‹‹እንደ አንቺ አንድ ቦታ የበቀልኩ ባሕር ዛፍ ሳልሆን እንደ ኮባ ውላጅ የተሸከረከርኩ ነኝ፡፡››
03/07/79
ለፅጌሬዳ ሐብታሙ
ፓ.ሣ.ቁ 0000
አዲስ አበባ
ለጤናሽ እንደምን ከርመሻል? ሦስት ሳምንቶች ያህል ከጠፋሁብሽ በኋላ በዐይነ ስጋ ሳይሆን—እንዲህ በወረቀት፣ በቀለም፣ በሆሄያት፣ በፓስታ ላናግርሽ መሆኔ ግራ ሳይሆንብሽ አይቀርም፡፡ ግን በማይተዋወቁ ሰዎች መሃል የሚጥም መግባባት ሊኖር አይችልም፡፡ እንደ ስዕል ቀለም ፊደላትን ማዘዝ ባልችልም …… ላዋይሽ የምፈልገው ጉዳይ ዕንብርቱ ላይ ማነጣጠር ባልችልም…… ሽታው እንዲደርስሽ ለማድረግ እሞክራለሁ፡፡
ስለአንቺ ያለኝን ርዕዮት የፈጠርኩበት መንገድ የከረመና ረዥም ነው፡፡ አንቺን ያወቅሁሽ ከአንቺ ጋር ከመጀመሬ በፊት ነው፡፡ ልጅ እያለሁ፣ ጎረምሳ እያለሁ፡፡
አባቴ አናጢ ነበር፡፡ (ይህ አይነት አጀመመር እንኩዋን ጥሩ አልነበረም፣ ይሁን ግን)
ዕድሜዬ አሥር አካባቢ ሲሆን ረዥም ሕንጻ ከሚጠግንበት ርብራብ ላይ ወድቆ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡ በዚህች አንዲት ገጠመኝ የተነሳ ሁለት ዐይነት አባቶች አወቅሁ፡- በሕይወት እያለ— እንጨት የሚልግ፣ ድንጋይ የሚቀጠቅጥ እና ሞቶ የፊቱ ቆዳ የደረቀ፣ የፅድ ሳጥን ውስጥ የተሰነቀረ……
ከባድ ዕውቀት ነው፡፡ ልጅ ከሆኑ ደግሞ ሕሊና ውስጥ ተጠብሶ ይታተማል፡፡
ሳይዘገይ እንጀራ አባት መጣ—አሥረኛ አመቴን አልፌ፡፡
አንቺ ባለ አንድ አባት ነሽ፡፡ እኔ ሁለት አባት ነበረኝ…… ሁለት እናትም፡፡ ሁለት እናት ለምን አልኩሽ? ምክኒያቱም እናቴ ተለወጠች፡፡ እናት ይለወጣል፡፡ በባልዋ ላይ የተደገፈች ስለነበረች (ከገንዘብ እስከ ወሲብ) የባልዋን አስተያየት መያዝ ነበረባት፡፡ ተቃወመች፡፡ መደሰቴን ተቃወመችኝ፡፡
አሥራ አንድ አመቴ ነበር ……
የአባቴ ወንድም አጎቴ መሰቃየቴ አሳዝኖት ይሁን በኋላ በሰማይ ለሚወርሰው ቦታ አስቦ ወደ ቤቱ ወሰደኝ፡፡ አሁን ሲያወራ ‹ሰው ያደረግኩት እኔ ነኝ› ይላል፤ የኑሮ ነገር ትንሽ እንደቀናኝ ሲያውቅ፡፡ በየመሃሉ ትንሽ ‹ተሳስቼ› ሳበሳጨው ‹አንተን ለማምጣት ሞላሌ የወረድኩበትን እግሬን ጎላ ሚካኤል በሰበረው› ይለኝ እንዳልነበር፡፡
አዲስአባ ለትምህርት ስመጣ አጎቴ በፖስታ ያልታሸገ የአደራ ደብዳቤ ጽፎ ወደ ዘመድ መራኝ፡፡ እነዚህ ዘመዶቼ መልካቸው እንጂ ነጠላ ፀባያቸው ከአባቴ፣ ከእንጀራ አባቴ፣ ከአጎቴ ጋር የሚቀራረብ ነበር፡፡
— ሁሉም ተመሳሳይ ለኾነ ነገር ይሥቃሉ (የሚለዩበት ነገር ቢኖር አንዱ ገጣጣ ወይ አንዱ ድዳም ይሆናል)
— ሁሉም ምላስ አላቸው (ቡና ይጠራሩበታል፣ ያሙበታል፣ ያሽሟጥጡበታል፣ ይሳደቡበታል)
ላውቃቸው ግን ተስፋ አልቆረጥኩም፡፡
ዕድሜዬ 16 ደረሰ ፍቅር ጀመርኩ (እንዲህ ስል አትቀኚም? ያለፈው ታሪኬን እንኳን ለመቀማት የምትገደቢ አይመስለኝም፡፡ ቅኚ)
ፍቅር ጀመርኩ፡፡ ደብሪቱ ትባላለች (ረካሽ? ስሟ የባላገር ስለኾነ፣ አንቺን ስላልበለጠችሽ? ራሴን አጠቃሁ መሰለኝ፡፡ ነጥብ ልቁጠርልሽ፡፡ አንድ)
ደብሪቱ ገረድ ናት፡፡ የዘመዶቼ ገረድ (ደስ አለሽ አሁንም? ወደ ገረድ ስለወረድኩ? ሁለት፡፡ ለአንቺ ነጥብ፡፡)
ደብሪቱን የወደድኩበት ምክኒያት ነበረኝ፡፡ ዘመዶቼ በትዕቢታቸው አገለልዋት፣ ያልተገራ ጎንደሬ አንደበትዋን እያሽሟጠጡ፣ እንዳታውቃቸው ከሩቅ ሲያባርሯት፣ በገረድነትዋ አገሸሽዋት፣ ግድግዳ ተለጥፋ የሚያምሩ ዐይኖችዋን ስታንከባልል ሳይ ለእስዋ በማዘን፣ በእነሱ ላይ ፀባይ ወይም ጉራ በመናደድና እልህ በመግባት ልወቃት አልኩ፡፡
እንድ ቀን ማታ ወደምትተኛበት ክፍል በቀስታ እየተራመድኩ ገባሁ . . . . . . አስተኛኘትዋ፡ ድርና ማጉ ብቻ የቀረ ከለአንሶላ የምትለብሰው ብርድልብስ ከላይዋ ተንሸራቶ ወርዶአል፡፡ የተኛችው በጀርባዋ ነው፡፡ አፍዋ በትንሹ ተከፍቶአል፡፡ አንድ እጅዋ ወደ መሬት ተንጠልጥሎአል፡፡ ጡቶችዋ ወደ ላይ ቆመዋል፡፡ ትንፋሽዋ አይሰማም . . . . . .
. . . ፅጌሬዳ . . . . . .
ውበትዋን መቋቋም ባልችልም . . . . . .
ነፍሴ ለሁለት ተከፈለች፡
እንደኛዋ እንዲህ አለችኝ፡ . . . . . . ተኛት፣ ተኛት፣ ተኛት፡፡
ሁለተኛዋ እንዲህ አለችኝ፡ . . . . . . ከዚህች ጋር አቤት ውርደት . . . . . . ቅሌት፣ ልክስክስ ጣሳ ጣሳውን ይለቅማል፣ ምንም ከማይታወቅ፣
አንደኛዋ አሁንም እንዲህ አለችኝ፡ ሰው ናት፣ ውብ ናት፣ ተኛት
በዚህ ፍተጋ መሐል አንድ የዘመዴ ልጅ ገባች፡፡
ያየችኝ አስተያየት . . . . . . ሁሉም ሴት በሚያይበት (አንቺም) . . . . . .
እኛ አለንልህ አይደለም፡፡ ሁልቀን የምንታጠብ፣ ምን ዓይነት ሽቶ ትፈልጋለህ? ይሔን ቁመና ይዘህ . . . . . . ይሔን ጥርስ፣ ይሔን ዐይን ይዘህ የትኛዋንም ሴት የሚያማልል (አትቅኚ አይዞሽ፡፡ ምንም ነገር አላደረግኋትም)፡፡
በሌላ ቀን ስገባ ልክ እንደመጀመርያው ቀን ተኝታ አገኘኋት፡፡
ላውቃት ፈለግሁ፡፡ (እዚህ ላይ መቼም አይምራትም በሚል ትንፋሽሽ ከአሁኑ ቁርጥ ቁርጥ ማት ሳይጀምር አይቀርም)
መጀመርያ መንካት ፈራሁ፡፡ እግሮችዋን ስታነቃንቅ ብርድ ልብሱን በሙሉ ከላይዋ ላይ ገፍታ ጣለችው፡፡ አንበርክኮ የሚያፀልይ ውበት አላት፡ ከዓሳ የተቀዳ ጠይምነት፡፡ የወደቀው ልብሷን ላለብሳት ስሞክር ተንቀሳቅሳ አንድ ዐይንዋን ገልጣ ፊትዋን ወደ እኔ አዞረች፡፡ ዳበስኳት፡፡ ወደ ጀርባዋ ገለበጥኳት፡፡ እንዳረኳት ሆነች፡፡ ዳበስኳት፡፡ እስኪበቃኝ ዳበስኳት፡፡ ዕንባ በዐይኖቼ ሽፋሽፍቶች ላይ ሲንጠለጠል ተሰማኝ—ሊወድቅ፡፡ ገላዋ እንደ ነብር ጅራት መወራጨት ጀመረ፡፡ ለቅሶ በጀመረው ድምጽ ወደ ደረትዋ እያስጠጋችኝ ትስመኝ ጀመር፡፡
በዚያች ቀን ብቻ አረገዘች፡፡ (አትቅኚ)
ያ ቤት ተናወጠ፣ ከኮርኒሱ እስከ ውሐ ልኩ፡፡ ሊተፉብኝ ምንም አልቀራቸውም፡፡
ከዚህች ልጅ ጋር አድንቄአት ተኛኋት እንጂ ስለ እሷ ብዙ የማውቀው ስለእኔ ብዙ ያወቀችው ነገር አልነበረም፡፡ ከራርሞ ግን በሰው ቤት እንደሚስት ሊያደርጋ ከጀላት፡፡
እሷን ማስረገዜን ያዩ የቤት ውስጥ ልጃገረዶች . . . . . . ጥቅሻቸውን ቢገቱም ነገር መዘምዘማቸውን አላቆሙም፡ ‹ልክስክስ› ‹ወራዳ› ‹አቅሙን አያውቅ› ‹ደደብ› ‹አህያ› ‹ከብት› ‹ጅል› ‹ጣሳ› (ከጀርባዬ ደሞ በትንሹ እንዲሰማ አድርገው፡- ‹ከአናጢ ልጅ ምን ሊጠበቅ›) እነዚህን ሁሉ ቃላት በተለያየ አገባብ እንድደነብርባቸው አድርገው በዐረፍተ ነገሮቻቸው ውስጥ በተለያየ መልክ እያዋቀሩ አመጧቸው፡፡
ጥርሴን ነከስኩ፡፡ አወቅሁ፡፡
ዕድሜዬ 18 ነው . . . . . .
ገረድዋ በወሊድ ሞተች፣ ልጁም አልቀረም፡፡
አሁንም ራሴ ውስጥ የዘነጋሁት ትግል መጣ . . . . . .
አንደኛው፡ እሰይ ተገላገልኩ . . . . . . ከገረድ የተገኘ ልጅ መሰደቢያ ነበር፡፡
ሁለተኛው፡ ለአንተ ክብር ብለህ (አለመከበርም ሊኖር ይችላል) ሰው ነፍስ እንኳን አለፈ ትላለህ? እሷን ባታውቃትም . . . . . . ምክኒያት ሆናህ እሷንም ሌላውንም ሰው አሳይታሃለች (ይሔን ክርክር ግን ሲዘገይ ረሳሁት)
እሷ ከሞተች በኋላ እዚያው ቤት ትከጅለኝ የነበረችውን ደብሪቱ መኝታ ቤት እጅ ከፍንጅ የያዘችኝን (እላይ ሳልጠቅሰው ስላለፍኩ ይቅርታ እጠይቃለሁ) ያገኘችኝን ልጅ ተኛኋት፡፡ ያው ናት፡፡ ሦስት ነበሩ፡፡ ሦስቱንም ተኛኋቸው፡፡ ያው ናቸው፡፡ ሥጋ ናቸው፡፡ አሠራራቸው በመጠኑ ቢለያይም፡፡
ሃያ አመቴ ሆነ፡፡
እዚህ እነገርኩሽ ቤት ውስጥ ያሉ ሴቶች በሙሉ አንዲትም ሳትቀር ከሌላ ሴት ጋር የማደርገውን ግንኙነት ይከታተሉኝ ነበር፡፡ መኝታ ቤት ገብተው ፎቶግራፍ፣ ወይ ደብዳቤ ይገኝ እንደኾነ ብለው ዕቃዎቼን ምክኒያት እየፈጠሩ ይበረብሩኛል፡፡ ግን ይሔ ለሴት የጻፍኩት የመጀመሪያዬ ደብዳቤዬ ነው፡፡ ለአንቺ እፅፋቸው የነበሩትን ማስታወሻዎች (Memos) ትተሸ፡፡
እንደ አንቺ አንድ ቦታ የበቀልኩ ባሕር ዛፍ ሳልሆን እንደ ኮባ ውላጅ የተሸከረከርኩ ነኝ፡፡
ከእነዚህ ሴቶሽ ምንሽ ይለያል? አስቢ! መልካችሁ፣ አወላለዳችሁ ላይማሰል ይችላል፡፡ እነኚህን ሴቶች ያወቅኋቸው ገና በ18 አመቴ ነበር፡፡ አሁን ሰላሳ ሰባተኛዬ ውስጥ ነኝ፡፡ ባንቺና በሌሎች በተኛኋቸው ሴቶች መሃል ልዩነት አላየሁም (ትንሽ ላጋንና)፡፡ ዲግሪሽን፣ ዲፕሎማሽን (የትኛው እንደኾነ ሳልረሳው አልቀርም) መኩራሪያ ብታደርጊው እንኳን የተለየሽ ትልቅ ወይዘሮ ወይም ወይዘሪት አያደርግሽም (አንዱን ምረጪ)፡፡
አንድ እሁድ እንገናኝ ስልሽ ከጓደኞቼ ጋር በየወሩ የገብርኤል ማሕበር አለብኝ አላልሽም? ይህን ዘመናዊ ሰንበቴሽን “get together” ነው ያልሽው? በአንቺ ቤት አውሮፓዊ (ስልጡን) ያደረግሽው መስሎሽ ነው፡፡
በሙሉ ያልታደላችሁ፣ ያልሞላላችሁ ያልተዳራችሁ የቤት እመቤቶች ናችሁ፡፡
…ከአለንጋና ምስር…