Tidarfelagi.com

ላንችይቱ

[Come out of the circle of time and into the circle of love. ~ Rumi]
~
ምንኛ ነው ግን… ‘የነገን ማወቅ ፈለግሁኝ’ ብሎ ምኞት… ዛሬ ላይ ሳይቆሙ ወደ ነግ መጎተት… የሚያውቁትን ጥለው በማያውቁት መሳብ… ምንኛ ነው ‘ነገን ላየው እጓጓለሁ’ ማለት… ከአሁንታ ተፋትቶ ካልመጣ ጋር ትግል… ባልነበረ ጭንቀት…

ውዴ… እኔ አንቺን ስወድሽ ዛሬዬን ብቻ ነው… አሁኔን!! … በጭራሽ ዘላለሜን እወድሻለሁ ብዬ አልዋሽም… ዘላለሜ አሁን ናት… እርግጠኛዋ ዘላለም… “ትናንት – ዛሬና – ነገዬን” የሸከፈች ቅጽበታዊት ሁለንታ… እውነቱን ልንገርሽ… በጊዜ ምህዋር ውስጥ ዘላለም የሚባል ስፍር የለም… አሁን ነው ዘላለም… አዕምሮ ነው ሰውን ከአሁኑ አፋትቶ ሲያበቃ ዘላለምን የሚያስቃዠው…

ማነው እርሱ ነገን እንዲኖር ተስፋ የተሰጠው… የሕላዌ ቃል የጨበጠ… ‘የዘላለሜነሽን’ አስረግጠው የነገሩት… ከተስፋው በስተቀር… ከእኖራለሁ ጉጉቱ ውጪ… ውዴ እኔ በተስፋ አልወድሽም… ተስፋ የምናልባት ዓለም ነው… ልቤ በምናልባት አትወድም የኔ ቆንጆ… አሁኔን ነው የምወድሽ… ከትናንት ይልቅ ብወድሽም ከዛሬ በላይ ስለመውደዴ ግን እርግጠኛ አይደለሁም… አዎን.. በደረስኩበት ቆሜ ያልነገርኩሽን ፍቅር ከማላውቀው ነገ አትጠብቂው…

ደግሞ ‘እፈራለሁ’ አትበይኝ… አሁን ውስጥ ፍርሃት የለም… በገና ውስጥ እንጂ… በምን ይፈጠር ነገ ውስጥ… እኔ እዚህ ነኝ… አሁን ውስጥ… ነገን እንዴት አውቄው ልስጋ… ኤመርሰን “ፍርሃት ካለማወቅ ማህጸን ይወለዳል” ይላል… ፍርሃት የአሁን ጸባይ አይደለም… የነግ ኮተት ነው… ነገ ምን እንደሚፈጠር ባለማወቅ ስጋት የሚፈጠር ቅዠት… ድሮስ ነገን ማወቅ ከቶ ምን ይረባል… ከአሁን ጋር ሳይዋቡ በይመጣል ቅዠት መቧቸር ምን ይፈይዳል… ‘ነገ ለራሱ ይጨነቅ’ የኔ ውድ…

አሁን ውስጥ ልቤ አልገባችሽም?… መውደዴ አልተዋጠሽም?… እርሱን ጠይቂ… አሁን ያላመንሽው መውደዴ ነገ አይኖርም… ‘ዛሬን የሌለ ለነገ አይደርስም’

ይልቅ… ‘ቆይ ኋላ’ ብዬ ያዘገየሁት እውነት ያለ ይመስልሽ ይሆን?… የሰሰትኩብሽ መውደድ… የቀነስኩብሽ ፍቅር… እንዲያ ተሰምቶሽ ይሆን?… እንኪ እንግዲያው… ነገ የሌለው መውደድ የኔ ውድ… ያልተሰሰተ… ያልተቆጠበ… ያልተሸረፈ…

ጥሪት ሲቆጥቡ ‘ካለሁ እጠቀመው ባልኖርም ለልጄ’ ተብሎ ነው… ፍቅር ሲቆጠብስ የኔ ውድ… ማን ስለኔ ይወድልኛል ብዬ ልቆጥብ… በፍቅር ውስጥ ትክክለኛ የሚባል መጪ ጊዜ የለም እኮ … አሁን ብቻ ነው ትክክል… አሁን ነው ሁለዜ… ለፍቅር ደግሞ ሁለዜም ትክክለኛ ጊዜ ነው…

እናም አሁንታችንን እንዋብ ውዴ… እስኪ አሁን ውስጥ በተጋራነው ነገር ደስ ይበለን… ዛሬ ደስ ካለሽ – ያ በቂ ነው… ዛሬ ፍቅር ከተጋራሽ – ያ በቂ ነው… ‘ነገ ባጣውስ’ እያልሽ ግን ፍቅርሽን አትሰስቺ… ‘ልቤን ሰጥቼው ቢሰብራትስ’ ብለሽ ግን በስጋት ውስጥ አትመላለሺ… ፍቅር በፍጹም ልብ እንጂ ‘በጥንቃቄ’ አይለገስም… በነፃነት ይቃኛል እንጂ ‘በመጠባበቅ’ አይጸናም…

ሌላ መስመር…

የዛሬሽን እውነት ባረጀ መነጽር አትፈትሺ… እልፊትን በነባራዊው ዓይን አትመዝኚ… ትናንት በድካም ስለተፈታ ዛሬ ከትጋት አይቀርም… ትናንት የተሰበረው ‘ኢጎ’ ነው… ትናንት የተወሽ ስሜት ነው… ፍቅር አይደለም… ፍቅር በሁኔታዎች ከፍ ዝቅ ውስጥ አይለዋወጥም… ብቸኛው ጽኑ ነገር እርሱ ብቻ ነውና…

አዎን ዛሬዬን እወድሻለሁ… አሁኔን… በዚህች ቅጽበት ውስጥ ሆኜ ከልቤ እወድሻለሁ… ውድድድድድድድ

የእንግሊዛዊቷን Vashti Bunyan ውብ የሙዚቃ መስመሮች ተጋሪኝማ…
.
I don’t say I’ll love you forever, baby
I don’t say I’ll love you forever
But I know that I love you now
.
Dunno what tomorrow will bring, baby
Dunno what tomorrow will bring
But I hope it can be like now
.
When you’re near me
I want it to stay that way
But if a new dawn breaks
Please understand, baby
.
I can’t say I’ll love you forever
Though I want to love you forever
I can only say that I love you now.
_______________
መልካም አሁን የኔ ውድ 

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...