Tidarfelagi.com

ህክምናው ይታከም

የዛሬ ሰባት አመት ግድም ጆሮን እያመመኝ በጣም እሰቃይ ነበር፤ጉዳዩን መነሻ አድርጌ” መግባት እና መውጣት” የተሰኘውን ልቦለድ በመፃፍ ፤ስቃዩን ወደ ሳቅ ቀይሬዋለሁ፤ አሁን ያልፃፍኩትን ልንገራችሁ።

በድፍን ጦቢያ ዶክተር ነጋን የሚያክል የጆሮ ሀኪም የለም ተባልሁ! ወደ ፒያሳ ወረድሁ፤ ዶክተሩ በትህትና በጨዋነት መረመሩኝ፤ የሚዋጥ እንክብል አዘዙልኝ፤ ግን አልረባኝም። ቀጥየ ባልቻ ሆስፒታል ሄድኩ፤ የባልቻ ሀኪም ሶስት ቀን እያመላለሰ ሶስት መድፌ ቀረቀረልኝ፤ አልጠቀመኝም፤ በማስከተል ቦሌ ውስጥ ወደ የሚገኝ ያንገት በላይ ክሊኒክ ጎራ አልሁ ፤ ይሄ ሰውየ ሀኪም የሚለው ስም ከብዶት ለምን እንዳልጎበጠ ይደንቀኛል ፤ ሲያናግረኝ ንግግሩ ውስጥ ያለው ጭካኔ እና ገልቱነት ለማመን ይከብዳል፤የታመመ ሰው እንደ ወንጀለኛ የሚመለከት አይነት ነው። በመጨረሻ ጆሮየ ውስጥ ወናፍ የሚመስል ነገር አስገብቶ በተደጋጋሚ አየር ጠቀጠቀብኝ፤ የጆሮ ታንቡሬ ወንፊት ሳይሆን የቀረው እድለኛ ብሆን ነው።

ባሰብኝ።

በመጨረሻ ተስፋ ቆረጥሁና ሀኪም ቤት መሄዴን ርግፍ አድርጌ ተውኩ። ግን ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ አሜሪካን አገር የፌሌውሽፕ እድል አግኝቼ ሄድኩ። በብራውን ዩኒበርሲቲ ድጋፍ አንድ ሀኪም መረመረኝ። በረበረኝ ቢባል ይሻላል መሰል። አንድ ሰአት ባልፈጀ ጊዜ ውስጥ ጆሮየን እንደ ሞተር ፈትቶ ገጠመው፤ ለውጡ አስገራሚ ነበር። በታመምሁ ጊዜ ሸራተን ርችት መተኮሱን የማውቀው የርችቱን ህብረቀለም በማየት ነበር፤ከታከምኩ በሁዋላ የመስማት አቅሜ በረታ! አራት ኪሎ ሮሚና ካፌ ተቀምጨ፤ ፒያሳ ቼንትሮ ካፌ ውስጥ ሲያሙኝ ሁሉ ልሰማ እችላለሁ።🙂

በተለያየ ጊዜ በታማሚነትና ባስታማሚነት በሄድኩባቸው ጊዜዎች የተረዳሁትን እውነታ ላፍርጠው ፤ የአገራችን ህክምና ጥራቱ የነተበ ነው ፤ ህክምናው ትምርት መታከም አለበት! በስነምግባር ደረጃም ብዙ ብዙ ይቀረዋል ፤ እዚህ ላይ በክምናው ውስጥ የሚከሰቱ ሃጢአቶችን ለመዘርዘር አልፈቅድም፤ሁሉም በየቤቱ የደረሰበትን ያውቃል፤ ከጥቂቶች በቀር፤ ያገራችን የህክምና ባለሙያዎች ብስጩ፤ ስልቹ በሽተኛ ማየት የሚያንገፈግፋቸው ናቸው፤በተለይ በሽተኛው ባላገር ከሆነማ ወዮለት! ባንዳንድ የጤና ባለሙያዎች አልፈርድባቸውም፤የሚያገኙት ደሞዝ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፤፤ ቤት ኪራይ ለመክፈል ልጅ ለማሳደግ አልፎ አልፎ ይልማ ስጋ ቤት ጎራ ብሎ ለመቁረጥ የተሻለ ገቢ ያስፈልጋቸዋል ፤ይህን ለማድረግ የተለያየ ቦታ መስራት አለባቸው፤ እንደ ዝዋይ የጋሪ ፈረስ ሳያርፉ በመስራት ሰውነታቸው ይደክማል፤ ናላቸው ይዞራል፤ይህ አመላቸውን ቢያመረው አይገርምም።

ያንዳንዶች ችግር በገንዘብ የሚመለስ አለመሆኑ ይገርመኛል፤ ለምሳሌ አንድ ጎበዝ የቀዶጥገና ሀኪም በከተማው ይከሰታል፤ ታማሚው ወደርሱ መጉረፍ ይጀምራል፤ይሄኔ እሱ ቀብረር ብሎ ማከም ያቆማል፤ክሊኒኩ በር ላይ ስሙን በግብዳው ይገደግና ሌሎች ጀማሪዊችን ቀጥሮ ያሰራል፤እሱ ፖለቲከኛ ይሆናል፤ወይ ጋዜጣ ቲቪ ላይ ሱቅ ብጤ ከፍቶ ወሬ ይቸበችባል፤ሙያ ስላለኝ በሙያየ ይሄን ህዝብ የማገልገል ህሊናዊ ግዴታ አለብኝ ብለው የሚያምኑ ጥቂቶች ናቸው።

የህክምና ባለሙያ ወዳጆቼ እውነቱን በመናገሬ ከምትቀየሙኝ ፤ከጥቂቶች አንዱ ወይም አንዱዋ መሆናችሁን አሳዩኝ።

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...