Tidarfelagi.com

ህዳሴው የማይነካቸው፣ ህዳሴውን የማይነኩ የሰፈሬ ወጣቶች

አንዳንዴ በግድ መገረብ ያለባቸው ፖስቶች አሉ ብለው እናምናለን። አምነንም እንገርባለን…
*******
ህዳሴው የማይነካቸው፣ ህዳሴውን የማይነኩ የሰፈሬ ወጣቶች
(ይሄ ፓስት ህዳሴው ትክክለኛ ነው፣ አይደለም ብሎ አይነታረክም)
‹‹‹‹‹‹ ›››››››
እዚህች ሰፈር ነው ያደኩት፡፡ አድጌ “እግሬን ከመፍታቴ” በፊት ዓለም ከዚህች ሰፈር አትበልጥም ነበር ለኔ- ዓለሜ ነበረች! ተጠፍጥፌ የተሰራሁባት ፡፡ ልጅ ሳለን፣ ከሌሎች ሰፈሮች ሁሉ ተለይታ የጨዋታ ንግስት ነበረች፡፡ እስኪመሽ እንዘላለን፡፡ ብዛታችን ደግሞ!- ኑሮ እንዲህ እራሱን ከመስቀሉ በፊት ህዝባችን ምን ያህል በመውለድ ትጋት ላይ ተጠምዶ እንደነበር ምስክር ነው( እኛን ለጨዋታ እየላኩ አልጋውን ሲጫወቱበት ይቆያሉ እነሱ) ….ከኛ ቤት ፊት ለፊት ትልቅ ሜዳ አለ፡፡ እዚህ ሜዳ ላይ፣ ሻራፕ፣ እንቡሼ እንቡሼ፣ መሀረቤን ያያችሁ…፣ አኩኩሉ፣አባሮሽ፣ ኳስ፣ ገመድ ዝላይ፣ ግብ አልባ ዝላይ….. መዓት መዓት የተዘነጉኝን ጨዋታዎች ተጫውተናል፡፡ አሁን ተጣልተን በኋላ ታርቀናል፡፡ “መረብ በጥስ” የሚባል የእግር ኳስ ቡድን አቋቁመን፣ እግርቻን እስኪቀጥን ገንዘብ ልናሰባስብለት ከሰፈር ሰፈር ዞረናል፡፡ ማመንዘርን ሳንፈራ፣ ዕቃ ዕቃ በሚባል የልጆች ትወና አብሮ አደግ ሴቶቻችንን ሁሉ ተኝተናል( ዛሬ፣ “አድጌያለሁ እኮ” በሚል ግድግዳ ተገድግደን “ሰላም ነው!” በምትል ቢጢቆ ሰላምታ ከመተላለፋችን በፊት)

ዓለማችን ነበረች! የወደፊት የህይወታችንን መልክ ቀለም የቀባንባት- ብሩሻችንና የመረጥነው ቀለም የተለያየ ቢሆንም ቅሉ… ከሰፊው ዓለም የሰፋች ዓለማችን ነበረች! ለህይወት ቱማታ ሳንጨነቅ የልባችንን ቱማታ ያስታገስንባት፣ አያ ጅቦ ሳይመጣ ጫካ ያቋረጥናባት( “እንሂድ…እንሂድ…እንሂድ በጫካ፣ አያ ጅቦ ሳይመጣ” እያልን)…. ማደግ የሚባል አያ ጅቦ፣ የልጅነት ልቦናችንን ሳይበላት በፊት…)

ዛሬማ “ታደገ”! …ዓለም ከሰፈራችን እንደምትሰፋ፣ ከዕቃ ዕቃ እንደምትለይ አየን። ሰፊው ጠበበን፡፡ በጥበት ውስጥ ብዙዎች ጠፉ፡፡ ዛሬ…“አንድ ላይ ብንሆንም ተለያይተናል”…. እንደ በፊቱ ከሰፈሬ ልጆች ጋር አብሬ አልውልም ፡፡ ተመሳሳይ ልቦና የያዙት ግን ዛሬም አንድ ላይ ናቸው፡፡ ሳገኛቸው ግን ስለዛሬያቸው ከአንደበታቸው እሰማለሁ፣ አልፎ አልፎ ስመጣም መንገዳቸውን አያለሁ፣ ጀቡዷቸውን ሲተርኩ ወይ ሲተረክ እሰማለሁ፡፡ ያቺ የልጅነት ነብስ እንዴት አድፋለች እናንተው?

ሲሳይ ጠኔ፣ ማን “ቁቅ ሰሪ”(ማጅራት መቺ) ይሆናል ብሎ ያሰበ ነበር? ከስሙ ቀጥሎ “ጠኔ” የሚል ማዕረግ የገባለት ልጅ እያለን ነው- ታች ክፍል፡፡ ለብሔራዊ መዝምሩ በተሰለፍንበት በሰልፍ መሀል ወደቀ፡፡ በውሃ፣ በክብሪት በምናምን አድርገውለት ነቃ፡፡ “ምን ሆነህ ነው?” ጠየቀው አንዱ አስተማሪ፡፡ “ እ..ር..ቦ..ኝ” ረሀብ በቦረቦረው አንጀት በሚበላ ድምፅ መለሰ፡፡ “ውይይ…” አለ አስተማሪው፤ “ ጠኔ ነዋ ለካ የጣለሽ?” …………………… ሲሳይ ጠኔ ተባለ፡፡ አንገት ደፊ ነበር በፊት፤ አንገት አናቂ ሆኗል ዛሬ፡፡ ቀበሌ ሁለት ሄደው ከኩባ ጋር ሞባይል መንትፈው ሲያመልጡ ተያዙ ተብሎ፣ ሙሉ ሰፈሩ እጁን በአፉ ጭኖ ነበር አንዴ! የተያዙበት ሰፈር ወጣቶች ቅጥቅጥ አድርገዋቸው፣ የሆረር ፊልም ተዋንያን መስለው ነበር የመጡት፡፡ ኩባ በዚያው ሲያቆም፣ ሲሳይ ጠኔ በዛው ቀጠለ፡፡

ዛሬ ለአብሮ አደጎቼ፣ ከአንዲት ሴት ጋር አራት አምስት ሆኖ ወሲብ መፈፀም ግርማ ያለው ጀብዱ ነው፡፡ ስንታየሁ የሚባል ልጅ አለ፡፡ ግቢያቸው ውስጥ የራሱ ክፍል አለችው- ከዋናው ቤት ፈንጠር ብላ የተሰራች፡፡ በየቀኑ ልክ የለሽ ወሲብ የሚገበርላት ናት እቺ ቤት፡፡ ከየትም ከየትም ብሎ ሴት ያመጣል፡፡ አምንጭው ብዙ ጊዜ ስንታየው ቢሆንም፣ የትኛውም መሰሉ ሊሆን ይችላል፡፡ የመጣችውን ልጅ አምጪው ይቀድሳል፡፡ሲጨርስ ለሽንት በሚል ሰበብ ይወጣል፡፡ ሌላ አንድ ወንድ ይገባል፡፡ ከተስማማች በፍቃዷ፣ ካልተስማማች በግዷ ታደርጋለች ልጅቷ፡፡ በአቅራቢያው ያለ ማንኛውም የፈለገ የሰፈረ ወጣት፣ የመግባት መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ “አታደርግም?” ተብለህም ትጋበዛለህ ብዙ ጊዜ፡፡ የሚገርመኝ ግን… ብዙዎቹ ሴቶች በንጋታው ተመልሰው የመምጣታቸው እውነት፡፡ የባሰባቸው ደግሞ፣ አንድ ለአምስቱን ባንድ ላይ ለማስተናገድ ፍቃደኛ ናቸው፡፡

አሁን ባለፈው፣ አንዷ የቤትኪራይ ፍለጋ ስትዞር ሰፈራችን መጣች፡፡ የተሰበቡትን ወጣቶች ጠየቀች፡፡ “የሚከራ ቤት ይኖራል እዚህ አካባቢ?”

“አዎ! አለ አለ! ይሄው እዚህ አለ” …የራሱን ክፍል ሊያሳያት ይዟት ገባ፡፡በሩን ዘጋ፣ጭኗን ከፈተ፡፡ ከተሰበሰቡት ውስጥ የፈለገ ሁሉ እየገባ በሩን ዘጋ( አራት ሰው)… ( ይህ በጣም የለዘበ የአብሮ አደጎቼ እውነት ነው) … በርግጥ አሉ ደግሞ ያመጧትን ሴት ከሌላ የማየረጋሩ፣ ሌላው ካመጣትም የማይጋሩ፡፡
እዚህ ሰፈር ውስጥ ባሰብኩት ቁጥር የሚያሳዝነኝ የዳንኤል ነገር ነው፡፡ ካምፓስ ከመግባቴ በፊት፣ ሰፈር ስውል እንገናኝ ነበር፡፡ ወሬው ሁሉ ስለሴት ነበር ያኔ! እኔ እራሴ ሲያበዛው ያደክመኝ ነበር፡፡ ስለ ሴት እንደዛ በፍቅር ያውራ እንጂ ሴት መቅረብ ይፈራል፡፡ ቀርበው ሲያናግሩት ያልበዋል፡፡ ሰፈር ከሰው ጋር ሲሆን በሩቁ ይላከፋል፡፡ ተላክፎ መልስ የማትሰጠውን ሴት፣ በቀፋፊ ስድቦች እስክትርቅ ይሸኛታል… እዛ ውስጥ የምትንደፋደፍ ሚጢጢ ስነልቦናዊ ቀውስ አይቼ ነበር፡፡ ግን…. እዚህ ትደርሳለች ብዬ በፍፁም አልተበኩም ነበር… ባለፈው ዓመት ነው የነገሩኝ…. የግቢ ቆይታዬን ጨርሼ ስመለስ… “ ጌይ ሆኛል!” አሉኝ፡፡ አዘንኩ! በጣም አዘንኩ! ሳልፈቅድ እንባዬ ወረደ፡፡ እንዲያ ቢሆን ወዶ እንዳይደል አውቃለሁ፡፡ ፍርሃቱን ሰብሮ ወደ ሴቶች ማለፍ ስላልቻለ ነው በሌላ በር የገባው፡፡ እዚህ ውሳኔ ውስጥ ህመም እንዳለ ስለገባኝ አዘንኩ፡፡ ማድረግ የሚፈልገውን ማድረግ ባለመቻሉ፣ እራን ማከሙ ነው ለሱ… ብዙዎች በመጠየፍ ያዩታል ዛሬ… ሴቶች ያንቋሹታል፣ ወንድ እንዲሆን ያላገዙት ሁላ የሀሜት ቡሉኮ ለብሰው፣ በወሬ ከሰል አቀጣጥለው ይሞኩታል-ያከስሉታል- ይደፉ ያራግፉታል፤ ባይሰማቸውም! እነሱም እንዲሰማቸው አርገው ባያወሩም፡፡ ህመሙን ሊዘግብ የሾለ አፍ እንጂ፣ ህመሙን ሊያክም የፈቀደ ልብ የማን ነበረ- እንዲህ እያረግን ሰንቱን ገደልነው፡፡ ወንዶች ይንቁታል… ወንድነቱን “ለሴትነት” አሳልፎ የሸጠ፣ የተፈጥሮ ከሃዲ ያደርጉታል፡፡ …ቅዳሜ እና እሁድ ሽክ ብሎ ከቤት ይወጣል ብዙ ጊዜ፣ “አዲሳባ ሎደረግ ነው የሚሄዴው” ይላሉ፡፡ ከዳንኤል ጋር እንደበፊቱ አናወራም፡፡ በ “ሀይ” አጥር ላይ ነው ሰላም የምንባባለው፡፡ መንገድ ሳልፍ ባየሁት ቁጥር ግን፣ ዓይኖቹ ውስጥ የተፃፈ ስቃይ ይታየኛል፡፡ የነብሱ ረፍት ማጣት ይሰማኛል፡፡ መግባት የሌለበት ዓለም ውስጥ ገብቶ መረጋጋት ያቃተው አይነት ሰው፤ ራሱን ድንገት ቀውጢ ጦርነት ውስጥ አግኝት የሚይዝ የሚጨብጠው ያጣ አይነት ሰው! እንዲያ ሆኖ ይነበበኛል- በዐይኖቹ መስኮቶች ውስጥ!

እምቡሼ እምቡሼ የአብሽ ገለባ
ሜዳ ነው ብዬ ገደል ስገባ….” ባልንባት እዚህች ሰፈር፣ ብዙ አብሮ አደጎቼ ፈቅደው እና ስተው ገደል ሲገቡ አየሁ- እያየሁ ነው….

…አለች ደግሞ በልጅነታችን ህሉ ቁሉ ብለን እንጠራት የነበረች- ህሊና፡፡ ያወጣንላትን የዳቦ ስም ዋጋ ቢስ ላለማድረግ ነው መሰለኝ ቁሉ ነገር ሆና ያረፈች፡፡ ሱዳኖች፣ ቻይኖች ምናምን ነው የሚያወጧት እየተባለ ተወራ፡፡የሴት አገናኝ ደላሎች ጋር ፎቶዋን አይቸዋለሁ ብሎኛል እንደውም አንዱ፡፡ ትናንት የያዘችውን ስልክ ዛሬ የመያዟ አጋጣሚ ምንም ነው፡፡ የሰፈሯ ወንዶች ላይ እስኬሏን ሰቀለች፡፡ ሰላምታዋም ሆኖ ፊቷ ላይ የሚነበበው፣ “የልጅነታችንን እንርሳው ባካችሁ” አይነት ትዕዛዝ እና ልመና ነበር፡፡ ገንዘብ ላለው ሁሉ ገንዘቡ ነች፡፡ ገንዘብ እየበላች የምትታዘዝ “የወንድ ማሽን” ነበረች፡፡ አንድ የግል ኮሌጅ ገብታ ነበር፡፡ ክላስ አለብኝ ብላ ትወጣለች ከቤቷ- የምትገባበት ክላስ ግን ሌላ ነው እንደሰማነው፡፡ ቁጭ ብለው የአስተማሪን ቃል የሚሰሙበት ክላስ ሳይሆን የምትገባው…የገላ ተሳትፎ ያለበት ነበር፡፡ የሚገርመው….. እሁድ እሁድ ብትሞት ቤቴክርስቲያን አትቀርም፡፡ ለየኔ ብጤዎችም ሳንቲም ዘርዝራ አድላ ትመለሳለች፡፡ በሳምንት አንድ ቀን ቤተክርስቲያን ትስማለች- በሳምንት ቀሪውን ቀን በማንም ትሳማለች፡፡ ለኔቢጤዎች ሳንቲም ትሰጣለች- እሷ ግን በዶላር ትቀበላለች…. አታፍርም እኮ በዚህ የማይመጣጠን ድርጊቷ የአምላኳን ምህረት ትፈልግ ይሆናል- ተላላ አደረገችው እንዴ ይሄን ያህል?

ለነገሩ ድሮም ልጅ እያለን ሚስት መሆን ነበር የምትወደው፡፡ ሚስት አርገን ካላጫወትናት ሰበብ ፈልጋ ወደ ቤቷ ትሄድ ነበር፡፡ ትንሽ እንደተጫወትን… “እንግዴህ መሽቷል አሉ….በቃ ወደየቤታችን ሄደን እንተኛ…” ብላ ሃሳብ ታቀርባለች… ኸረ ውሽማ የሚባልንም ሃሳብ ከየት እንዳመጣችው ያኔ እሷ ነበረች ያስተዋወቀችን፡፡ ውሽማ ስንሆናት ታዲያ፣ “ውሽሞች ገንዘብ ይዘው ነው የሚመጡት፣ ገንዘብ ይዛችሁልኝ ኑ” ስለምትል ሰፈሩ ጭር እስከሚል ድረስ የቅጠል መዓት ቀጥፈን ይዘንላት እንሄድ ነበር- እቃቃ አይደል? የቅጠል ገንዘብ ነበር መገበያያችን፡፡ …..የያን ግዜ ቤታችን እኛ ግቢ ያለ ማድቤት… ከነተመስገን ቤት ጀርባ ያለው የሰንሰለት አጥር ወዘተ ነበር…. እዛ ገብቶ “የልጅ አዋቂ” መሆን ነው እንግዲህ….. የዛሬን አያርገውና ስንቴ ባሏ ሆነን ነበር የህሊና! እኛ ያችን እቃቃ እዛው ልጅነት ደጃፍ ላይ አራግፈናት መጣን ስንል( በርግጥ ብዙዎች ተሸክመናት መተናል) እሷ ግን ህይወቷ አረገቻት፡፡ እናም ይህችን የሰፈራችን ልጅ፣ ያኔ በቅጠል ገንዘብ እንዳልተኛናት፣ ባዕድ በእውነተኛ ገንዘብ ሲተኛት አየን… ከባልጩት የሚጠቁር አፍሪካዊ፣ ማዶ ሰፈር ድረስ ሸኝቷት ከመኪና ስትወርድ አየን…. አይተን ለወጋችን ማጣፈጫ አደረግናት…. ተይ አላልናትም…. በልባችን እየናቅናት( አንቺ የገንዘብ ባሪያ እያልን….. ዋጋ የተፃፈብሽ አሻንጉሊት እያልን…. ምን ያላልናት አለ?)…….. በዚህ ሁሉ መሃል ግን………..

አረገዘች!!

…..አባትየው ቀውጠውት ነበር አሉ ሲሰሙ- ልባቸውን ከልጆቻቸው እንደ ሰማይ ያርቁና እንዲህ ሲሆኑ አገር ይያዝልን ይላሉ!- የት ነበሩ ወደ እርግዝናዋ ስታዘግም? የት ነበሩ “ህሉ የሁሉ” ብለን ስናወራ! ጆሯቸው የት ወድቆ ነበር? የት??….

ወለደች፡፡ ምጥ ሲበዛባት፣ ሆስፒታል ተወስዳ በኦፕራሲዎን…. “ማህበራዊ ኑሮ” እዚህ ነኝ ኑ እያለ የሚጠራቸው የሰፈራችን እናቶች…. ተከትለው ሄዱ፡፡ ሙሉ ገላው ከሷ የሰውነት ቀለም የሚቃረን ነጭ ልጅ ወለደች! -ፈረንጅ! እንግዳ ፍጡር የመጣባቸው ያህል ደንግጠው ነበር አሉ- እናቶቻችን፡፡ ይሄው ልጁ ዛሬ እንደትንግርት እየታየ አድጓል- አፍ ፈቶ “የእናት ቋንቋውን” መናገር ጀምሯል፣ ህሉ አማረኛ የሚናገር ፈረንጅ ለሰፈሩ አበርክታ ተሰበሰበች፡፡ ያቺ ያለው የኔ የሚላት፣ የሌለው ወይኔ የሚልባት ህሊና የለችም ዛሬ፡፡ ክስት ግርጥት ብላ፣ መልከ መልካም ጣረ-ሞት መስላለች፡፡ መፈለግ ቢኖራት እንኳን የሚፈልጋት የለም፡፡ በሯ ፊት ለፊት ቁጭ ብላ… ወጣትነቷን በቁጭት ስትሰናበት አይቻለሁ…. ፍቺ የሌለው ፀፀት(ነው ቁጭት?) ፊቷ ላይ ሲሮጥ……..

ያ ደግሞ አለ… በመጠጥ የቆመው ፋሲካ! ጠጃም! ቢራኣም! ጠላኣም! አረቄያም! የሚጠጣ የማይመርጥ አልኮላም! ወጣትነቱን በአልኮል እያለቀለቀ የሚጠጣ ጉድ… ሁሌ ማታ ማታ ሰክሮ ይመጣል…. “እኔ ፋሲካ!” እያለ ይጮሃል፣ “እኔ ፋሲካ!” እናቱ ይሄን ድምፅ ሲሰሙ የውጭ በራቸውን ከፍተውለት ወደ ቤታቸው ይገባሉ… አመት ያልፋቸዋል ከሱ ጋር በጠጣ ቁጥር መጯጯህ፣ መነታረክ ካቆሙ፡፡ ቀን ቀን ጓደኞቹ መጥተው ፤ “ማዘር ፋሲካ አለ?” ሲሏቸው፤ “ሁል ጊዜ ፋካ የለም” ብለው ይመልሳሉ- መሰላቸት ሹፈት ያሰለጠናቸው እናት!…. አንዳንዴም፣ “ፋሲካ ይኖራል ማዘር” ብለው ሲጠይቋቸው፣
“ አሁን ይመጣል፣ ነገ ተመለሱ” ይላሉ፡፡ ከየት እንዳመጧት እንጃ እቺን መልስ፡፡ የድሮ አራዳ ነገር ናቸው አሉ፡፡ ልጃቸው ግን የህይወት አራድነት ከቶም ከእናቱ ያልወረሰ… ቀን በቀን እራሱን በአልኮል እየበላ የሚገድል ፋራ ነው፡፡

እዚህች ሰፈር… ለመንግስት ስጋት ያልሆኑ፣ በ“አደገኛ ቦዘኔነት” የማይጠረጠሩ፣ እራሳቸው ለመውደቅ የዘመሙ እንጂ መውደቅ የሚፈራ መንግስትን ለመጣል የማይችሉ… በ“ፈርሶ” የፈረሱ ወጣቶች ብዙ ናቸው። አንድ ለአምስት የሚደረግ ልቅ ወሲብ እንጂ፣ “አንድ ለአምስት” የሚባል አደረጃጀት ምናቸውም አይደለም። ሙሉቀን ጫት ይዘው ከጫታቸው ጋር ጊዜያቸውን ሲያመነዥጉ ማየት እንግዳ አይደለም- አያስደንቅም! የሴት ቂጥ ሲከተሉ በረሃ አቋርጠው ቢሄዱ እንግዳ አይደለም……..
በየመጠጥ ቤቱ እየዞሩ ጊዜያቸው ላይ ሲያመነዝሩ ማየት እንግዳ አይደለም….. እራስን መግደልም እንግዳ አይደለም እዚህ!

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...