Tidarfelagi.com

ሁለቱን ባሎቼን ላስማማ እያሸማገልኳቸው ነው (ክፍል አስር)

14ማለትሽ አይቀርም ነበር። በእርግጥ እንደወሰለተ ነው እንጂ የነገራት ሌላ ጣጣችንን አልነገራትም።

መፅሃፍ ቅዱሱ እንኳን ፍቺን የሚፈቅድበት ብቸኛ ምክንያት ውስልትና መሆኑን እያወቀች። እሱን አልፋ ስለይቅርታ ስትሰብከ አመሸች።
“ውይ አንጀቴን በላው! ሌላ መሄጃ የለኝም …. ጉዴን ልንገርሽና እንደፈለግሽ አርጊኝ ብዬ ነው አንቺጋ የመጣሁት አንቺው አማልጂኝ! ያለእሷ መኖር አልችልም ብሎ እግሬ ላይ ሲወድቅ አንጀቴን በላው! በጣም ነው የሚወድሽ” ብላ ጭራሽ ልትቆጣኝ ሁላ ዳዳት።
ከዛ ግን ለብቻዬ እንዲህ አለችኝ
“ትዳር አንዴ ከገባሽበት በኋላ ያውም ልጅ ካመጣሽ በኋላ በሰበብ አስባቡ ብድግ እያልሽ ወጥቼበታለሁ የምትዪበት አይደለም።” (በሰበብ አስባቡ አይደለምኮ ብዬ የሆነውን ሁሉ ልነግራት እፈልግና እተወዋለሁ። ምናልባት ‘መጀመሪያ እረፊ ብዬሽ ነበር’ መባልን ፈርቼ? ወይም ‘ልክ ነበርሽ እሱን ተከትዬ መምጣት አልነበረብኝም’ ማለት ሽንፈት መስሎኝ ወይም አሁንም ለእሱ ያለኝ ፍቅር እርሱን እንዳትጠላብኝ እንድሰስት አድርጎኝ። ዝም ብዬ ሰማሁ ብቻ)
“አግብተሽ ያውም ከልጅ በኋላ ብቻሽን ህይወትን መግፋት ለሴት ልጅ ከባድ ነው። አንቺ ገና ህፃን ነሽ ለዛ አልተዘጋጀሽም! ቅስምሽ ይሰበራል። ምንም አድርጎሽ ውጪ ዝቅ ተደርገሽ የምትታዪው አንቺ ነሽ። ምንም በደል ደርሶብሽ ትዳርሽን ፍቺ ያው ፈት ነሽ! የምታገኚው ወንድ እንኳን ፈት መሆንሽን ሲያውቅ ያጎድልሻል።” አለችኝ (ይሄኛው ምን ማለት እንደሆነ የገባኝ ዘግይቶ ነው።)
ከምክሩ በኋላ በዘይትም በእጅ መጫንም ተፀልዮልን። “በጌታ ስም ትዳራችሁ ካሁን በኋላ የሰይጣን ሴራ መጠቀሚያ አይሆንም። ልጆቼን ልትዋጋ በአየር በባቡር በየብስ …… የምታንዣብብ በየሱስ ስም የከሸፈ ይሁን” ተብለን ታረቅን።

እኔና እሱ መሃል ሶስተኛ ሰው ገባ! ያ ለእኔ የትዳራችን መፍረስ ጅማሬ ነበር። በዚህ ሁሉ መሃል እያለፍን ሌላ ሰው የማይረዳው የእኔና የእሱ ስሜት አለ። በቃ ለሌላ ሰው የማይገባው ያንን ድንበር አልፈን ተጣልተን እንዲያሸማግለን ሶስተኛ ሰው ስንጠራ መግባባት አቅቶናል።
ክረምቱን ፀጊ መጣች እኛጋ። ሁሉ ሞላልኝ። እሱም ቦረቀ። ሁለቱን ወር እራሱ ፈጣሪ ተገልጦ ‘ምን ልስጥሽ?’ ቢለኝ
‘እያየኸኝ? ከዚህ በላይ ምን እፈልጋለሁ?’ ነበር የምለው። ደስታ አልፈጅም ብያችሁ የለ? በቃ ምንም ነገር ከዚህ ደስታ አይበልጥም አልኳ!! የልጄና የአባቷን መፍለቅለቅ እያየሁ ይሄን ቤት ለማቆየት መክፈል ያለብኝን እከፍላለሁ አልኳ!
አልኩ ነው እንግዲህ …….. ትምህርት ሲጀመር ጸግዬን ወደነበረችበት ወሰድኳት። ንትርኩ የተጀመረው ይሄኔ ነው። “ልጄ አብራኝ ትሁን!” አለ። እኔም ልጄ አብራኝ ብትሆን ደስታዬ ልክ የለውም። ግን የሚያስከፍለኝን ደግሞ አውቀዋለሁ። ልጄን እቤት እየተውኩ ምን አይነት ትምህርት ነበር የምማረው? ከዛ ደግሞ እነማሚን በቃ ልጄን ወስጃለሁ ካልኳቸው በኋላ የሆነ ቀን ቢባርቅበት አይ በቃ ደግሞ ትመለስ ልላቸው ነው? በዛ ላይ እዛ የለመደችውን ድሎት በሰዓቱ እኔ አልሰጣትም። የነበረው አማራጭ ሁለት አመት ታግሼ ልጄን በሙሉ አቅሜና ትኩረት ማሳደግ ነበር።

“ለሁለተኛ ጊዜ ልጄን ቀማሽኝ!” የንትርክ ሁለት ነጥብ ሆነ። ይችልበታል! እናም በዚህ ጉዳይ ሁሌ ራሴን እንድወቅስ ….. ራስ ወዳድ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ አደረገኝ። እናም ይሄን ነጥብ አንስቶ ንትርክ ሲጀምር እንደጎዳሁት ስለሚሰማኝ ሁሌ ይቅርታ እጠይቀዋለሁ። እውነታውንኮ ልቤ አሳምሮ ያውቀዋል። ልጄን ባመጣት የሆነ ቀን ትምህርቴን አቆማለሁ። ግን ደግሞ እሱም ልክ ነው ልጁን ነው ከአጠገቡ ያጣው። እሱ እንደአባት ሃላፊነት ወስዶ ቀን ከሌት ልጁን ይንከባከባል ብዬ 100 % እሱን ማመን ልቤ ከበደው። ስለዚህ በራስ ወዳድነቴ ፀናሁ!!
ከዚህ በኋላ ያለው አንድ አመት አዙሪት ነው። እያንዳንዱን ዝርዝር ብፅፍላችሁ ምክንያቱና ሰዎቹ ይቀያየራሉ እንጂ ሂደቱ ያው ነው። አንድ ወር እፍፍፍፍ ብለን እንፋቀራለን ከዛ በሆነኛው ሰበብ እንጣላለን ወይ ይጠልዘኛል ወይ ሞልጬው ወደዶርሜ እመለሳለሁ። በነገታው ትምህርት ቤት ይመጣል እማ አይለመደኝም ይላል። ሁለት ቀን አኮርፋለሁ ከዛ ደግሞ እፍፍፍፍፍፍፍ …….
ደግሞ የሆነ ቀን እኔው ደሙን አፈላዋለሁ። እንፋታ በቃ መዝሙሬ ሆነች። ያብዳል። ይቅርታ እጠይቃለሁ ….. ደግሞ እንታረቃለን።
ለውጡ ምንድነው መሰላችሁ? ያቺ ምስኪኗ ሜሪ ድራሿ ጠፋ! ይህችኛዋ በራሷ የማትተማመን ‘ሽቶ ሸተተኝ’ ብላ ሀገር ይያዝ የምትል። (እርግጥ ሸቶኝ ነው። ፓንቱ ድረስ የሴት ሽቶ ምን ይሰራል? ) ‘ደብዳቤ ሴት ፅፋልህ አልነገርከኝም’ ብላ እሪሪሪሪ የምትል …….. ራሴን እያየሁት ሌላ ሰው ሆንኩ። በጣም የምጠላት እና ልሆን የማልፈልጋት መንቻካ ሴት ሆንኩ። በፊት እንዳይናደድ ሰማይ ከምድር የምገለብጥ ልጅ ሲናደድ እሳት ለኩሼለት ሄዳለሁ።
አሁን እንደበፊቱ ሰው ሰማ አልሰማ ችግሬ አይደለም። ይሄኔ ስንጣላም ስንታረቅ ጓደኞቼ ወይም ሰፈር ያውቃሉ። እርግጥ ዶርም ድረስ መጥቶ አንጥፎኝ ያውቃል እና ላያውቁ የሚችሉበት ሁኔታ አልነበረም። ብቻ አቡካካነው። ስንታረቅ ሁሉ እንደነበረ ቢመስለንም አልነበረም።
የሆነ ቀን ከአንዱ የፈረደበት ተማሪ ጋር የሙዝ ገበያ እያወራሁ እየገለፈጥኩ አምሽቼ ወደዶርሜ ገባሁ። መጥቶ ሲያስጠራኝ የነገር ዲዘርት ሊያበላኝ እንደሆነ ሳልጠረጥር ዊን ዊን እያልኩ ተንደርድሬ ወረድኩ። ሁለቱን እጆቼን ጭብጥ አድርጎ እያሳመመ አርገፈገፈኝ። የተፈጠረው ስላልገባኝ የያዘኝ እጁ ስለሚያም ለማስለቀቅ እታገላለሁ።
“ማነው?”
“ማነው ማን?”
“ቅድም አብሮሽ የነበረው? ከዛሬ ጋር ብዙ ጊዜ ነው አብረሽው የነበርሽው! ማነው?” ሲለኝ የፈረደበት ልጅ ትዝ አለኝ
“ኸረ ማንም አይደለም በጌታ ! ከሰው ሰው ጋር እንዳትጣላ?” ዘግይቻለሁ ልጁን ዘመዶቹን የሚያስረሳ ቡጢ ጠብቶት ነው እኔጋ የመጣው።
ልጁ ደግሞ ወሬ አማረልኝ ብሎ ከሰይጣን ጋር እንደተፋጠጠ ሳይገባው “ሜሪ ቀሽት ልጅ ናት” ምናምን ብሎ ዘላብዷል።እኔኮ ብድግ እያልኩ ባምፅም መጽሃፍ ቅዱስ ሳጠና እንደማደጌ እግዜሩን እፈራለሁ። መጀመሪያ የዘፈንኩ ቀን ዝናብ ሲዘንብ በኔ ምክንያት መብረቅ ሊዘንብ ነው ብዬ የፈራሁ ሴትዮ ነኝ። አንድ የሆነ ቆንጅዬ የክፍላችን ልጅ ቸኮሌት ገዝቶ ሰጥቶኝ ስለበላሁ በከፍተኛ የፀፀት መንፈስ የምናዘዝለት ካህን ባገኝ “አባ በድያለሁ በትዳሬ ላይ ማግጫለሁ” ልል ትንሽ የቀረኝ ሴትዮ ነኝ።
የዚን ቀን ዓይኖቹ ሲያስፈሩ
“የሌላ ሆነሽ ከማይ ገድዬሽ ሞታለሁ!” ያለኝን አመንኩት። የንዴት አይደለም። የምሩን እንደሚያደርገው ያስታውቅ ነበር።
የሚያውቀን ሁሉ “አንድ ቀን ይገላታል!” ይላል። የኔ ቤተሰቦች “የሆነ ነገር አድርጎባት!” ነው ብለው ወጥረው ይፀልያሉ። ጭራሽ ከጅምሩ ያልነበሩ የሱ ቤተሰቦች በተቃራኒው ባለቀ ሰዓት መጥተው “ልጃችንማ የሆነ ነገር ሆኖ ነው በሴት ፍቅር እንዲህ አይኮንም ፀበል ይግባ!” ይሉኛል ከነሱ ብሶ
ጓደኞቼ ቢሞቱ እሱን በእኔ ፊት አያሙትም።
ምንም ሆኜ ብመጣ
“ኸረ አርፈሽ ቁጭ በይ እነሱ ነገ ታርቀው አልጋቸው ላይ ሆነው። ‘ይህቺ ወሬኛ እንዲህ አላለች መሰለህ?’ ሊባባሉብን ዝም በይ ነገ ይታረቃሉ” ይባባላሉ።
ደግሞ የምራቸውን ነውኮ ‘ውይ በቃ ይሄማ የመጨረሻቸው ነው!’ ሲባል በነገታው እኛ እፍፍፍፍፍፍ ብለን የሚሪንዳ ቆርኪ ለሁለት ሻወር ለመውሰጃ ይበቃናል። እንላለን። እዚህጋ ብጠየቅ ምን እዛ ትዳር ውስጥ እንዳቆየኝ አላውቅም። በየቀኑ አዲስ ነገር እንደማይፈጠር አውቃለሁኮ ግን በቃኝ አልልም። ምን እንደፈራሁም አላውቅም። ብቸኝነቱን ነው የምፈራው? ፍቺውን? እሱን ማጣቱን? አላውቅም ምናልባት እሱ ናት ያላትን ሜሪ እወዳታለሁ ይመስለኛል። ልዩ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ የሚያደርገኝን …….. ብቻ አላውቅም። ለስድቡ ለምቱ ለሌላው ለእያንዳንዱ ጥፋት የራሴን ምክንያትና ሰበብ እደረድራለሁ። ለውስልትናው ግን ምንም ሰበብ ብሰጠው ልክ አይደለም። ልክ እንዳልሆነ እያወቅኩም አልፈዋለሁ። እንደበፊቱ አያምም …….. እንደመጀመሪያው አይጠዘጥዝም። ግን አዙሪት አለው ተመሳሳይ ሂደት እዞራለሁ!!
ቸርቹን እሱም እርግፍ አድርጎ ተወው ጭራሽ ክለብ ይዞኝ ወጣ። ድሮ በመዝሙር እንዳልተባረክን ሙዚቃ መገባበዝ ያዝን …..በዛኛው ህይወቱ ዲጄ ሁላ ሆኖ የሚያውቅ ቀውጢ እንደመሆኑ ሙዚቃ ምርጫ ሲያውቅበት ….. ማሪንጌ ሬጌ ፖፕ ብለን ጨፈርን። (እነዚን ሁሉ ነገሮች አላውቅም ለምን ብሎ እንዳደረጋቸው። እሱ አንቺን ለማስደሰት ደስ የሚልሽ መስሎኝ ነው የሚለው። )

ከዓመት በኋላ ለክረምት ፀጊ እኛጋ መጣች በድጋሚ። እንደተለመደው ፈንጠዝያችን ተጀመረ። ይሄኛው ክረምት ግን ከአንድ ወር አላለፈም። አሁን ምክንያቱን በማላስታውሰው ምክንያት ንትርክ ጀመርን። ጸቡ እየተጋጋለ ሲሄድ ልጄ ስላለች ዝም አልኩ። አልቀረልኝም አንዴ በጥፊ ሲለኝ ልጄን ነው ያየኋት ፊቷ ላይ የነበረው መሳቀቅ ድንጋጤ ፊቷ አመድ መሰለ። የተመታሁ አልመስልም። የእጁ ምልክት የተሰመረበትን ፊቴን እያሸሁ ልጄን ማባበል ጀመርኩ። ምንም አልተናገርኩም። በቃ ምንም !!!
ጠዋት እሱ ስራ ሲሄድ ቀለበቴን አስቀምጬለት ልጄን ይዤ ሄድኩ። አላለቀስኩም። አልተገረምኩምም። ውስጤ ዝም ነው ያለው። በቃ እንዳከተመ ገባኝ!! ራሴን ስሰማው የገባኝ አሁን እሱ ከህይወቴ ቢጎድል አልጎዳም! ሳላየው ሳምንት ሲሆን የማብድ የሚመስለኝን ባሌን ስለመለየት ሳስብ እርፍት ነው የተሰማኝ። እቤት ስሄድ ለማሚ መፋታት ነው የምፈልገው አልኳት። ገባት! ዝም አለች አልመከረችኝም። ምንም ቢመጣ እቀበላለሁ። ተመርቄ ስራ እይዛለሁ። ልጄን አሳድጋለሁ።

ስመለስ መነጋገር አለብን ብሎ የቀጠረኝ እሱ ነው። ተገናኘኝ!! ምንም ቢፈጠር የቃልኪዳን ቀለበቴን እንደማላወልቅ ያውቃል። የእውነት የሚመስለኝ የነበረው ያ ማለት ቃሌ ነው። ያ ማለት ፍቅሬ ነው። ያ ማለት እኔና እሱ ብቻ ማንም ሳያየን በእግዜሩ ፊት እንደሚስት በህመም በድሎትም ብዬ የገባሁት ቃሌ ነው። (እርግጥ ከገባሁት በላይ ኖሪያለሁኮ ስጠለዝም ሲማግጥም ብዬ የገባሁት የለም)
“እሺ እንለያይ!” አለኝ የምር ማመን አቃተኝ።
“ከምርህን ነው? ያ ማለት አትከታተለኝም? የፈለግኩትን እሆናለሁ ማለት ነውኣ? እንደመንፈስ ዙሪያዬ አታንዣብብም። አብሮኝ የታየ ወንድ አትደበድብም? ”
“አዎ አጠገብሽ አልደርስም። እንደፈለገሽ ሁኚ ቃሌ ነው። ብቻ እንደማፈቅርሽ እወቂ!” አለኝ
“እንደምታፈቅረኝ ጠርጥሬ አላውቅም። ችግሩ ፍቅርህን የምትገልፅበት መንገድ ልክ አይደለም። 24 ሰዓት ሙሉ አይንህ ስር የምትሆን ከማንም የማትገጥም ሴት እኔ መሆን አልችልም። ስታገኘኝ ያቺን ሴት አልነበርኩም። ስትወደኝ ያቺን ሴት አልነበርኩም። ያንተ ካደረግከኝ በኋላ ሌላ ሴት አድርጌ ልስራሽ ብለህ ትግል ነው የያዝከው። አይሆንም!” አልኩት
“አውቃለሁ” አለኝ። ተለያየን። ተለያየን ስላችሁ መቶ ጊዜ መተቃቀፍ መቶ ጊዜ መሳሳም እንደነበረውም አልደብቃችሁም። ለቅሶም ነበረው ከፈለጋችሁ። ለተወሰኑ ቀናት ማመን አቅቶኝ በየሄድኩበት ድንገት ዱብ ይል እንደው ብዬ እፈልገዋለሁ። የለም። ማታ ትምህርት ቤት ሲገባ ድንገት ከሆነ ሰው ጋር ካየኝ ፈነዳ ብዬ ብጨነቅም የለም። አልከፋኝም። ይልቅስ ነፃነት ተሰማኝ። በቃ ተለያይተናል። የምጠቀመው እሱ የሚሰራበት ባንክ ስለሆነ የሆነ ቀን ስሄድ የለም። ጓደኞቹን ስጠይቃቸው ስራ መልቀቁን ሰማሁ። የሆነ ቀን የጋራ ጓደኛችን ትምህርቱን ለሴሚስተር ዊዝድሮ ሞልቶ አዲስ አበባ ለእረፍት መሄዱን ነገረኝ። ጣዖቴ እንደነበረው ባሌ ሳይሆን እንደሰው አዘንኩ። እንዴት ስራ ይለቃል? እንዴት ትምህርቱን ያራዝማል?
ከአንድ ሴሚስተር በኋላ ባሌን ከተማ አየሁት። በጣም ከስቶ ጠቁሮ አምስት ወር ሳይሆን 5 ዓመት ያልተያየን ነበር የመሰለኝ።
“በየሱስ ስም ደህና ነህ?” አልኩት ደንግጬ ሳየው
“ደህና ነኝ!” አለኝ። “እቤት ሄጄ ነበር። ከቤተሰቤጋ ከሀ ለመጀመር እየሞከርኩ ነው። ቢያንስ አሁን ጴንጤ ስላልሆንኩላቸው ደስተኛ ናቸው!” አለኝ። ደስ አለኝ ያ የህይወቱ ጉድለት እንደሆነ አውቅ ነበር።
“አሪፍ አደረግክ!” አልኩት። እኔም የማውቃትን ደብዳቤ ፅፋለት አጊንቼ የተጣላሁትን ሴት ስም ጠቅሶ (የድሮ ፍቅረኛው ነበረች። ቤተሰቦቹ የሚወዷት ፍቅረኛው ነበረች።) ከሷጋ እንደሆነ ነገረኝ። እውነት ነው በቃ ተለያይተናል። እርግጠኛ ሆንኩ። ከዛን ቀን በኋላ እሷም ተከትላው መጥታ ኖሮ አብረው ከተማ አየኋቸው። ያ ማለት እቤቴ ሌላ ሴት እየኖረች ነው። አልጋችን ላይ ከሌላ ሴት ጋር እየተኛበት ነው። ያ ማለት በይፋ ትዳራችን ፈርሷል ማለት ነው። አልተናደድኩም። ጭራሽም አልቀናሁም። በቃ ለሱ ያለኝን ነገር ጨርሻለሁ። ወይም መሰለኝ።
መመረቂያዬ እየደረሰ ባለበት ጊዜ ውስጥ በባለጌ አይን ያየኝ ከነበረ ልጅ ጋር ባለግኩ። ዌል የባለግኩ የመጀመሪያ ቀን ቁጭ ብዬ ሳለቅስ አደርኩ። ትዳሬ እንደፈረሰ እያወቅኩ እንኳን የሆነ ሀጢያት የሰራሁ የረከስኩ ዓይነት መሰለኝ። ለምን እንዳለቀስኩ እንኳን አላውቀውም። ብቻ የዛን ቀን ነው ቃሌን ያፈረስኩ የመሰለኝ:: ….. የካድኩት አይነት……… የሆነ ቀን ከልጁ ጋር ወክ እያደረግኩ ስልክ ተደወለለት።
“እገሌ ነህ?”
“አዎ ነኝ ማን ልበል?”
“የሜሪ ባል ነኝ (ባልሽ ነው አንቺ አለኝ ዞር ብሎ ጥጋበኛ ነው ለራሱ። ደነገጥኩ)
“እኔ ሜሪ ከባሏ መለያየቷን ነው የማውቀው!” አለው መልሱ ድምፁን ላውድ አድርጎት እሰማዋለሁ
“እገልሃለሁ እናትህ ሆድ ብትገባ የምታመልጠኝ እንዳይመስልህ እገድልሃለሁ።” ይለዋል። ወላ አጠገባችን ያለ መሰለኝ ተንቀጠቀጥኩ። እሱ ምንም አልመሰለውም።
“ስትገለኝ ዝም ብዬ እሞትልሃለሁ እንዴ?” ይለዋል። ሲያብድ ይሰማኛል

ሁለቱ ባሎቼን ላስማማ እያሸማገልኳቸው ነው (ክፍል 11 – የመጨረሻ ክፍል)

One Comment

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...