ለምን ዓላማ እና ለማን ዓላማ ለመሞት ዝግጁ ናችሁ? ለአላማ መሞት አሪፍ ነገር ነው አይደል? አዎ! አሪፍ ነው ለብዙኀኑ- በግሌ ለኔ አይደለም፡፡ በያዝኩት ነገር ምክንያት ሞት ከመጣብኝ፣ ምላሴን አውጥቼበት ላሽ እላለሁ እንጂ፣ የሞኝ ጀብደኛ ሞት አልሞትም፡፡
በመሰረቱ አላማ የለኝም ቢኖረኝም ሙትልኝ የሚል አይደለም፡፡ እንዲያ ካለ ጠላቴ እንጂ አላማዬ ስላልሆነ ዶሮ እስኪጮህ ሳልጠብቅ እክደዋለሁ፡፡ ሃይማትም ለጊዜው የለኝም፣ ለነገገሩ እንዲያው ለጊዜው፣ ለጊዜው ብዬ ልለፈው እንጂ ለዘላቂውም አይኖረኝም፡፡ ሃይማኖትና እምነት ይለያያል አይደለ ግን? ….ሀገር አለኝ በእርግጥ፡፡ ለሀገሬ ግን አልሞትላትም፡፡ ብችል እኖርላታለሁ፣ እኖርባታለሁ እንጂ ለምን ስል እሞትላታለሁ፡፡ እሷስ ምን ቆርጧት ሞቴን ትሻለች? አንድ ደረጄ ዓለማየሁ የተባለ የዛ ዘመን ሰው( የመኢሶን አባል የነበረ)፣ በእፎይታ መፅሄት ላይ ለአንድ የሕወሓት ሰው በፃፈው የመልስ ደብዳቤ ውስጥ እንዲህ ይላል፤
–
“ ወንጀሉ የሚጀመረው መግደል ላይ ሳይሆን፣ ለመሞት ዝግጁ መሆን ላይ ነው፡፡ ለቅዱስ ዓላማ መሞት ቅዱስ ይሆንና እርኩስ የተባለን ዓላማ ተከታይ መግደል ወንጀል መሆኑ ይቀራል” ይላል፡፡ ዝቅ ብሎም፤ “እየፎከረ የሚሞት፣ እየዘፈነ ቢገድል ምን ይገርማል?”
ምስለ ሴጣን የሆነችው ደርግ በዘመኗ አገሩን ፣ ህይወትን እየተኛ ሞትን እንዲያልም` አድርጋው ነበር …“አብዮታዊት እናት ሀገር ወይም ሞት!፣ አብዮት ልጆቿን ትበላለች ፣ቀይ ሽብር ፣ ነጭ ሽብር ፣ አረንጓዴ፣ ቡራቡሬ….. ሽብር… ሞት! … ካካካ ጥይት ዷዷዷ…ጠብመንጃ…. ስንቱ ለሀገሩ ሞተ፣ ስንቱ በሀገሩ ሞተ? ስንቱ ለዓላመው ሲል ስንቱን ገደለ? ስንቱ ዓላማውን እየዘመረ ደረቱን ነፍቶ ወደ መቃብሩ ነጎደ? የስንቱ ዓላማ ትክክል ነበር? ከሞታቸው ሀገራቸው ምን አተረፈች? ሞታቸውን እያቃለልኩ አይደለም፡፡ ከውድ ህይወታቸው አንፃር ግን ሞታቸው የቀለለ ነው፡፡( ለነገሩ ስለ ህይወት ውድነት እርግጠኛ መሆንም አይቻልም)
መቼም ያ ዘመን፣ ሞት በዓላማ ወለል ላይ የሚደንስበት እየዘፈኑ መሞት የበዛበት ነበር፡፡ መረራ ጉዲና በግለ ታሪክ መፅሐፋቸው እንዲህ ይላሉ፤
“ ለዓላማችን ነው ብለን የገባንበት የፓለቲካ ዓለም ምን እንደነበርና ከሞት ጋር ስንጫወት የነበረውን የጅዋጅዌ ዐዋታ አስታውሼ በጣም አዘንኩ” (ገፅ 72)
….ብዙ ሰው ለሀገሬ እሞታለሁ፣ ለሃይማቴ እሞታለሁ ሲል ይገርመኛል፡፡ የሃይማት አላማ ህይወትን መስጠት እንጂ ህይወትን ማጥፋት ከሆነ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ ሀገር የሚኖሩባት እንጂ ማገዶ የሚሆኑባት ከሆነችም ነገር ተበላሽቷል፡፡ በመሰረቱ ማንም ለማንም አይሞትም፡፡ ማንም ለማንም በመሞቱ ለማንም የተሻለ አለም አያመጣም፡፡ ለሁሉ ነገር እራሳቸውን የመስዋት በግ አድርገው ማቅረብ የሚወዱ ሰዎች የነብሳቸውን ሰንካላነት በሞታቸው ሊያቀኑ የሚሞክሩ ሰነፎች ነው የሚመስሉኝ፡፡
የሚገርመው፣ ሟችም የሚሞተው ለዓላማ ገዳይም የሚገድለው ለዓላማ መሆኑ…….
ዓለም ከምናየው እጅግ የሰፋ ነው፡፡ እና በዚህ ሰፊ ዓለም ውስጥ ዓላማ በሚባል ጠባብ በረት ውስጥ የተከረቸምን መጋዣ መሆን አለብን??