Tidarfelagi.com

ለከፋ ችግር የማይዳርግ ለከፋ

ከጥቂት አመታት በፊት” የምነው ሸዋ “ ባለቤት አቶ ሸዋ ኢተና፥ ለእህቱ ልደት፥ ዲሲ በሚገኝ ክለብ ውስጥ የእራት ግብዣ አዘጋጀ፤ በእሱ መጥርያ ወደ አሜሪካ የመጡ ዘፋኞች አንደኛው ጥግ ላይ ተከማችተው ተቀምጠዋል ፤ ፋሲል ደሞዝ ፥ አጫሉ ሁንዴሳ ፥ ሃይሉ ፈረጃ ፤ ሀፍቶም (አባቱን የረሳሁት) ዘፋኝ እና ሌሎች ድምጻውያን ነበሩ ። ይህን ማስታወሻ የጻፈው ጭሮ- አደርም የዘፋኝ ለምድ ለብሶ ተቀላቅሏል።

እኛ ከተጠቀመጥንበት ጥግ የተረፈው የክለቡ ሆድ ፥ ካፍ እስከ ሰደፉ በሌሎች ደንበኞች ተሞልቷል ፤ ከወድያ ማዶ ጥግ የሆነ ሰውየ ሲመጣ ተመለከትኩት፤ የሚጨበሱ ፤ የሚደንሱ፤ ወይም ያለምንም አላማ በትጋት የሚቆሙ ሰዎችን እየጣሰ አሁንም አሁንም ” እስኪውዝ ሚ” እያለ እኛ ወደ ተቀመጥንበት ይሳባል ፤ ሁለት ብርጭቆ ቢራ ጨርሼ ቀና ስል ሰውየው፥ በክርናቸው እሚጎስሙትን በግራቸው እየደቀደቁትን ዳንሰኞች ታግሶ እየገሰገሰ ነው ። የቀረበልኝን ራት አጠናቅቄ ወደ ፊት ሳፈጥ ፥ ሰውየው ልክ በሚፈጥን ባቡር ውስጥ ካንዱ ፉርጎ ወደ ሌላው ፉርጎ የሚዛወር ተሳፋሪ ይመስል ከወድያ ወዲህ እየተላጋ ወደኛ ለመድረስ ይፍጨረጨራል ፡ በመጨረሻ ከፊትለፊታችን ቆሞ ኩንታል ከትከሻው እንደ ተራገፈለት ኩሊ በረጁሙ ተንፍሶ ሲያበቃ “ የመጣሁት እንደማላደንቃችሁ ለመናገር ነው ‘ አለና በመጣበት ሁኔታ ተመለሰ። እንደማያደንቀን ለመናገር የከፈለውን መስዋእትነት ባሰብኩት ቁጥር ሳደንቀው እኖራለሁ።

ይህ ደግሞ ጉዋደኛየ ነው የነገረኝ፤ ጊዜው ትንሽ ቆየት ብሏል:; ባንድ ምሽት፥ አሜሪካን አገር በታወቀ ሬስቶራንት ውስጥ ንዋይ ደበበ ይዘፍናል “ “ አገሬን አልረሳም አገሬን “ እያለ ይቀውጠዋል! በዛ ሰአት ደግሞ አብዛኛው ዲያስፖራ አገሩን ለመርሳት እየጠጣ ነው፤ ንዋይ “ አገሬን አልረሳም “ ይልና እንዲጨርሱለት ማይኩን ወደ ታዳሚው ይደግነዋል፤ “ “እዚህ ጋ አንድ ጎድን ጥብስ አዝዘን ነበር! “ ከሚል ያንድ ተስተናጋጅ ምሬት በስተቀር ከታዳሚው አካባቢ የሚመጣ ድምጽ አልነበረም ። ንዋይ ዘፍኖ ጨርሶ ልብሱ ለመቀየር ወደ ሬስቶራንቱ ጓዳ ሲገባ አንዱ ታዳሚ እንደ ጥያ ደንጋይ ጓዳው በር ላይ ተገትሮ ጠበቀው። እና ተገታሪው የንዋይን ተከሻ እየተመተመ እንዲህ አለ ፥
“ በርታ! በዚህ ከቀጠልክ አልበም ማውጣትህ አይቀርም”።

ከአመታት ባንዱ ቀን ከጌትነት እንየው ጋራ ” አንበሳ ባር” ምሳ በላን፤ ከዚያ ወጥተን ልንሸኛኝ፥ ወደ ካዛንቺስ እሚያራምደኝን መንገድ እና ወደ ብሄራዊ ቲያትር እሚመልሰውን ጎዳና የሚያገናኝ ቦታ ላይ ቆምን ፤ ወድያው አንድ ጎልማሳ ሲጋራ እያጤሰ አጠገባችን እግሩን አንፈራጦ ቆመ! ካቋቋሙና ካስተያየቱ ተነስቼ ለአድናቆት ሳይሆን ለለከፋ እንደተሰናዳ ገመትኩ፤ እና ክፍተት ላለመስጠት የሰማይ የምድሩን ስቀድ ሰውየው ጮክ ብሎ፥
“ ጌትነት ! ቅድም ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ፊትለፊት አየሁህ ! አሁን ደግሞ እዚህ አገኘሁ ፤ እንዴት ነው ነገሩ?” አለና በእርካታ ፈገግ አለ።
እንዴት ነው ነገሩ? የሚለው ሲተረጎም ፤ በዛህብኝ ፤ ብርቅ መሆንህ ቀረ ምናምን ሊሆን ይችላል።
ጌትነት የሰጠው ምላሽ መቸም አይረሳኝም!
“ስራ ፈተህ እምትከተለኝ ከሆነ ፤ ትንሽ ቆይተህ ደግሞ ለቡ አካባቢ የምታገኘኝ ይመስለኛል”

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...