Tidarfelagi.com

ሃይማኖት ወይስ ፖለቲካ

ያለፈውን አመት ለውጥ ተከትሎ ለአገራችን አንድነት፣ ለሕዝባችን ሰላም አደገኛ የሆኑ አጀንዳዎች በድፍረት ሲነሱ አይተን ደንግጠናል። ሰሞኑን ከኢትዬጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስትያን ጋር ተያይዞ እየጮኸ ያለው መንፈሳዊነት የነጠፈበት አጀንዳ ዋነኛው ነው።

የትላንት ታሪክ እንደሚነግረን አትዬጵያ-ጠል የሆኑ ኃይሎች ቤተክርስትያኗ ላይ አደጋ ሲጥሉ ቆይተዋል። ከጉዲት እስከ ማህዲስት፣ ከደርቡሽ እስከ ፋሽስት… ተጠቃሽ ናቸው።

አሁን ደግሞ ‘ቋንቋ’ን ተንጠላጥሎ የፖለቲካና የቁስ ሰቀቀንን ለማርካት ሩጫ ተጀምሯል። ይህ ግን መዘዙ ብዙ ነው። በተለይም በኦርቶዶክሳዊው የኦሮሞ ሕዝብ ላይ የሚፈጸመው ደባ ፌድራሊዝሙን በማዳከም ብቻ ‘ይቆማል’ ብሎ መገመት፣ ስህተት መሆኑን ለመረዳት እስከ ምጽአት ቀን መጠብቅን አይጠይቅም።

ቤተክርስትያኒቷ የምትመራበት መዋቅር ብቻ ሳይሆን፣ የመንፈሳዊ ሰውነትና የዕውቅት ብቃት ደረጃንም የደነገግ ቀነኖአዊ ሕግ አላት። እያንዳንዱ ነገር የሚወሰነው በዚህ መሰረትነው። እናም አገልጋይ ለመሆን የወሰነ ከድቁና ጀምሮ ሲጨርስ፣ ለቅስና ይማራል። እዚህ ከደረሰ በኋላ ውስኔው የመጨረሻ ነው። ቤተሰብ መመስረት የፈለገ ካህን ሆኖ ይቀጥላል። ዓለምን የናቀው ደግሞ ይህንን አይነት ህይወት ለዘላለሙ ይቀርበትና፣ በድንግልናው ጸንቶ ለጵጵስና ራሱን ያዘጋጃል። የቅዱሱ ሲኖዶሱም ሆነ የሀገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስነት የሚሾሙት እዚህኛው ምዕራፍ ከደረሱ አባቶች ብቻ ናቸው።

የኦሮሚያ ቤተክርስቲያንን ከመዋቅር ውጪ እንመሰርታለን የሚሉ ሰዎችን አጀንዳ የማይታሰብ የሚያደርገውም ይህ ነው። የቋንቋ ጥያቄ ሽፋን እንጂ፣ ችግር ሆኖ አይደለም። እኔ እስከማውቀው ድረስ በኦሮሚያ ካሉት 15 አገረ ስብከት፣ 11ዱን የሚመሩት የብሔሩ ተወላጆች ሲሆኑ፤ ሥራ-አስኪያጆቹን ጨምሮ በሁሉም ቤተክርስትያን ያሉ ሠራተኞች ኦሮሞዎች ናቸው። ስብከት፣ መዝሙር፣ ወለጋ አካባቢ ደግሞ ቅዳሴም ጭምር በኦሮምኛ ነው የሚካሄደው (የቅዳሴ መጽሀፍ ከመላው ኢትዬጵያ ቋንቋዎች ውስጥ በአማርኛና ኦሮምኛ ብቻ ነው የተተረጎመው። ዛሬ ድረስ የኤርትራ ቤተክርስትያን መንፈሳዊ ቋንቋ ግዕዝ እንደሆነ ይታወቃል።)
የኦሮሞ ብሔረሰብ ካፈራቸው ሊቀ-ጳጳሳት አንዳቸውም እብደት የገፋውን ይህን ጥያቄ ሲያነሱም ሆነ ሲደግፉ አላየንም። አልሰማንም።

እንዲህ አይነቱ አደጋው የበዛ አጀንዳን ሁሉም ኢትዬጵያዊ፣ የሁሉም እምነት ተከታይ በጋራ ሊቃወመው ይገባል። ምክንያቱም የዘረኝነት ጥያቄ ረክቶ አያውቅም፤ በቃኛንም አያውቅም፤ ከርዕትነትንም ጋር ዝምድና የለውም። ነገ ደግሞ ‘አዛን’ እና ‘አላሃ ዋክበር’ በኦሮምኛ ወይም በትግርኛ… ይባልልኝ ማለቱ አይቀርም። እናም ዛሬ ይህንን መሰል አፍራሽ አጀንዳ ለማምከን በጋራ መቆም ያስፈልጋል።

ነሐሴ 26/20011
አዲስ አበበ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...