ከበር እንደገባሁ፣ ልክ እድሜ ልክ ሳደንቀው እንደኖርኩ ታዋቂ ሰው ሳየው ተንሰፍፌ አብሬው ‹‹ሰልፊ›› የተነሳሁት ከሰፋፊ ቅጠሎች ጋር ነው። እነዚህ ቅጠሎች በልጅነታችን ከደጃፋችን እንደዋዛ ቀጠፍ አድርገን ለጢባጢቢ የምንጠቀምባቸው ነበሩ።
እዚያ ጋር እንደ ብርቅ መአድን የምነካካው ዛፍ ልጆች ሳለን ከሰው ግቢ ገብተን አውርደን እየበላን ቤቶቻችን ከጎረቤት ጋር ንተርክ ውስጥ የምንከትበት የሆምጣጤ ዛፍ ነው።
እዚያ ጋር አይኖቼን በትዝታ እንባ ያስቀረረው እጅብ ብሎ የበቀለው ነገር በልጅነታችን ጥፋት ስናጠፋ ፍዳችንን የምናይበት መገረፊያችን የሳማ ቅጠል ነው።
እዚያ ጋር ያሉት ለአይን የሚስቡ ብርቱካንማ ሾጣጣ አበቦች በየእለቱ ትምህርት ቤት ስንሄድ መንገድ ላይ አግኝተን የምንመጣቸው ባለማር አበቦች ናቸው።
የኮባ ተክሉ ወንድሞቼ ክረምት በመጣ ቁጥር ዘንጠል እያደረጉ ‹‹ጠመንጃ› ሰርተው የሚፋለሙበት ተራ ዛፍ ነው።
በስተግራ በኩል ያየነው ለዛሬ አይን እንግዳ የሚመስል አጭርና ወፍራም ዛፍ መሰል ተክል ስንራገጥ በወደቅን እና በቆሰልን ፣ እምባችንን እያዘራን ቤት በመጣን ቁጥር እናቶታችን ‹‹ጠባሳ እንዳይሆን›› ብለው የሚቀቡንን ‹‹ፊጪጭ የሚል›› ነገር ይዞ የሚበቅል የሬት ተክል ነው።
እዚህ ግቢ ፈዝዘን የምናያቸው ቤቶች ቄንጠኛ ይሁኑ እንጂ ያደግንባቸው፣ የኖርንባቸው የጭቃ ቤቶቻችን ናቸው።
ለዛሬ ልጆች ማየትም ሆነ መንካት፣ መመገብና ማጫወት ከዱር አውሬ ጋር እንደዋሉ ብርቅ የሚሰራባቸው እነዚያ ጋር የምትመለከቷቸው እንሰሳት ምን መሰሏችሁ? …የወተት ላሞች ናቸው። እኛ ቤት ባይኖሩ ከቤታችን ዝቅ ወይ ከፍ ብለው ያሉት ባለ ወተቷ ሴትዮ ቤት የነበሩ ላሞች።
አዚያ ጋር ደግሞ ፈረንጅና ኢትዮጵያውያን ህጻናት ከበው የሚያዩያቸው በእኛ ጊዜ በየደጀሰላሙ ቅጥር ግቢ እንደልብ እናገኛው የነበሩ፣ ብሎም ሰው አየኝ አላየኝ ብለን እየተገላመጥን በጨርቅ ጠቅልለን ቤታችን እናመጣቸው የነበሩ ኤሊዎች ናቸው።
እንደው ባጠቃላይ ዛሬ ላይ እንዲህ የሚያስደምመን፣ አይናችንን የሚያጠግበው አትክልትና አበባው የዛን ጊዜየጓሮ አትክልታችን፣ አረንጓዴው መስክ ደግሞ መራገጫ ሰፈራችን ነበር።
አሁን ግን ይሄ ሁሉ ነፃ ሃብታችን ድንቃድንቅ ነገር ሆኖ ቤተ መዘክር ገብቷል።
ቀልዴን አይደለም።
ትላንት በዝና የማውቀው ዞማ ቤተመዘክር ሄጄ ነበር።
እውነቴን ነው፣ ለሁለት አስርት አመታት ያላየኋትን የልጅነቴን አዲስአበባ ቤተመዘክር ሆና አገኘኋት።
ግን ቤተመዘክር ውስጥ ሆና ያገኘኋት፤ የጢባጢቢ እና የሳማ ቅጠል፣ የኮባ ዛፍ፣ የሆምጣጤ ዛፍ፣ የሬት ተክል፣ የጭቃ ቤት፣ የጓሮ አትክልት፣ ዶሮ ማርቢያ እና የላም በረት ይዛ እንጂ ሌላ ከመቶ አመት በላይ ያስቆጠረ ታሪካዊ ቅርስ ይዛ አይደለም።
እርግጥ ነው፤ በዚህች የአይን ማረፊያ ባጣች የዛሬዋ ውጥንቅጥና ጩኸታም አዲስአበባ ይሄን የመሰለ ‹‹ቤተ መዘክር›› ማግኘት የላቀ ደስታን የሚሰጥና ውብ የእፎይታ እድል ነው። ተለፍቶበታል፣ ተደክሞበታል። ለአሰናዱትም ሰዎች ምስጋና ይገባል።
ግን ገረመኝ። ‹‹ዛፍ የሌባ መደበቂያ ነው፣ ዛፍ ኋላ ቀርነት ነው›› እያለልን ከተማችንን በሲሚንቶ እና በብሎኬት ክምር አስጨንቀን፣ ብዝሃ ሕይወትን ድራሹን ከማጥፋታችን የተነሳ ፤ በልጅነታችን ከደጃፋችን የነበረን ተራ ነገር ለማየት፣ የአፍታ እፎይታና ፀጥታን ለማግኘት፣ የጥሞና ጊዜ ለመሸመት በገዛ ከተማችን በቆመ ‹‹የድሮ አዲስአበባ›› ቤተመዘክር መቶ ብር ከፍለን ለመግባት ስንሰለፍ ግን ክፉኛ ገረመኝ። የሚበልጠውን ባለማስበለጣችን ለፀጥታም ሆኖ ለአረንጓዴ ስፍራ ገንዘብ መክፈላችንን ሳስብ ትንሽም ከፋኝ።