጂ ከአፍሪካ መሄዷ ሲታወቅ ሕገ ወጥ ስደተኛ ነበር የምትባለው፡፡ የግብጽ ሥልጣኔ እያልን የምንጠራው ታላቁ የዓባይ ሥልጣኔ ‹የአህዮች ሥልጣኔ› ነው ይሉታል፡፡ ያ ሁሉ ሀብት ከምድረ አፍሪካና ከመካከለኛው ምሥራቅ ተጭኖ ግብጽ የገባው በአህያ ጀርባ ነውና፡፡ አውሮፓና እስያን ያገናኝ በነበረውና ከሰላማዊው ውቅያኖስ እስከ ሜዲትራንያን ባሕር በተዘረጋው ጥንታዊው የሐር መንገድ ላይ ሲወጡ ሲወርዱ የኖሩት አህዮች ናቸው፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ43 ዓመት ሮማውያን እንግሊዝን በወረሩ ጊዜ ብሪታንያ የዘለቁት አህዮች ዛሬ እዚያው ብሪታንያ ውስጥ ለመኖር ከፈለጉ ፓስፖርት እንዲኖራቸው ሕጉ ያዛል፡፡ በ16ኛው መክዘ ደግሞ ስፔኖች አህያን ወደ ላቲን አሜሪካ አደረሷት፡፡ አህያን ያለ ዲቪና አሳይለም በ1598 ዓም ሰሜን አሜሪካ የወሰዳት ዩአን ዲ ኦናቴ የተባለው አሳሽ ነው አሉ፡፡ ቻይና ዓለምን የምትመራው በሕዝብ ብዛት ብቻ ሳይሆን በአህያ ብዛትም ጭምር ነው፡፡ በምድሪቱ ላይ ካሉት 41 ሚሊዮን አህዮች መካከል 11 ሚሊዮኑ አህዮች የሚገኙት ቻይና ውስጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በ5 ሚሊዮን፣ ሜክሲኮ በ3.2 ሚሊዮን ሁለተኛና ሦስተኛ ናቸው፡፡

    ‹አንድ እግረኛ ያወራውን ሃምሳ ፈረሰኛ አይመልሰውም› የተባለው ደርሶባት እንጂ አህያ እንኳን ‹ደደብ› አልነበረችም፡፡ አህያኮ የኖረችበትን አካባቢና ሌሎች ወዳጅ ዘመድ አህዮችን ሳትረሳ ለሃያ አምስት ዓመታት ማስታወስ የምትችል ፍጡር ናት፡፡ ዛሬ ሰው በሳምንትና በወር እየተረሳሳ ‹እገሌኮ ረሳኝ፣ እጄ አመድ አፋሽ ነው፣ አይ ሰው – ከዓይን ከራቁ ከልብ ይርቁ› እያለ በሚተርትበት ዘመን ሃያ አምስት ዓመት የበላችበትን ቤትና አብረዋት የበሉትን አህዮች የማትረሳውን አህያ እንዴት ‹ደደብ› እንላታለን፡፡ እስኪ ወጣ በሉና ገጠሩን ተመልከቱትማ፡፡ ገበሬው ለገበያ ይወጣና አህሉን ሽጦ ሲመለስ፤ መንገድ ዳር ወዳለው ጠጅ ቤትና ጠላ ቤት ጎራ ይላል፡፡ አህያዋ ግን ግራና ቀኝ ያገኘችውን ሣር እየጋጠች ቀጥ ብላ ወደ ሠፈሯ ታቀናለች፡፡ ጅብ ካላገኛት፣ ሌባ ካልሰረቃት በቀር አህያ ቤቷን ስታ አትጠፋም፡፡

    አህያን ‹ደደብ› ያስባላት ሰው በፈለገው መንገድ እንደፈለገው ስለማይወስዳት ነው፡፡ ይኼው የፋርሱ ጠቢብ በለዓም እንኳን እስራኤልን ሊረግም ሲጓዝ አህያው አልሄድም ብትለው እስኪበቃት በዱላ ዠልጧት የለ፡፡ ግን ጥፋቱ የማን ሆኖ ተገኘ? የራሱ የበለዓም ነዋ፡፡ አህያዋ ያየችውን ጠቢቡ ለማየት ባለመቻሉ፡፡ አህያዋ ከፊቷ መልአኩን አየች፤ ከዚያ ቆመች፡፡ ጠቢቡ ግን አላየውም፡፡ ታድያ አህያ ከጠቢቡ በላይ ጠቢብ አልሆነችም፡፡ ይህ የአህያ ጠባይ በሳይንስ ተረጋግጦላችኋል፡፡ አህያ ትሞታለች እንጂ ሰላማዊ ባልሆነና ደኅነቷን በማያረጋግጥ ሁኔታ ውስጥ አትገባም፡፡ አህያ ሊመጣ ያለውን ችግር፣ ሥጋትና መከራ ቀድማ የመጠርጠር ጸጋ ተሰጥቷታል፡፡ ከፊት ለፊቷ አደጋ፣ ችግር፣ መከራ፣ ሕይወቷን የሚያሰጋ ነገር መኖሩን ካረጋገጠች ‹ፍንክች የአባ ቢላ ልጅ› ከቆመችበት አትነቃነቅም፡፡ በለዓም እንዲህ አይደል የሆነው፡፡ እርሷ ሰይፍ የመዘዘ መልአክ ታይቷታል፡፡ እርሱ ግን እኛ እንደምናደርገው ‹አህያና ዱላ› እያለ ነረታት፡፡ እርሱ እጁን ደከመው እንጂ አህያዋ ግን ሐሳቧን አልቀየረችም፡፡ አጥኚዎቹ የደረሱበት የአህያ ጠባይ ይሄ ነው፡፡ ደኅንነቷ እስካልተረጋገጠ ድረስ በዱላ ብዛት አህያ ሐሳቧን አትቀይርም፡፡ እኛም ሐሳቧን ከመረዳት ይልቅ ዱላ ይቀናናል፡፡

    እንዲያውም ሊቃውንቱ እንደሚሉት አህያ ከፈረስ በላይ ታመዛዝናለች፡፡ መጀመሪያ በተሰጣት የመገምገም ችሎታ የአካባቢውን ደኅነት ትገመግማለች፣ ከዚያ ታረጋገጣለች፣ በመጨረሻም ትወስናለች፡፡ እኛ ግን ጥሎብን ይህንን እንድታደርግ ዕድል አንሰጣትም፡፡ መነረት ብቻ ነው፡፡ ለአህያ ግን ከደኅንነት የሚበልጥ ነገር የለም፡፡ የጥንት ሰዎች ‹በፈረስ የሚመጡ ጦረኞች፣ በአህያ የሚጡ ግን ሰላማውያን ናቸው› ብለው ያምኑ ነበር፡፡ ምክንያቱም አህያ ከፊቷ የደኅንነት ሥጋት እያለ እሺ ብላ አትንቀሳቀስምና፡፡ ክርስቶስም በዕለተ ሆሳዕና ከፈረስ፣ ከበቅሎና ከግመል ይልቅ በአህያ የሄደው ሰላማዊ መሆኑን ሊያበሥር ነው ይላሉ ሊቃውንቱ፡፡

    አህያ ‹ነገር በቀላሉ የማይገባው› ሰው ምሳሌ ሆና ስሟ ጠፍቷል፡፡ አንዱ ማይም ሊቁን ደደብ ብሎ ተሳድቦ ይከሰሳል አሉ፡፡ ዳኞቹ ተሰብስበው ሁለቱን ሲያካስሱ አንደኛው ዳኛ ይጠራሉ፡፡ ለጠሪውም ሰው ‹ጠብቀኝ ስም ተቀያይሮ እያስመለስን ነው› ብለው ላኩበት አሉ፡፡ አሁንም የአህያን ስም የሚያስመልስ ጠፍቶ እንጂ አህያ እንኳን ነገር የማይገባት አልነበረችም፡፡ አህያን ማስተማር ግን ፈረስና በቅሎ፣ ውሻና ድመት እንደማስተማር አይደለም፡፡ አህያ ሁለት ነገር ትፈልጋለች፡፡ አንድ አካባቢው ደኅናና ሰላማዊ መሆኑን፣ ሁለት ደግሞ የሚያስተምራት ሰው ለአደጋ የማያጋልጣት፣ ቢቻልም ከአደጋ የሚከላከልላት መሆኑን ማረጋገጥ፡፡ ይህንን ሳታረጋግጥ አህያ ለትምህርት ዝግጁ አትሆንም፡፡ ትምህርቱ የሚያበላ ነው ቢሏትም – መጀመሪያ ራስ ደኅና፣ ልብ ጤና – ትላችኋለች፡፡ ደግሞ ይግረማችሁ ብላ ይህንን በሂደት ነው የምታረጋግጠው፡፡ ቀደማ ባየችውና በሰማችው ነገር ምስጥ ብላ የምትቀር አይደለችም፡፡ ‹አካሄዱን አይታ ጭብጦውን የምትቀማ› ናት፡፡ እንደጀመርከው መጓዝህን፣ እንደተጓዝከው መጨረስህን ማረጋገጥ ትፈልጋለች፡፡ ይበልጥ ባረጋገጠች ቁጥር ይበልጥ የምታዛትን ትቀበልሃለች፡፡ ምን ዋጋ አለው ታድያ፡፡ ይህንን ማን ያውቅላታል፡፡ አልገባትም ብሎ ያልገባው ይነርታታል እንጂ፡፡ ይልቅ አህያ እንደ ብቸኝነት አድርጋ የምትጠላው ነገር የለም፡፡ ካገኘች ከሌሎች አህዮች ጋር፣ ካልቻለች ከፍየሎችም ጋር ቢሆን መኖርን ትመርጣለች፡፡ እንዲያውም አህያ ብቻዋን ከኖረች እድሜዋ በግማሽ ያጥራል ይባላል፡፡

    መቼም በሀገራችን እንደ አህያና የዝሆን ጆሮ የተቀለደበት ጆሮ የለም፡፡ አህያ ግን በረሐ ውስጥ እስከ 60 ማይል ድረስ የሌላውን አህያ ጩኸት መስማት የምትችል ፍጡር ናት፡፡ ዛሬ ዛሬ ጉርብትና እየጠፋ ጎረቤት ጎረቤቱን መስማት ባቆመበት ዘመን ወዳጁን ከ60 ማይል መስማት ከሚችል ፍጡር በላይ ምን ወዳጅነት አለ፡፡ የአህያ ጆሮ ይህ ብቻ አይደለም ጥቅሙ፡፡ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ተናገሩት የተባለውን ነገር የሚያረጋግጥልን ነገርም አለው፡፡ ንጉሡ ወደ ደብረ ዘይት ሲሄዱ የአየር ንብረት ዘገባ በሬዲዮ ይሰማሉ፡፡ ቀኑ ፀሐይ ነው የሚል ነው ትንበያው፡፡ ንጉሡም ይህንን አምነው ወደ ደብረ ዘይት ያመራሉ፡፡ መንገድ ላይ ግን አንድ ገበሬ አህያውን እያስሮጠ ሲሄድ ያዩታል፡፡ ንጉሡም ‹ምነው አህያዋን ታስሮጣታለህ› ይሉታል፡፡ ገበሬውም ‹ዝናብ ሊመጣ ስለሆነ ነው› ይላቸዋል፡፡ ንጉሡም ‹እንዴት ዐወቅህ› ይሉታል፡፡ ገበሬውም ‹አህያዋ ጆሮዋን ጥላለች› ይላቸዋል፡፡ እርሳቸውም ገርሟቸው ይሄዳሉ፡፡ እልፍ እንዳሉም የአየር ትንበያው የተናገረው ፀሐይ ቀርቶ ገበሬው የተናገረው ዝናብ መጣ ይባላል፡፡

    የአህያ ጆሮ የአየር ንብረትን በተመለከተ ለአህያዋ ሁለት ነገር ይጠቅማታል፡፡ በአንድ በኩል የውስጧን የሙቀትና የቅዝቃዜ ሁኔታ ለመጠበቅ ሲያገለግላት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የአካባቢውን የአየር ሁኔታ ገምግማ ርምጃ ለመውሰድ እንድትችል ያግዛታል፡፡ አህያ እንደነፈረስ ዝናብ የሚችል ቆዳ የላትም፡፡ ያላት ዝናብ መምጣቱን ዐውቆ እንድትጠለል የሚመክር ጆሮ ነው፡፡ ከፈጣሪ ካገኘችው አደጋን ቀድማ የመገመት ችሎታ ጋር ተጨምሮ ጆሮዎቿ የአካባቢውን ቀጣይ የአየር ሁኔታ ዐውቃ ሰውነቷን ለማዘጋጀት እንድትችል ያደርጓታል፡፡ የደብረ ዘይቱ ገበሬም ይህንን ነገር ነው የደረሰበት፡፡

    ባይሆን አህያ በሆዳምነት መታማቷ እውነት ሳይሆን አይቀርም፡፡ አህያ እስከ 40 የሚደርሱ ጨጓራዎች እንዳሏት ስትሰሙ ኡኡ ማለታችሁ አይቀርም፡፡ የአሁኑ ይባስ እንድትሉ ሁለት ነገሮች እንጨምር፡፡ አህያ በእድሜ በገፋች ቁጥር የጨጓራዋን መጠን እየጨመረችው ትሄዳለች፡፡ እድሜ ለዐርባ ጨጓራዎቿ 18 ኪሎ ካሮት እምሽክ ለማድረግ አንድ ሰዓት አይፈጅባትም፡፡ እስካሁን በአህዮች ታሪክ ከፍተኛውን ጨጓራ ያስመዘገበችው የኡዝቤክስታን አህያ ናት፡፡ 59 ጨጓራ አስመዝግባለች፡፡ አንድ አህያ እግዜርን ካልፈራች 2722 ኪሎ ምግብ በዓመት ትፈጃለች፡፡ እንኳን የሸመተ ያረሰም አይችልሽ ማለት አሁን ነው፡፡

    የአህያን መሥዋዕትነት ብነግራችሁ ግን ‹ትብላ፣ ደግ አረገች› ትሏታላችሁ፡፡ የአህያ መንጋ የቡድን መሪ አለው፡፡ ጠርጣራዋ አህያ አደጋ ሊመጣ መሆኑን ከጠረጠረች አካባቢዋን ታስሳለች፡፡ ቀጥላም የአደጋውን አቅጣጫ ታረጋግጣለች፡፡ ከዚያም አደጋው በመጣበት በኩል ራስዋን ታሠማራለች፡፡ በመጨረሻ አደጋውን ትጋፈጣለች፡፡ የአህያ መሪ አደጋውን ስትጋፈጥ ሌሎቹ በቂ ጊዜ አግኝተው ከአካባቢው ይሸሻሉ፡፡ በመሪዋ መሥዋዕትነት ሌሎቹ ይተርፋሉ፡፡ መሪ ማለት እንዲህም አይደል፡፡ ራሱን ሠውቶ ሕዝቡን የሚታደግ፡፡ የአህያ መሪ ይስጠን፡፡

  • Anonymous commented on May 11, 2018 Reply

    ይገርማል

  • Anonymous commented on October 3, 2018 Reply

    i like the comment

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...