የሳመኝ ቀን “በናትህ ይሄን ነገር በምስክር ፊት አድርግልኝ” ብለው ደስ ባለኝ። ስሜ መራራ ነዋ። ሳመችው እንጂ ሳማት አይባልልኝማ! እርግጥ የሳመኝ እለት ያልኳችሁ ቀን ማለት በዋዛ የተገኘ እንዳይመስላችሁ
“ጌታ ሆይ ይሄ ሰው በወንድምነት ይሁን በባልነት ፍቅር የሚወደኝ መለየት የምችልበት ፀጋ ስጠኝ! …. ወይ ምልክት ነገር አሳየኝ! ….. ቢያንስ በህልሜ አንድ ጋቢ ለሁለት ስንለብስ ምናምን ……. አለ አይደል የሆነ ምልክት በቃ …… እኔ ልጅህ በውዝግብ ስንገላታ በቤትህም እንደሚገባህ እያገለገልኩህ አይደለም! (ይሄኛው በእርግጥ ለራስህ ስትል ባሪያህን አስባት አይነት ልምምጥ ነው። ውለታዬ አለብህ በዚህ እንኳን ክፈለኝ አይነት ሰፋጣም ነው።) ብዬ ፆም ፀሎት ልይዝ ትንሽ ሲቀረኝ ነው ያው ምልክት መሆኑ ነው መሳሙ!!
ከምልክቱ አስቀድሞ ከወራት በፊት
ሲሊፐር ያጠለቁ እግሮቼ የቸርቹን በር አልፈው ሲገቡ ራሴን አገኘሁት። ከቤት የወጣሁት ቁምጣዬን ሆዴን በሚያሳይ አላባሽ ለብሼ ከእግዜሩ የተጣላሁበት የወንድሜ መቃብር ጋር ለመሄድ ነበር። እንደለመድኩት
“የማይሰማ ፀሎት ለምን እፀልያለሁ? ወይም ቁልጭ አድርገህ በዚህ ጉዳይ አትፀልዩ ምናምን ብለህ ህግ ብታወጣ ጥሩ …… በደፈናው ብቻ አንኳኩ …… ብቻ ፀልዩ አልክ …… ከዛ ግን የማትሰማው ፀሎት ብዛቱ …..” እያልኩ ከራሱ ከፈጣሪ ጋር እየተነታረኩኝ በእግሬ እስኪደክመኝ ከተጓዝኩ በኋላ ነው ድንገት አቅጣጫዬን ወደቸርቹ ያዞርኩት ……… ገባሁ።
ለወራት ያላዩኝ አስተናጋጆች በፈገግታ ሰላም እያሉኝና አለባበሴን እየገላመጡ ክፍት ቦታ አሳዩኝ። እሱ መድረኩ ላይ አይኑን ጨፍኖ ፒያኖውን እየመታ ይዘምራል።
ከተደረገልኝ በጎነትህ
አንዳችም ለእኔ የማይገባ ነበር
በቸርነትህ አድርገሃልና እደነቃለሁ
አብዝቼ ተመስገን እላለሁ ……
እያለ በሚጣፍጥ ድምፁ ይዘምራል:: ህዝቡ ቆሞ ግማሹ እጁን ወዳፈጣሪ አንስቶ …. ግማሹ ወሬ እያየ ግማሹ ጨፍኖ አብሮት ይዘምራል። መግባቴን ያወቀ ይመስል አይኖቹን ገልጦ አየኝ። ተያየን!! ፈገግ ብሎ አይኖቹን ጨፍኖ ማስመለኩን ቀጠለ። ያስተዋለ ሰው ምላስ ማሟሻ ሆኜ መክረሜን እያወቅኩት ሳቅ ብዬ ተቀመጥኩ። የዛን ቀን ስንወጣ ሲንደረደር መጥቶ አቀፈኝ (በጌታ ፍቅር ነው ይህኛው)
“ስለመጣሽ ደስ ብሎኛል። ሳይሽ በጣም ነው ደስ ያለኝ” አለኝ ወደጆሮዬ ጠጋ ብሎ “ምንም እንኳን ቸርች ለመምጣት አስበሽ ባትመጪም!” አለኝ። አለባበሴን መሆኑ ገብቶኛል።
ከዛን ቀን በኋላ የጌታ ፍቅር ይሁን የሱ ፍቅር መጀመሪያ ሰሞን ባልለየሁት ምክንያት ቸርች እመላለሰው ጀመር። በሳምንት እሮብና እሁድ መደበኛ የቸርቹ ፕሮግራም አልበቃ ብሎኝ …… አርብ የአገልጋዩች ፕሮግራም …… ቅዳሜ የወንድሞች ፕሮግራም …… ማክሰኞ የማለዳ ፀሎት ….. ብቻ ምንም ይሁን እሱ ካለ እኔ አለሁ!!
ፕሮግራሞቹ ሲያልቁ እስከቤት መንገድ እያራዘምን ወክ እያደረግን የባጥ የቆጡን እናወራለን። ጠዋት ተነስቶ ትምህርት ቤት ድረስ ሸኝቶኝ ይመለሳል። የማነባቸውን መፅሃፍቶች ተከራይቶልኝ ይመጣል:: … አንብቦ ነው የሚሰጠኝ… እኔ አንብቤ ስጨርስ መፈጠራችንን ለማያውቀው ደራሲ ሂስ እንሰጣለን…. እንከራከራለን….
ማታ በየቀኑ ደብዳቤ ይፅፍልኛል… እኔም እፅፍለታለሁ … ጠዋት ስንገናኝ ደብዳቤዎቹን እንቀባበላለን:: ከሰዓት ከስራ የሚወጣበት ሰዓት ከኔ ጋር ስለማይዛመድ ከሱጋር ሳይክሌን እየገፋሁ በእግሬ 40 ደቂቃ የሚወስድብኝን መንገድ በሳይክል በ10 ደቂቃ እልሰዋለሁ።
ደጋግመን የሄድንባቸው መንገዶች ኮቴያችንን ሰምተው እስኪያውቁት …. በየመንገዱ ያሉ የንግድ ቤት ዘበኞችና ቋሚ የኔቢጤዎች እንደወዳጅ ሰላምታ መስጠት እስኪጀምሩ …… ቤተኞቼም የኔና የእሱን አብሮ መውጣትና መግባት ከመልመዳቸው የተነሳ እሱ የአጥሩን በር ሲያንኳኳ ‘ሜሪ መጥቷል!’ ብለው መጥራት እስኪለምዱ ….. ከዚህን ያህል የጊዜ ለውጥ በኋላ ነበር የሳመኝ። (መፀለይ ይነሰኝ?) እንደጠጣ ሰው ጀብረር አድርጎኝ ነበር አሳሳሙ ሳልዋሻችሁ (ቤተኞቼ አንድም እሱን ስለሚያምኑት ‘የጌታ ሰው’ ስለሆነ … ሁለትም ለወትሮው በየቀኑ የሆነ ጥፋት የማጠፋ የነበርኩትን ልጅ ስላለዘበላቸው … በተጨማሪም ወደ ቸርች ስለተመለስኩላቸው …. ከእርሱ ጋር መውጣት መግባቴ ብዙም አልጎረበጣቸውም)
ይሄ በሆነ በጥቂት ቀን “የስራ እድገት አጊንቼ ሌላ ሀገር ልሄድ ነው አለኝ!” እንዴት እንደሚነግረኝ አፉ ላይ ቃላቶቹን ሲያንገዋልላቸው ቆይቶ
“እኔስ? ስምንት ወር ሙሉ እጅህን ተመርኩዤ ሀዘኔን የረሳሁት እኔስ? ትተኸኝ ስትሄድ ምን ልስራ? በቀን ሁለቴ የማይህ እኔስ አንተ የሌለህበትን ቀን እንዴት ልለፍ? ምን ልስራ? አንተ ሳትኖር ማነኝ? ንገረኝ ምን ልሁን?”
እንደሚሄድ እርግጠኝነት ነበረው ድምፁ ስለዚህ ‘ቅርልኝ’ ልለው አቅሙ አልነበረኝም። ምን ያህል በፍቅር ሙክክ ብዬ እንደበሰልኩ የገባኝ የዛን ቀን ነው። ለወትሮ በሰው ፊት ማልቀስ ያውም ለማልቀስ ምክንያት በሆነኝ ሰው ፊት ማልቀስ ሽንፈት የሚመስለኝ እኔ ……. በሱ ፊት ተዝረከረኩ።
“በቃ አልሄድም እቀራለሁ::” አለኝ “በቃ አንቺ ትምህርትሽን እስክትጨርሺ የትም አልሄድም ይቅር !” አለኝ አቅፎ እያባበለኝ። አዲሱ ስራው አዲስ በተከፈተው የአቢሲንያ ባንክ ማናጀር ሆኖ ነው የሚሄድ የነበረው። ገና እንደተመረቀ ነው አሁን የሚሰራውን ስራ አጊንቶ የጀመረው። በአንድ አመቱ አሁን ያገኘው እድገት ለእሱ ምን ያህል ትልቅ ነገር መሆኑን አውቃለሁ። ‘ትቼልሻለሁ’ ሲለኝ የባሰ ሙክክ ከማለት ውጪ ምርጫ ነበረኝ? እኔ ደግሞ አስራ ሁለተኛ ክፍልን ገና መጀመሬ ነበር። ተስማማን!! በሆነ መልኩ ራስ ወዳድ እንደሆንኩ ገባኝ።
“ይዘኸኝ ሂድ!” አልኩት በነገታው ጠዋት ትምህርት ቤት ሊሸኘኝ እንደመጣ እስክነግረው ጓጉቼ እላዩ ላይ እየተንጠለጠልኩ ምን እንዳልኩ ገብቶታል። ግን ማመን አልፈለገም።
“የት ነው ይዤሽ የምሄደው? የምትዪው የማስበውን ከሆነ…. አይሆንም!!” አለኝ ኮስተር ብሎ
“ለምንድነው የማይሆነው?”
“ስለምወድሽ ነው የማይሆነው!! …የኔ ሚስት በስነስርዓት ለቤተሰቦቿ ሽማግሌ ልኬ …. ቸርች ቆሜ በጌታ ፊት ቃል ገብቼላት …. በቤተዘመድ ተመርቀን ….. ነው የማገባሽ! በፍፁም እንደወመኔ ብድግ አድርጌ ይዤሽ አልሄድም። ትምህርትሽን በጥሩ ውጤት ትጨርሻለሽ …. እንደህልምሽ ህግ ትማሪያለሽ ….. ስትመረቂ ከፈለግሽ የምርቃትሽ ቀን ሰርጋችንን ማድረግ እንችላለን።” አለኝ ኮስተር ብሎ ቀጠል አድርጎ “አንቺ ግን የምርሽን ነው?”
“እሱማ የምሬን ነው። ቆይ ምንድነው ያልከውን ሁሉ ከማድረግ የሚያግደኝ? ሰሞኑን ሽማግሌ ትልካለህ …. ከዛ ቸርች ሄደን ቃል እንገባባለን…. ይዘኸኝ ትሄዳለህ …. አንተም ስራህን እኔም ትምህርቴን …”
“እ እ አይሆንም አልኩ አይሆንም!” አለኝ ከአፌ ቀምቶ “እብድ እኮ ነሽ …”
ማታ ምን አቅብጦኝ እንደሆነ ሳላውቅ ለማሚ ነገርኳት። በቤቴኮ ‘እንዴት ያለ የተባረከ ልጅ ነው::’ ብላ እንድታሞግስልኝ ነበር:: ቦንብ ማፈንዳቴ አልታወቀኝም። ከዛን ቀን በኋላ እሱ እኛ ቤት በምንም ሰበብ ቢሆን እንዳይመጣ ለእርሱም ለወንድሜም ማስጠንቀቂያ ተሰጠ። ትምህርት ቤትም ሆነ ቸርች ወይ ማሚ ወይ አባቴ ሆኑ የሚያደርሱኝ። ቸርች የምሄድባቸው ቀናት ተወሰኑልኝ። እሱም ቸርች ማስጠንቀቂያ ደረሰው። አንድ ሳምንት ሳናገናኝ አለፈ። … እንደዛ እንደመልዓክ የሚያዩት ቤተኞቼ …. ሲያዩት ሁላ የሞት መንፈስ እንዳዩ ይሸሹት ጀመር … ማሚ ጭራሽ ተከርብታ ‘ባንተ ተመስሎ ልጄን ከአላማዋ ሊያሰናክል ያለ መንፈስ ወጋሁ!!” ብላዋለች🤣 ለትምህርት ቤት ሁላ ማንም ቢጠራኝ እንዳያስጠሩኝ መልእክት ተላለፈ። በርቀት መድረክ ላይ ብቻ አየዋለሁ።
(ምንም አልገቡኝም:: ቀላሉ መንገድ ከኔጋር ማውራት ነበርኮ … እውነቱንኮ ነግሬያቸዋለሁኝ… )
ከዛ ግን ያቺ እንቢ ባዩዋ እኔ ሁሉንም “የራሳችሁ ጉዳይ!” አለች ከትምህርት ቤት አሞኛል ብዬ አስፈቅጄ ስራ ቦታው ስበር ደረስኩ ሲያየኝ ሊጮህ ሁላ ዳዳው በደስታ ከመሬት አንስቶ አየር ላይ አሽከረከረኝ።
“የማብድ መስሎኝ ነበር::” አለኝ ፀጉሬን.. አንገቴን .. ጉንጬን … ከንፈሬን … እየሳመ… እንደሌላው ቀን ለሚያየው ሰው ሁላ ሳይጨነቅ
“አሁንስ ይዘኸኝ አትጠፋም?” አልኩት
ፈገግ ብሎ “መቼ?” አለኝ
One Comment