ረመዳንን የሚጾም ሰው ስለ“ለይለቱል ቀድር” ማንነት በሚገባ ያውቃል ብዬ እገምታለሁ። “ለይቱል በድር”ን ግን ብዙዎቻችሁ ላታውቁት ትችላላችሁ። ስለዚህ በዛሬው የረመዳን ወጋችን “ሀረር ጌይ” በተሰኘው መጽሐፌ ስለ “ለይለቱል በድር” የጻፍኩትን አጋራችኋሁ።
*****
“በድሪ” እና “በድሪያ” እኔ በተወለድኩበት አካባቢ በጣም ከሚታወቁት ስሞች መካከል ይገኛሉ። በነዚህ ስሞች የሚጠሩትን ሰዎች ለምን እንዲህ እንደተባሉ አንድም ቀን ጠይቄአቸው አላውቅም። ወደ ሀረር ከመጣሁ በኋላ ግን ነገሩን በቀላሉ ተረድቼዋለሁ። ለዚህም የረዳኝ “በድሪ በሪ”ን ማወቄ ነው። እንዴት… ወጋችንን እንጀምር እንግዲህ።
*****
በሀረሪ ህዝብ ትውፊትና ባህል ከፍተኛ አክብሮት ከሚሰጣቸው ህዝባዊ በዓላት መካከል አንዱ “በድሪ አያም” (ለይለቱል በድር) ይባላል። ይህ በዓል የሚውለው በረመዳን ወር 17ኛው ቀን ነው። በዓሉ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ከጥቂት ባልደረቦቻቸው ጋር ሆነው በሶስት እጥፍ የሚበልጧቸውን ጠላቶቻቸውን በድር በሚባለው አምባ ላይ ድል ያደረጉበትን ኩነት ለማሰብ ተብሎ ነው የሚከበረው።
ሀረሪዎች በዘመናችን “በድሪ አያም”ን የሚያከብሩት በየቤታቸው ነው። በጥንቱ ዘመን ግን መላው የሀረር ጌይ ህዝብ የሚሳተፍበት ክብረ በዓል በየዓመቱ በ“በድሪ በሪ” ይካሄድ ነበር።
*****
አዎን! በአማርኛ ስሙ “ቡዳ በር” የሚባለው ደቡባዊው የሀረር በር በከተማዋ ባህል ከፍተኛ ቦታ በሚሰጠው “በድሪ አያም” ስም ነው የተሰየመው ። የዚህ በዓል ዋነኛ ማዳመቂያ ደግሞ “በርቲ በርቲ” የሚባለው ጨዋታ ነው። ይህ ጨዋታ ከ“በድሪ በሪ” ፊት ለፊት ባለው አነስተኛ ሜዳ ላይ ይካሄዳል። ለመሆኑ “በርቲ በርቲ” ምንድነው?
“በርቲ በርቲ” ቃል በቃል ሲፈታ “ብትር ለብትር” ማለት ነው። በዚህ ስያሜ የሚጠራው የጥንቱ የሀረር ጌይ ወጣቶች ችሎታና ጉልበት የሚፈተሽበት የዱላ ምክክቶሽ ጨዋታ ነው። በጨዋታው የሚሳተፉት ያላገቡ ወጣቶች ብቻ ናቸው። ታዲያ ወጣቶቹ “በርቲ በርቲ”ን ሲጫወቱ “ቀላ በሪ” እና “በድዳ በሪ” በሚባሉ ሁለት ቡድኖች ይቧደናሉ። 5
በነገራችን ላይ “ቀላ በሪ” በአማርኛ “የቆላ በር” በር ማለት ነው። ይህ ስያሜ በሀረር ጌይ ሰሜናዊና ምስራቃዊ አቅጣጫዎች በሚገኙት ቆላማ ስፍራዎች ትይዩ ያሉትን ሶስት የከተማዋ በሮችን ማለትም “አስሱም በሪ”ን፣ “አርጎብ በሪ”ን እና “ሱጉድ አጥ በሪ”ን በአንድነት ያመለክታል።
በትውፊትና በአንዳንድ የጽሁፍ መረጃዎች እንደሚወሳው “ሀረር ጌይ” ከአካባቢዋ ማህበረሰቦች ጋር የነበራት ግንኙነት ተጠናክሮ በሚገኝበት ዘመን ከቆላማው የምስራቅ ኢትዮጵያ ክልል የሚመጡ ባለጉዳዮች የሚገለገሉበት ዲዋን (ፍርድ ቤት) “ቀላ በሪ” በሚል ስም ተቋቁሞላቸው ነበር።
“በድዳ በሪ” ደግሞ የ“ደጋ በር” ማለት ሲሆን ይህም የ“አስማእዲን በሪ” እና የ“በድሪ በሪ” የጋራ ስም ነው።6 እነዚህኛዎቹ በሮች ደግሞ በደጋማው የምስራቅ ኢትዮጵያ ክፍል ባሉት የሀረር ጌይ ተጎራባች ክልሎች አቅጣጫ ስለሚገኙ ነው እንዲህ የተባሉት። ከደጋማዉ የሀረርጌ አውራጃዎች የሚመጡ ማህበረሰቦችም በነዚህ በሮች ወደ ከተማዋ ይገቡ ነበር። አሚሩ ከነዚህኛዎቹ ማህበረሰቦች ጋር በነበረው ግንኙት መሰረትም እነርሱን ብቻ የሚያገለግል ሌላ ዲዋን “በድዳ በሪ” በሚል ስያሜ አቋቁሟል።
*****
ከላይ ከጻፍኩት ትንተና እንደምትረዱት የሀረር ጌይ ወጣቶች “በርቲ በርቲ”ን ሲጫወቱ የ“አስሱም በሪ”፣ የ“አርጎብ በሪ” እና የ“ሱጉድ አጥ በሪ” ልጆች “ቀላ በሪ” በሚባለው ቡድን ውስጥ ይካተታሉ። የ“አስማእዲን በሪ” እና የ“በድሪ በሪ” ልጆች ደግሞ “በድዳ በሪ” በሚባል ቡድን አንድ ላይ ይጠቃለላሉ።
ወጣቶቹ “በርቲ በርቲ”ን የሚጫወቱት በ“በድሪ ኦርቲ” (የበድር ምሽት) ነው። ይህም “በድሪ አያም” የሚጀምርበት ምሽት ነው። በጨዋታው ላይ የሚሳተፉት ወጣቶች በነጠላና በቡድን የሚደረጉ የዱላ ምክክቶሽ ግጥሚያዎችን ያደርጋሉ። ጨዋታውን የሚዳኙት ደግሞ በህዝብ የተመረጡ ሽማግሌዎች ናቸው።
ወደ ጨዋታው የገባ ተጫዋች ብልሀቱንና ቅልጥፍናውን በማሰባሰብ ተጋጣሚው “በቃኝ” ብሎ እጁን እስኪሰጥ ድረስ በዱላ ይከተክተዋል። እያንዳንዱ ተጫዋች በጨዋታ ላይ እያለ ድንገት ቢፈነከት አንዳች ስሞታ ለማቅረብ አይችልም። ህመሙን ችሎ መጫወት ከቻለ ጨዋታውን መቀጠል ይችላል። ካልሆነም “ፎርፌ” ሰጥቶ የመገላገል መብት ነበረው።
በ“በርቲ በርቲ” ጨዋታ አሸናፊ የሚሆነው ቡድን ደስታውን ለመግለጽ ሀረር ጌይን በዜማና በ“ዚክር” ከዳር እስከዳር ያዳርሳታል። በመንገዳቸው ላይ የሚያጋጥሟቸው ሽማግሌዎችም “እድሜያችሁ ይርዘም! ውለዱ ክበዱ!” በማለት ምርቃት ያዥጎደጉዱላቸዋል።
*****
በወጋችን መጀመሪያ ላይ እንደገለጽኩት ከ“በድሪ በሪ” ጋር በመተዋወቄ “በድሪ” እና “በድሪያ” ስለሚባሉት ስሞችም ለማወቅ ችዬአለሁ። እነሆ በነዚህ ስሞች ዙሪያ ስለሚነገሩ ወጎችም በጥቂቱ ላጫውታችሁ።
በሀረር ጌይ ትውፊት መሰረት “በድሪ አያም” በሚከበርበት ዕለት (ቀንም ሆነ ሌሊት) የተወለደ ህጻን ጾታው ወንድ ከሆነ “በድሪ” የሚል ስም ይሰጠዋል። ሴት ልጅ ደግሞ “በድሪያ” ትሰኛለች። እነዚህ ስሞች ለልጆች መጠሪያነት የሚውሉባቸው ሌሎች መነሻዎችም አሉ። ለምሳሌ መኖሪያ ቤቱ በ“በድሪ በሪ” ክልል የሆነ “ጌይ ኡሱእ” ልጁን “በድሪ” በማለት ሊጠራው ይችላል። እንደዚሁ ደግሞ በ“በድሪ በሪ” ክልል የተወለደ “ጌይ ኡሱእ” የኑሮው አድራሻውን ወደሌሎች ስፍራዎች ሲቀይር ጥንተ-ማንነቱ እንዲታወስ በማሰብ ለልጁ “በድሪ” (ሴት ከሆነች ደግሞ “በድሪያ”) የሚል ስም መስጠቱ የተለመደ ነው።
(ምንጭ:- አፈንዲ ሙተቂ: “ሀረር ጌይ- የአስገራሚዋ ከተማ የኢትኖግራፊ ወጎች”: ገጽ 216-219 )