Tidarfelagi.com

‹‹ሃገሬ ቆማበት››

ቢሮ መግቢያዬ አካባቢ ዘወትር ማለዳ አላጣውም።

አንድ እግር የለውም።

ሆኖም ሁሌም ክራንቹን ተደግፎ በፍጥነት ወዲህ ወዲያ ይላል። ሁለት የባለፀጋ ልጆች የሚማሩባቸው ትምህርት ቤቶች ደጃፍ ነው ላይ ታች ሲል የሚያረፍደው። ልጆቻቸው ከመኪና ወርደው ሶስት አራት እርምጃ በእግራቸው ቢራመዱ እንደ እንቁላል ከሽ፣ ተወጥሮ እንደተነፋ ፊኛ ጧ የሚሉ ይመስል፣ የትምህርት ቤቱ ደፍ ድረስ መኪናቸውን ለማስጠጋት የሚተራመሱ ወላጆችን መኪኖች ወግ ወግ ማስያዝ ነው ስራው። ለዚህ ድካሙ ትምህርት ቤቶቹ መጠነኛ ደሞዝ በየወሩ፣ ወላጆቹ ደግሞ ደስ ያላቸውን በየቀኑ ይሸጉጡለታል።

ትምህርት ቤቶቹ ፊት ለፊት ያለው ጭማቂ ቤት ካንድም ሁለቴ አግኝቼው ‹‹ልጋብዝህ›› ብለው እዚያ ሰፈር ያሉ ቁርስና ጭማቂ ቤቶች ሁሉ በነፃ እንደሚበላ እና እንደሚጠጣ ነገረኝ። ‹‹ለምን›› ብዬ ስጠይቀው ‹‹የደርግ ወታደር ስለነበርኩ አሳዝናቸዋለሁ። በዚያ ላይ ስለማልለምን ደስ ይላቸዋለል። ለፍቼ ነው የምበላው። ያው እንደምታዩው አንድ እግር ባይኖረኝም ክራንቼን እግር አድርጌ ስሮጥ ነው የምውለው›› አለኝ።

በሌላ ቀን ካንዱ ቁርስ ቤት ቁጭ ብለን ስናወጋ ከቆየን በኋላ እያወቅኩ ግን ወሬ ለመቀጠል ብዬ ፣ ‹‹እግርህን ጦርነት ላይ ነው ያጣኸው አይደል?›› ብዬ የጅል ጥያቄ ጠየቅኩት።

‹‹ሁሉም ሰው እያወቀ ይጠይቀኛል….አዎ…እግሬን ለኢትዮጵያ ሰጥቻት ነው›› ብሎኝ የጀመረውን ቡና በወተት በፍጥነት አገባድዶ ወደ መኪናው ትርምስ ተመለሰ።

ህም።
አይገርማችሁም?
‹‹አዎ…ጦርነት እግሬን ቀማኝ….ለሃገሬ ስል አካሌን አጎደልሁ….ለዚህች ሃገር እግሬን ገበርኩ…›› ብሎ አልተነጫነጨም። እንደዋዛ ‹‹ ለኢትዮጵያ ሰጥቻት ነው›› ነው ያለው።

አመለካከቱም፣ አነጋገሩም ገረመኝ።

ከዚያ ወዲህ በየጠዋቱ ሳየውና ‹‹እንዴት አደርህ…እንዴት አደርሽ›› ስንባባል የመቅደስ ዓብይ ወግ ትዝ ይለኛል።

የመቅደስ ወግ ላይ ያለው እንዲሁ አንድ እግሩን ‹‹ለኢትዮጵያ የሰጠ›› የቀድሞው ሰራዊት ወታደርን አንድ ትንሽ ልጅ አገኘውና፣ ‹‹አንተ….አንድ እግርህ የት ሄዶ ነው?›› ብሎ ቢጠይቀው ምን ብሎ መለሰለት መሰላችሁ? ‹‹ሃገሬ ቆማበት ነው››

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...