እሰከመቼ በአሳቻ ለሊት፣ በሀሰተኛ ዶሮ ጩኸት እየነቃህ!?
አርፈህ አተኛም? አርፈህ አገሩን አትመስልም?
ይልቅ እንካ ምክር፣
ሀሰተኛ ዶሮ በኳኮለ ቁጥር፣
የሚናድ፣ የሚጣስ የእንቅልፍህ አጥር
መኖርህን አብዛ ከመተኛት ቅጥር።
**
ተኛ። ብትችል አውቀህ ተኛ። “አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም ” ይላል የተኚዎች ተረት።
እንቅልፍ እምቢ ካላቻሁ በህብረት እንዲህ ፀልዪ፣
የመንቃትን ፀጋ ሁሌ ከምንነቅፍ፣
ጌታ ሆይ ላክልን የአርባ ዓመት እንቅልፍ!
እርፍ!
ዓርባ ዓመት? የምር ልተፅልዩ ይሆናል እኮ?
እነ እንትናም ከዚህ በኋላ ልማቱን ለማስቀጠል ዓርባ ዓመትም አይደል ያስፈልገናል ያሉት?
በቃ እነሱ ያልሙ(ጠብቆም ላልቶም) አንተ ተኛኣ?
በእንቅልፋም ዘመን ማስታወቂያው ሁሉ ፍራሽ ብቻ ነው።
አሪፍ ፍራሽ ገዝተህ ለሽ በል!
ነቅተህ ካልነቃህ ምን ታንጎላጃለህ ወዲህ? አንድ እርምጃ ወደ እንቅልፍ፣
አንድ ሺ እርምጃ ወደ ፀጥታ። ቻው።
Switch on ur tv,
lots of bed time stories are waiting for u.
ነግቷል የሚሉህን አትስማ። አንተ ፀሃይን መስራት ያቃተህ ልፍስፍስ ነህ። በሰዎች ፀሀይ ንጋትህን አትጠብቅ። ተነስተህ ካልተነሳህ አርፈህ ተኛ።
አለመንጋቱ ለልጆች እንኳን ገብቷቸዋል።
አኩኩሉ ሲጫወቱ፣ “ነጋ? ” ሲባል፣
“ነግቷል ” የሚል ልጅ ድሮ ቀርቶ?
ጨዋታው ሁሉ አልነጋም ሆኗል።
የንጋት አብሳሪ ወፎች ሁላ ቀልደኛ ሆነው፣ ባልነጋ ለሌት መሃል ኮራ ብለው ዝማሬ ያሰሙሃል። ከማን ተመሳጠሩ?
አውራ ዶሮው እንኳን እንደ አውራ ፓርቲ በአደባባይ ሲያሾፍ?
በናትህ ለምን አትተኛም?
ወይ ለናትህ ስትል ተኛላት።
የመንቃትህ ስጋት እንቅልፍ የነሳቸው፣
ለዕድሜ ሳያስተኙህ ቀድመህ ተኛላቸው።
ሃሃ
ልትተኛ ነው አይደል?
ተኛ ሲሉህ የምትተኛ ኖረሃል እንዴ ግን አንተው? ተኛ ሲሉት የሚተኛ በዝቶ እኮ ነው ሀገሪቱ ትልቅ ቤርጎ የመሰለችው።
የሚገርምህ ይህን ፅሁፍ ከዚህ በላይ ላረዝመው ፈልጌ ነበረ፤ እንቅልፌ ስለመጣ መተኛት አለብኝ።
አንተ ግን ለምን አትተኛም?
3 Comments
እጅግ በጣም ተመችቶኛል!
ተኝቻለሁ!
Wow ተመችቶኛል
አቤት!!! ስትመቸኝኮ¥