Tidarfelagi.com

‹‹ለእኔ ያላት እንጀራ››

ሰው አይወጣልኝም።

በሰላሳ ሰባት አመቴ ሕይወቴ ከጥቂት ሰዎች የተሰራ ነው። ሁለት በሰላሳዎቹ እድሜዬ ያገኘኋቸው የልብ የማይባሉ ጓደኞች፣ እናቴ፣ አባቴ፣ አንድ ግማሽ እህት (አባቴ ከእናቴ በፊት የወለዳት) እና ጊዜያዊ ወዳጆች።
እግዜር ከሰጠኝ ሰዎች ውጪ የእኔ ብዬ ያቆምኩትና የፀና የረጅም ጊዜ ግንኙነት የለኝም። የልጅነት ባልንጀራ የለኝም። አብሬው አንድ በአል ሁለት ጊዜ ያከበርኩ የወንድ ጓደኛ ኖሮኝ አያውቅም። ሚስጥረኛ የለኝም።

የፍቅር ግንኙነቶቼ አጭርና በጉድፍ የተሞሉ ናቸው። ይህ ሁሉ በልጅነቴ ያመንኩት ሰው ከድቶኝ ወንድ አላምን ብዬ ምናምን አይደለም። እስከማምነው አብሮኝ የሚቆይ ወንድ አላገኘሁም። እንተዋቃለን። የተግባባን እንመስላለን። ቡና-ማኪያቶ እንባባላለን። ክትፎ- በየአይነቱ እንገባበዛለን። ወይን -ቢራ አብረን እንጠጣለን። ቤርጎ ወይም ቤቱ ሄደን እንተኛለን። ከዚያ ሁሉ ነገር ይከስማል። ይፀድቃል የተባለው ይጠወልጋል። እንደ እሳት የተንቀለቀለው በቀናት ወደ አመድነት ይለወጣል።

እንደ ሰው ባል የሚሆን ወንድ አግኝቼ መሰብሰብ፣ ልጅ ወልዶ መሳም ጠልቼ አይደለም። በጉልምስና እድሜዬ በሃያዎቹ መባቻ ላይ ሆና ጊዜ ተርፏት እንደምትሽኮረመምና ከአንዱ አንዱን የምታማርጥ ልጃገረድ በየካፌው የማይረባ ማኪያቶ የማንቃርረው፣ በየቤርጎው ያልታጠበና ሌላ ሰው-ሌላ-ሰው የሚሸት አንሶላ ላይ የምጋደመው ሰው ፍለጋ፣ ባል ባገኝ ብዬ ነው። ግን ሰው አልወጣልኝም።

ለዚህ ነው መስፍን የተለየብኝ።
መስፍኔ!
ቢሯችን ጨረታ ሊያስገባ መጥቶ ነው የተዋወቅነው። እንደታየሁ የወንድ ልብ ትርክክ የሚያደርግ ውበት፣ የሚያስደነብር ቁንጅና፣ እስቲ ስልክሽን አስብሎ የሚያስለምን ቁመና የለኝም። ግን መስፍን እንደሱ ሰራው።

ጨረታውን እንኳን ሳያስገባ ስምሽ ማነው ብሎ ጠየቀኝ።
– ማህደር…አልኩኝ ትኩር ብለው የሚያዩኝን አይኖቹን ሽሽት ጠረጰዛዬ ላይ ተመሳቅለው የተቀመጡትን ወረቀቶች እያየሁ፣ ከዚያ ደግሞ ቀና ብዬ እያየሁት።
– ፐ! የሚያምር ስም…ማህ- ደር! አለ ስሜን ሁለት ቦታ ከፍሎ።
ስሜን እንዲህ ከወደደው ስልክ ቁጥሬንማ በጣም ይወደዋል ብዬ ለራሴ ቀልድ ነግሬ ራሴው ፈገግ ስል
– ምነው? ፊቴ ላይ የሚያስቅ ነገር አለ? አለኝ
– አረ የለም….
– ወደሽኝ ነው?
– ሆሆ…
– ምነው የምወደድ አይደለሁም?
ሳቅኩ።

የሚወደድ አይነት ነበር።

ፍቅር ጀመርን።

ሁለት ወር በየቀኑ በሚባል መጠን እንገናኝ ነበር። ያልተገናኘንባቸውን ጥቂት ቀናት እና ሰአታት በሌሊት የስልክ ወሬዎች እንሞላቸው ነበር።
የምወደውን ስለሚወድ፣ የሚወደውን ስለምወድ ሁሉ ነገር ቀላል ነበር።
ቲያትር ብንገባ ብዬ ያሰብኩ ቀን ቀድሞ ‹‹ዛሬ ቲያትር እንይ›› ይለኛል።
የከቤ ኬክ ቤት ኬክ ውል ሲለኝ ፊቴ ላይ የተፃፈ ይመስል ‹‹ዛሬ ኬክ አላማረሽም? እስቲ ከቤ ኬክ ወክ እናድርግ ›› ይለኛል።

የሚወደድ አይነት ነበር።
ትሁት እና ደግ፣ ቁጥብና ርጋታ ያለው ሰው ነበር።

ብቻንን ስንሆን ደግሞ ቁጥብነቱ ወደ ስግብግብነት፣ ርጋታው ወደ ሚያስገርም ጥድፊያ …ደስ በሚል ሁኔታ ይለወጥ ነበር። በአደባባይ በትህትና እጆቼን ይዞ እንደማይጓዝ፣ ቤት ውስጥ ለፍቅር እያዘጋጀ ሲያቅፈኝ በመሃከላችን አየር እንኳን አያልፍም ነበር።

ከንፈሮቼን ተርቦ እህል እንዳገኘ ሰው ሲጎርሳቸው….
እያንዳንዳቸው አስር ጣት ያላቸው አምስት እጆች እንዳሉት ሁሉ ልገምት በማልችለው ፍጥነት መላ ሰውነቴን አንድ በአንድ፣ ግን ደግሞ ባንድ ጊዜ ሁሉም ቦታ ሲነካካኝ፣ ሲዳብሰኝ….ጀርባዬ ጋር ነው ስል ጭኖቼ ጋር…ጭኖቼ ጋር ስል ጡቶቼ ጋር…ጡቶቼ ላይ ናቸው ስላቸው ጭኖቼ መሃል የሚገቡት እነዛ ጣቶቹ….
እነዚያ ለሶስት ሰው የሚበቁ ወፋፍራም ከንፈሮቹን አስተባብሮ ጆሮዬን እየሳመ ስሜን አጣፍጦ ሲያንሾካሹክ (ማ…ዲ…ዬ…ዬ) ፍቅረ ሳንሰራ ጧ ብዬ የምፈነዳ ይመስለኝ ነበር።

ወ-ደ-ደ-ኩ-ት።

እኔም በተራዬ ሰው ወጣልኝ።
ስንቴ የተማለድኩት ፈጣሪዬ መስፍኔን ባል አድርጎ ሰርቶ ላከልኝ።

ግን ፈራሁ።
ስለ መጋባት፣ ስለትዳር ወሬ ላወራው ፈራሁ። ግጣሜ መሆኑን ባውቅም በሁለት ወር ውስጥ ብንጋባስ የሚል ሃሳብ ከአፌ አውጥቼ ማስደንበሩን ፈራሁ።

ግራ የሚያጋባ ሁኔታ ውስጥ ነበር ራሴን ያገኘሁት። ለጋብቻ የረፈደ እድሜዬን ሳስብ ስለ ጋብቻ አለማውራት አልችልም። ረፍዶብኛል። የሁለት ወር ግንኙነታችንን እድሜ ሳስብ ግን ስለ ጋብቻ ማውራት አልችልም። መዋከብ ይሆናል። ብሽቅ ሁኔታ አይደለም?

ሁለቱን ጓደኞቼን አማከርኩ።
ቤቲ በዘወትር ችኮላዋ ፣
– ስንት አመቱ ነው? አለችኝ።
ያልጠበቅኩት ጥያቄ ነበር።
– ስንት አመቱ ነው እሱ? ደገመችው።
– እ…እኔንጃ..
– እንዴ! አታውቂም እንዴ? እድሜውን ሳታውቂ ነው እስካሁን ላይ ታች የምትይው?
መስፍኔን እድሜውን በቀጥታ አልጠየቅኩትም። መጠየቅ ትልቅ ነገር ሆኖ ሳይሆን ያንን ጥያቄ የሚያስነሳ የወሬ ክር ስላልጀመርን ነው። አለ አይደል…ስለ ጃዋር ምናምን እያወራን ለመሆኑ አንተ እድሜህ ስንት ነው አይባል ነገር….
– አልጠየቅኩትም ግን መገመት እችላለሁ….አልኩ
– እ…ስንት ነው? ቤቲ አሁንም በጥድፊያ ጠየቀችኝ
– ኦኬ…ዩኒቨርስቲ …ግራጂዌት ያደረገው በ92 ነው….
– በእኛ?
– እንዴ ኦፍኮረስ በኛ! ይሄን ያህል ሽማግሌ አረግሽው እንዴ! አልኩ እየሳቅኩ።
– የዛሬ ወንድ ምኑ ይታመናል! ለራሳቸው ሰርግ ሽማግሌ ሆነው መሄድ ሁሉ ጀምረዋል እኮ…
ሁላችንም ሳቅን።

አፍታም ሳትቆይ ቤቲ ስልኳን ከቦርሳዋ በፍጥነት አወጣች። መስፍኔ በሌለበት እድሜው ሊሰላለት ነው።
ጎንበስ ብላ ጠቅ ጠቅ አድርጋ ቀና ብላ አየችኝና፣
– የአዲሳባ ልጅ ነው? አለችኝ
ግር ብሎኝ…
– እሱ ደግሞ እድሜው ውስጥ ምናገባው? አልኳት
– እንዴ…የገጠር ልጅ ከሆነ ትምህርት ቶሎ ስለማይጀመር አንድ አምስት ልጨምርበት ነዋ! ብላ ስትስቅ እስካሁን ዝም ብላ የነበረቸው ሄዋንም አጀበቻት።
– ወይ ጉድ..ያንቺ ጉድ ብዙ ነው…የአራት ኪሎ ልጅ ነው.. አልኩ
– ፋይን! እንግዲህ ሁለት ሺ አስራአንድ ገባን አይደል….በሃያ ሁለት አመቱ ጨረሰ ብንል እንኳን አርባ አንድ ወይ አርባ ሁለቱን ጠጥቷል ማለት ነው! አለችና ትልቅ ሚስጥር ቆፍሮ እንዳገኘ ሰው ኮራ ብላ ሶስት ጊዜ አጨበጨበች።

ከግምቴ ብዙ የራቀ ስላልነበር አልተገረምኩም።

– እሺ…እድሜው ይሁን እና ምንድነው ምትመክሩኝ? አልኩ ቤቲንም ሄዋንንም እያየሁ
ሄዋን ንግግሯን ለመጀመር አፏን ስትከፍት ቤቲ ቀደመቻትና
– እኔ ጠይቂውና ያበጠው ይፈንዳ ነው የምለው….እሱም ትልቅ ሰው ነው ደግሞ…ከማይሆን ሰው ጋር ጊዜሽ ዌስት የምታደርጊበት እድሜ ለይ አይደለሽም…በዛ ላይ አሪፍ ነው ምናምን ብለሻል…እና…ጠይቂው ባይ ነኝ። አለችኝ።
ምክሯ አልገረመኝም። የቤቲ የኑሮ ዘይቤ ችኮላ እና ያበጠው ይፈንዳ ነው። ፍጥነት ነው። ዛሬን መኖር ነው።

ሄዋንን አየኋት።

– እኔ….እኔ….. ብላ ጀመረች። ልትሽከረከር ነው እንግዲህ!

ሄዋን አንዲት ነጥብ ለማንሳት ቃላትን ስለምትፈጅ እና የምትፈልገውን ነገር ለመናገር ጊዜ እንደምትወስድ ስለምናውቅ እኔም ቤቲም ወንበራችን ላይ ለጠጥ ብለን ተቀመጥን።

– እኔ…እኔ ግን ትንሽ ብታይው ጥሩ ነው ባይ ነኝ። እኔ እንደሚመስለኝ…ማለቴ ሲመስለኝ….እስካሁን ያላገባበት ምክንያት ይኖራል…ትዳር ይፈራ ይሆናል….ወይ ደግሞ መጥፎ ነገር ደርሶበት ቢሆንስ…ለማለት የፈለግኩት ምንድነው….ቶሎ ጠይቀሽ እንዳታስደነብሪው..ቢሸሽስ? ትንሽ ብትታገሺ ከራሱ ሊመጣ ይችላል….እኔ እንደሚገባኝ…ወንዶች..ማለቴ ብዙ ወንዶች ትዳር ትዳር ሲባሉ አይወዱም…እኔ የምለው…እንደውም…እንደውም እንዲያገባሽ ከፈለግሽ ትዳር የሚባል ሃሳብ ውስጥሽ እንደሌለ ማሳመን አለብሽ…ሰናይ ሁሌ ነው ለእኔ የሚነግረኝ….ሰናይ ምን ይላል መሰለሽ….ወንድ የሚወደው እንደዛ አይነት ሴት ነው….ዛሬን የምትኖር…አለ አይደል…ነገ ነገ ማታበዛ…..አሁን እኔን አታይም? ማለቴ ሰናይን አታይም? አንድ ቀን ስለትዳር ሳላነሳበት ሁለት አመት ኖረን ነው ራሱ የጠየቀኝ…ለጓደኞቹ ምን ብሎ እንደነገራቸው ታውቂያለሽ? እንጋባ እንጋባ ብላ የማትነዘንዝ የመጀመሪያ ገርልፍሬንዴ እሷ ነበረች እያለ ነው የሚነግራቸው…..ለእኔም ምኔን ወደድከው ስለው እሱ ነው የሳበኝ ምናምን ሲለኝ ነበር…እነሱ…ማለቴ ጓደኖቹ.. ራሳቸው ታድለህ ምናምን ሲሉት ነበር…እና…ፈታ በይ…ኢንጆይ…በዛ ላይ ሴክሱ አሪፍ ነው አይደል?

ሳቅኩ።
– ምናባሽ..አሪፍ ነው አይደል? አለች ሄዋን
– አዎ…በጣም… አልኩና ተሸኮረመምኩ።
– ከመጋባታችሁ በፊት ኢንጆይ ኢት እናቴ! ከዚያ እንደኛ ድር ያደራበታል አለች ሄዋን እሳቀች።

አብረናት ስቀን ስንጨርስ ሁለቱንም አፈራርቄ አየኋቸው።

ያበጠው ይፈንዳ ባይዋ ቤቲ በሰላሳ ስድስት አመቷ አሁንም ላጤ ናት። ረጋ በይ ባይዋ ሄዋን ደግሞ በሰላሳ ሁለት አመቷ አግብታ ሁለት ወልዳለች።

አላማዬ ሄዋንን እንጂ ቤቲን መሆን ስላልሆነ ልቤ ወደ ሄዋን ምክር አደላ። ሃሳቤ ፊቴ ላይ አስታወቀብኝ መሰል ቤቲ በራስሽ ጉዳይ ትከሻዋን ሰበቀች።

ሺህ ጊዜ ትስበቅ።

ለእኔ ያላት እንጀራ ትሻግታለች እንጂ ማንም አይበላትም ይላል ሃበሻ። ለኔ ያለው ባል ቆሞ ይቀራል እንጂ ማንም አያገባውም።

እስኪጠይቀኝ አልጠይቀውም ።

ለእኔ ያላት እንጀራ (ክፍል ሁለት)

 

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...