Tidarfelagi.com

ለሙዚቃ የመነነው ኤሊያስ!

 

በዓሉ ግርማ ከሀዲ ደራሲ መሆኑን የነገረኝ የቀድሞ መምህሬ ቴዎድሮስ ገብሬ ነበር።“ከአድማስ ባሻገርን” ካነበብኩ በኋላ እኔም የእሱ ጭፍራ ሆንኩኝ። ታላቁን ደራሲ በክህደት ወነጀልኩኝ። ተስፋ ያጣውን አበራ ወርቁ ለምን ሲል በልቦለዱ መቋጫ ላይ በጉልበት ብሩሽ አስጨብጦ ከብርሃን አገናኘው አልኩኝ። ፍርሃቱን እረገምኩኝ። እርግማኔ ግን በጊዜ ሂደት ተረታ። ከበዓሉ በላይ ከሀዲ ከሆነ የጥበብ ሰው ጋር ተዋወኩ።

ምናኔው ያስፈራል። ከዓለም ርቆ መኖሩ ያስደነግጣል። አብነት ተወልዶ አዲስ አበባን ዘንግቷታል። ዳርማርን ረስቶታል። ልደታ ሰፈርን ይናፈቀው ይዟል። ምን ጉድ ነው ?አልኩ።ከተማ እየኖሩ መመነን እንደሚቻል ከእሱ ተማርኩ። የጥበብ ምንኩስናው አንቱ ቢያስብለውም እኔ ግን ኤሉ ለማለት አላንገራገርኩም። ኤሊያስ መልካ ከሃዲ የጥበብ ሰው ነበር። ክህደቱ ፅልመትን ነው። ሽሽቱ ከጨለማ ነው። ስራዎቹ ላይ የምታዘበውን እውነት አንድ ቀን በድፍረት ጠየኩት። በሚያስፈራ ሀገር እና ዓለም ውስጥ እየኖሩ ሁሌም ብርሃንን ማዜም ውሸት አይደለም ወይ ?አልኩት። ማዕረግ ውሸታም ነህ እያለኝ ነው ብሎ ፊቱን ወደ ሃይሌ ሩትስ አዞረ። ሰራዊቱ በተጠንቀቅ እየጠበቀኝ ነው።

ጌቴ አንለይ ሙዚቀኛ ከተሰፋ ውጭ ሌላ መዝፈን የለበትም ብሎ ብዙ ነገር ዘረዘረ። አልበም ያላወጡት ሁለት ወጣቶች ጥበብ ከጨለማ ሽሽት መሆኑን ሊያብራሩልኝ ሀሳቤን ተቀባበሉት።የልጆቹ መልስ እዮብ መኮንን በወቅቱ ስለሙዚቃ ከሰጠው ቃለ-መጠይቅ ጋር መመሳሰሉን ሳስብ ነገርዬው የኤሊያስ የህይወት ፍኖት ውጤት መሆኑ ተገለጠልኝ።
ውሸታም አልከኝ ? አለ በድጋሚ። ፈገግ አልኩ። እጁ ላይ ያለችውን ሲጋራ አሻሽቶ ለኮሳት። ሁለት ጊዜ ከማገ በኋላ። ሀገር ምን ማለት ነው ? የሚል ጥያቄ አቀረበልኝ። ሀገር ሰው ነው አልኩት። መራሄ ተውኔት አባት መኩሪያ ያዘጋጀው ቴአትር ላይ ያለውን “ሀገር ማለት ሰው ነው ”የሚል መዝሙር እንደሚወደው ስለማውቅ ብዙ አልተጨነኩም። ቀጠለ። የሀገር ተስፋ ማለት የሰው ተስፋ ማለት ነው። የእኔ እና አንተ ተስፋ ማለት ነው። ኢቢሲ መስራትክን እርሳው። ኢትዮጵያዊነትን ሩቅ አታድርገው።

ኢትዮጵያዊነት ማለት የጥንዶች፣የባላትዳሮች፣የአንድ ቤተሰብ ፍቅር የወለደው ነገር ነው። ለእነዚህ ጉዳዮች የምንሰጠው ቦታ ነው ትልቋን ኢትዮጵያ የሚፈጥረው። እኔ በስራዎቼ ስለ ፍቀረኞች መለያዬት እንዲዜም አልፈቅድም። ቀኑ ጨለመብኝ የሚል እንጉርጉሮ አልወድም። ምክንያቱም የፍቅረኞች መለያየት ነው የሀገርን መለያዬትን የሚወልደው። የግለሰቦች ጨለምተኛ መሆን ነው የሀገርን ጨለምተኝነት የሚፈጥረው። እኔ የካድኩት ፅልመትን ነው። እኔ የካድኩት ጨለማን ነው። ……..የቤት ሰራተኛው ኤሊ ሰው ይፈልግሃል አለችው። ተነስቶ ወጣ። ተመስገን አልኩ ! አያያዙ እኔንም ሊያጠምቀኝ ከጫፍ ደርሶ ነበር።

የኤሊያስ ሀዲድ ብርሃን ነው። የኤሊያስ ኢትየጵያ እኔና አንተ ነን።የአብነቱ ብላቴና ክህደት ከክህደት ጋር ነበር።በጊዜ ሂደት ከሃዲነቱን ወደድኩት። እንኳን ውሸታም ሆንክ አልኩት። ሰውነት ህይወትን ዳግም መተርጎም ፤በተፍጥሮ ላይም መሰልጠን ነው።የኤሊያስ መልካ ስኬት ምንጩም ህይወትን መተርጎሙ፣ተፈጥሮ ላይም መጎርመሱ ይመስለኛል። ኤሊያስ የአንተን ጎርናና፣ቀጭን፣አስቀያሚ ድምፅ ወስዶ አዲስ ውብ ድምጽ ይለግስሃል።

የሚኪያ በኃይሉ የመጀመሪያ ዓልበም ዓመታትን ወስዶ የመጨረሻ ሰራው እየተካሄደ እያለ አንድ ልብ ያላልኩትን ውብ ድምፅ ገና አሁን ሰማሁብሽ ብሎ ሙሉ አለበሟን እንዳስፈራት ሰምቻለሁ። የጌቴ አንለይን ድምፅ ከባህል አላቆ ሲያሻው ብሉዝ ፣ደስ ሲለው ችክችካ እንዲጫወት አድርጎታል። ኤሊያስ መልካ ከሳህሌ ደጋጎ (ኮለኔል) እና ሙላቱ አስታጥቄ በኋላ ተፈጥሮን በውሉ መግራት የቻለ ኢትዮጵያ የሙዚቃ ሰው ይመስለኛል። ማኅሌት ገብረ-ጊዮርጊስ ጋር የሰራውን የትግረኛ ሙዚቃን ልብ ብሎ የሰማ ሰው የምለው ይገባዋል።

የአብነቱ ብላቴና የሙዚቃ ችሎታ ልምድ የወለደው ነው ብዬ ለመቀበል ይቸግረኛል። የኤሊያስ መልካ የመጀመሪያ ስራ “ሁሉም ይስማው” የተሰኘው የማሀሙድ አህመድ ዜማ ነው። መግቢና መሸጋጋሪዎቹን ደጋግሜ ስሰማቸው የበኩር ስራው እንዲህ የተዋጣለት የሙዚቃ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ የለም ብዬ በድፍረት እሟገታለሁ። የቴዲ አፍሮ የመጀመሪያ አልበም እንዴት የጀማሪ አቀናባሪ ስራ ነው ብዬ ላምን እችላለሁ። ለዛውም ክርስቲያን ስቱዲዎ ውስጥ ሰው አየኝ አላዬን ተብሎ ተደብቆ የተሰራ። ነዋይ ደበበ በአንድ ወቅት የነካው ሁሉ ይመርልህ የተባለ ሰው ነው ሲል ገልፆታል። እውነት ነው የኤሉ ጣቶች ታዓምረኛ ናቸው። እንደ ሚኪያ ድምፅ ታች አውረድው እንደ እዮብ ሬጌ ላይ ያወጣሉ። ፕሮዲውሰሮች ከኤሊያስ ስቱዲዮ የሚወጣን አልበም በውድ ለመግዛት አይሰስቱም። አድማጩም የጌቴ አንለይን አልበም አርባ ብር ገባ ብሎ አልተወውም።

ኤሊያስን ለስራ ከመጨነቁ አንፃር በሰው እድሜ ቀላጅ አድርገው የሚያዩት ብዙ ናቸው። ግን ስህተት ነው። አረጋሃኝ ወራሽ ያወጣው “በቃ በቃ ” አልበም እኮ አንድ ወር ብቻ ነው የወሰደው። ይርዳው ጤናውን በጥቂት ወራት ውስጥ ሙዚቃ አስተምሮ ለአልበም ማብቃት ታዓምር ይመስለኛል። ኤሊያስ መልካ ቀጥታ የሚሉት ዓይነት ሰው ነበር።ካመነበት የሌላውን ድጋፍ አይፈልግም። ብቻውንም ሆኖም ቢሆን ይፋለማል። የቅጅና ተያያዠ መብቶችን በተመለከተ በሸራተን ሆቴል በተካሄደው ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ያበላሹ ያላቸውን ሰዎች ስም እየጠራ በአደባባይ ተችቷል። አንድ ወቅት ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ጋር ልታገኛኝ ትችላለህ? አለኝ።ምነው በሰላም አልኩት።

አዲሱ የቱሪዝም ሞቶ ምደረ ቀደምት የሚሉት ነገር ሀገር እንደሚያዋርድ ልነግራት እፈለጋለሁ እለኝ። ምክንያቱን ጠየኩት። ምዕራባዊያን የሰው ልጅ በዝግመተ ለውጥ መጣ ብለው የሚያምኑ ህዝቦች ናቸው። ሀገራችንን ምድረ ቀደምት ብለን ማስተዋወቃችንም ኑ ዝግመተ ለውጡን ያልጨረሰ ህዝብ ታገኛላችሁ ብሎ ከመቀስቀስ አይተናነስም አለኝ። እንዲህ ያለው የኤሊያስ ነገሮችን በሌላ መንገድ መመልከት ለሙዚቃችን ትልቅ ገፀ በረከት ነበር።

ኤሊያስ መልካን ነበር እያሉ ማውራት ይከብዳል። ከቀናት በፊት እፈልግሃለሁ ብሎ ደወለልኝ። ሲ.ኤም ሲ የሚገኘው የአውታር ቢሮ ሄድኩ። ኤሊያስ በቦታው አልነበርም። ደወልኩለት፤ ዲያሊስስ ሲሰራለት ቆይቶ ናፕ እያደረገ እንደሆነ ነገረኝ። ከአፍታ በኋላ ደረሰ። አጎንብሷል ፤መራመድ ተስኖታል። ሃይሌ ሩትስና ጆኒ ራጋ አብረውት አሉ።መብራት በመጥፋቱ የህንፃው ሊፍት አይሰራም። አራተኛ ፎቅ ለመድረስ ደረጃዎችን መውጣት ጀመረ። ሦስት ደረጃዎችን ከወጣ በኋላ አቀተው። ቁጭ አለ። ተፈጥሮ ላይ የሚያምፀው ኤሊያስ እንደተረታ ገብቶኛል። አራት ፎቅ ለመውጣት ከ20 ደቂቃ በላይ ወስዶበት ቢሮ ተገናኘን። ስለአውታር አወራን። ድምፁ ይቋራረጣል። እረፍት አድርግ አልኩት። ሞትን ለመተባበር አለኝ ? ደነገጥኩ።

በመሃል አንድ ዓይነስውር ወደቢሮው ገባ። ለመነሳት ቢያቅተውም ተቀምጦ አልጠበቀውም። አጎንብሶ ሄዶ እየመራ ወንበር ሰጠው።ኤርፎኑን ከኪሱ አወጣ። የልጁ ሞባይል ላይ ሰክቶ ሙዚቃ መስማት ጀመረ። የአንተን ድምፅ ነው የምፈልገው የአንተን ዘፈን ነው የምፈልገው አለው። ልጁ የእኔ ድምፅ አኮ ነው ሲል መለሰለት። እንዳልወደደው ፊቱ ላይ ያስታውቃል። ታገሰኝ በደንብ እናወራለን ብሎት ወደእኔ ተመለሰ።

ሁኔታው ልብን ይሰብራል። ዓለምን ጥሎ የመነነላት ሙዚቃ እስካሁን የነፍሱ ገዥ መሆኗ ይገርማል። አሁንም ስቱዲዮ ትገባለህ ? አልኩት። አዎ አለኝ። ለእሱ ባልነግረውም ከሞት ጋር እልህ እንደተጋባ ተረድቻለሁ። ተፈጥሮን የማሸነፍ ልክፍቱ እዚህ ድረሰ መሆኑ ቢያስገርመኝም ምንም ልለው አልፈለኩም። የቢሮውን ደረጃ ቅልቁል ስጀምር ለምን እንደሆነ ባላውቅም አጋፋሪ እንደሻው ትዝ አለኝ። አጋፋሪ እንደሻ በስብሃት ገብረእግዛብሄር ልቦለድ ውስጥ ያለው ዋና ገፀ ባህሪ። ያ ሞትን ሽሽት በቅሎውን ጭኖ ሩቅ የሚሄደው አጋፋሪ እንደሻው። ከሞት ሊርቅ ፈረሱን ሽምጥ የሚጋልበው አጋፋሪ እንደሻው። ለኤሊያስ ያን ፈረስ ተመኘሁለት።

የአብነቱን ብላቴና አፍንጫው ስራ ከሚገኘው ሞት የሚያርቀው አንዳች ነገር አሰብኩ። ከሙዚቃ ውጭ ምንም እንደሌለ ተረዳሁ። የኤሊያስ አልጋ ጠልቶ ሙዚቃ ውስጥ መሸሸግም ትክክል ነው አልኩ። ግን የኤሊያስ ሙዚቃ እንደ አጋፋሪ እንደሻው ፈረስ ለጊዜው እንጅ ለዘላለሙ ከሞት ለማምለጥ የሚረዳ አልነበርም። ጠዋት ጆኒ ረጋ አዎ አጣነው ሲለኝ ማመን አልቻልኩም። ተፈጥሮን የሚረታው ወዳጄ ኤሊያስ መልሶ ተራታ። ወደማይቀረው ዓለም ለመሄድ በተሰለፍንበት ፌርማታ ላይ የማውቀው ቅኑ ኤሊያስ ተራው ደርሶ ጥሎኝ ሄደ።ደና ሁን ብርሃን የምትናፍቀው ወንድሜ። ደና ሁን

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...